የአሜሪካ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ሰላም ያሰፍናሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል (ቶፕ ዋር ፋይል)

ዓለም የተወሳሰበው የሩሲያና የዩክሬን የሰላም ድርድር ውጥን

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: November 20, 2024

በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜና እሑድ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትን የተመለከቱ ሁነቶች ተከናውነዋል፡፡ የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ሁለት ወራት ብቻ የቀራቸው ጆ ባይደን፣ ዩክሬን የአሜሪካን የረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች ተጠቅማ ሩሲያን ማጥቃት እንድትችል ፈቅደዋል፡፡ እነዚህ ሚሳይሎች ወደ ሩሲያ ዘልቀው እንዳይተኮሱ በአሜሪካ መንግሥት ክልከላ የተደረገባቸው ነበሩ፡፡ የዕገዳው መነሳት ሩሲያ ቅዳሜ ሌሊት በመላው ዩክሬን ያደረገችውን መጠነ ሰፊ የሚሳይል ድብደባ ተከትሎ የተደረገ ነው፡፡

ባይደን ለቡድን ሃያ ስብሰባ ወደ ብራዚል እየሄዱ ነበር የመጪውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ ባያፈርሰውም፣ ያወሳስበዋል የተባለለትን ዕርምጃ የወሰኑት፡፡ ይህ ክልሉን ወደ ከባድ ቀውስ ሊያመራ ይችላል የሚሉም ሲኖሩ፣ ሩሲያ በበኩሏ የአሜሪካ ሚሳይሎች ወደ ግዛቷ ከተተኮሱባት ፀቡ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጋር ይሆናል ስትል ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡

በታሪካዊዋ የጀርመን ከተማ በርሊን ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሠልፈኞች ጦርነቱ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ፑቲን ከሌሉ ጦርነት የለም›› እና ‹‹ፑቲን ሥልጣን ይልቀቁ›› የሚሉ መፈክሮች በሠልፈኞቹ ተስተጋብተዋል፡፡ ከሠልፈኞቹ መካከል ከወራት በፊት በሩሲያ እስር ቤት ውስጥ ለሕልፈት የተዳረጉት ቀንደኛ የቭላድሚር ፑቲን ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ ባለቤትን ጨምሮ የሩሲያ ተቃዋሚዎች ተገኝተዋል፡፡

ሮይተርስ፣ የባይደን የአሜሪካ ሚሳኤሎችን ለሩሲያ ጥቃት እንዲውሉ መፍቀድ፣ ዩክሬን የመደራደሪያ ኃይሏ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ሲል፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጉዳዩ ይፋ መደረግና በሚዲያ መራገብ አልነበረበትም ብለዋል፡፡ ‹‹ሚሳይሎቹ ለራሳቸው ይናገራሉ፤›› ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡

ነጩ ቤተ መንግሥትና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ደግሞ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ከበርካታ ሰሞነኛ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዋነኛ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካ ምርጫና የቱጃሩ ሪፐብሊካን ዶናልድ ትራምፕ እንደገና መመረጥ ይገኝበታል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. የ2020ን ምርጫ በጆ ባይደን ተሸንፈው የነጩን ቤተ መንግሥት እንዲለቁ ከተገደዱ በኋላ የምርጫውን ውጤት ባለመቀበል ደጋፊዎቻቸውን ለአመፅ አነሳስተዋል፣ በአንድ ወቅት የዘሞቷትን ስቶርሚ ዳንኤልስ ለምትባል የፍትወት ፊልም ኮከብ አፍ ማዘጊያ ከፍለዋል፣ የአሜሪካን ከፍተኛ ምስጢራዊ መረጃዎች በግል መኖሪያቸው አስቀምጠዋልና የመሳሰሉ በርካታ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክሶች ተቆልለውባቸው ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲማስኑ ከርመዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ትራምፕ፣ አሁንም ከብርቱ ፖለቲካዊ ፉክክር በኋላ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የአሜሪካ 47ኛ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

የመመረጣቸው ዜና ከተሰማበት ዕለት አንስቶ ካቢኔያቸውን እያዋቀሩና በአገር ውስጥና በውጭ የሚተገብሯቸውን ሥራዎችና ፖሊሲዎች እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በዓለም ሰላም አሰፍናለሁ የሚለውና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ቃል የገቡለት ከባድ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስና የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ዋና የትኩረታቸው አቅጣጫ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡

ዕውን ቃል እንደገቡት በመጪው ጃንዋሪ ሥራቸውን በጀመሩ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሩሲያንና የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ይቻላቸዋልን? ይህ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ተንታኞችና መገናኛ ብዙኃን ሲያራግቡት የከረመ ርዕስ ሆኗል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘሌኒስኪ ባለፈው ዓርብ እንደተናገሩት፣ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት በገቡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዩክሬን ከሩሲያ የገጠመችው ጦርነት ይቋጫል፡፡

ፎርብስም በድረ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፣ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው ቢሆን ኖሮ ቀድሞም ቢሆን ሩሲያ ዩክሬንን አትወርም ነበር፡፡ የትራምፕ የኮሙዩኒኬሽን መኮንን ስቴቨን ቹንግንም፣ የትራምፕ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመን ዓብይ ትኩረት የሩሲያንና የዩክሬን ጦርነትን በድርድር ማስቆም ይሆናል ብለዋል፡፡

ትራምፕ ባለፈው መስከረም ዩክሬን ቀደም ብላ የሰላም ድርድር ውስጥ ገብታ ቢሆን ኖሮ ተጠቃሚ በሆነች ነበር ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ ጆ ባይደንና ከማላ ሃሪስ በዩክሬን ላይ የተከተሉትን ፖሊሲም ሲተቹ፣ ‹‹የሰላም ድርድር ማድረግ ዩክሬን ከገባችበት ሁኔታ ሊብስ አይችልም…፡፡ ዩክሬን ወድማለች፣ ሰዎች ሞተዋል፣ አገሪቱ ፍርስራሽ ሁናለች፤›› ብለዋል፡፡

ክሬምሊን ቢያስተባብልም እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 7 ትራምፕ ለሩሲያ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ስልክ እንደ ደውሉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ትራምፕ ፑቲንን ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለውን ጦርነት እንዳታባብስ አሳስበዋል፡፡ እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ በምስጢር በተደረገው ውይይት፣ ትራምፕ በሚደረገው የሰላም ድርድር ሩሲያ በጦርነት ወቅት ቀድማ ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች መልቀቅ ሳይኖርባት ቢሆንም እንደሚደግፉ አልሸሸጉም፡፡

በትራምፕ የሽግግር ቡድን የቀረበ ሌላ የሰላም ድርድር ሐሳብ ደግሞ ዩክሬን ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን  (ኔቶ)ን የመቀላቀል ውጥኗንና ጥረቷን እንድትተው፣ አሜሪካ በበኩሏ ዩክሬን ለወደፊቱ በቀላሉ በሩሲያ እንዳትወረር የሚያስችላትን ትጥቅ እንድታቀርብ የሚሉ ሁኔታዎች እንደያዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡

በአዲሱ የሰላም ሐሳብ ከተካተቱት ውስጥ በሁለቱ አገሮች ድንበሮች መካከል የ800 ማይል የጦርነት ነፃ ቀጣና እንደሚመሠረት የተጠቆመ ቢሆንም፣ የትኛው የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚቆጣጠረው አልተገለጸም፡፡ ትራምፕ ከፑቲን ጋር አደረጉት በተባለው የስልክ ውይይት ወቅት አሜሪካ በአውሮፓ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ የጦር ኃይል እንዳላት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

ዘገባውን ተከትሎ ግን የክሬምሊን የሕዝብ ግንኙነት ጸሐፊ ድሚትሪ ፔስኮቩ አስተባብለዋል፡፡ ‹‹በመገናኛ ብዙኃን እየታተሙ ያሉ መረጃዎች፣ በታዋቂዎች ሳይቀር ያለባቸውን የጥራት ጉድለት አመላካች ነው፤›› ብለውታል፡፡

ቀደም ብሎ ፑቲን የሰላም ሐሳብ ያሉትን ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህም ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን አካሄዷን እርግፍ አድርጋ መተው ይኖርባታል፡፡ ብሎም ዩክሬን በአብዛኛው ሩሲያኛ ተናጋሪ ሕዝብ ካለባቸው አራቱ አወዛጋቢ ክልሎች ጦሯን ማስወጣት እንደ ቅድሚያ ሁኔታዎች ከተቀመጡ ነጥቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ዩክሬን ግን በሩሲያ ተወረዋል የምትላቸውን ክልሎች ለማስለቀቅ በጦርነት እንደምትገፋበት ዝታ ነበር፡፡ ትራምፕ ከተመረጡ በኋላ ዘሌኒስኪ፣ ‹‹ጦርነቱ በአፋጣኝ ይቆማል›› ማለታቸው የአሜሪካን የሰላም ጥረት ለመቀበል አዎንታዊ ምላሽ አድርገው የቆጠሩ አልጠፉም፡፡

እንደ ዎልስትሪት ጆርናል፣ የትራምፕ የሰላም ግፊት በአውሮፓ ባለሥልጣናት ዘንድም ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ‹‹ጊዜ ለዩክሬን እንዳላደላ›› በመገንዘብ የሰላም አማራጩን ተቀዳሚ ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ ሲል ዘገባው አክሏል፡፡

ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ በመስከረም ወደ አሜሪካ በማቅናት ‹‹የድል ዕቅድ›› በማቅረብ ቀጣይ የጦር መሣሪያና ገንዘብ ዕርዳታ የጠየቁት ፕሬዚዳንት ዘሌኒስኪ፣ ዛሬ ‹‹የሰላም ዕቅድ›› ወደሚለው የትራምፕ ሐሳብ ማማተር ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ቢቢሲ የቀድሞ የትራምፕ አማካሪንና ‹‹የምረጡኝ›› ቅስቀሳቸው  ተሳታፊ ብሪያን ላንዛን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ መጪው የትራምፕ አስተዳደር ከዘሌኒስኪ ‹‹ለሰላም ተዓማኒ የሆነ ርዕይ›› ይዘው እንዲቀርቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር የሚያተኩረው ሰላምን ለማስፈን እንጂ መሬት ማስመለስ ላይ አይሆንም በማለት፣ ዩክሬን በአሁኑ ጊዜ የሩሲያ አካል የሆነችውን ‹‹ክሪሚያ›› የማስመለስ ጥያቄ ላይ ሙጥኝ ማለት እንደሌለባት መክረዋል፡፡ ‹‹ክሪሚያ ሄዳለች›› ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሆኖም የትራምፕ ቃል አቀባይ እንዳሉት ብራያን ላንዛ ትራምፕን ወክለው አይናገሩም፡፡

ሩሲያ የክሪሚያን ሰርጥ እ.ኤ.አ. በ2014 በወረራ መቆጣጠሯ ይታወሳለል፡፡ ይንን ተከትሎ በተደረገ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ክሪሚያ በይፋ የሩሲያ አካል ብትሆንም፣ ምዕራባውያን በተለይም አውሮፓውያን የድምፅ አሰጣጡን ባለመቀበል እስከ ዛሬ ክራሚያ የዩክሬን እንደሆነች ያምናሉ፣ መመለስ እንደሚኖርባትም ይሞግታሉ፡፡ የዘሌኒስኪ አማካሪ ዲሚትሮ ሲትቪን ላንዛ ላይ ወቀሳ ሲሰነዝሩም፣ ጦርነት ፈላጊዋ ሩሲያ ሆና ሳለ፣ ዩክሬን ላይ ጫና ማሳረፉ ተገቢ አይሆንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሃል ዩኒቨርሲቲ ዕውቅ የሥነ ወንጀልና የስለላና ደኅንነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሮበርት ዶቨር፣ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 6 የዶናልድ ትራምፕን ዳግም መመረጥ ተከትሎ አራት ሁኔታዎች ቁልጭ ብለዋል ይላሉ፡፡

አንደኛው፣ የቀዝቃዛ ጦርነት አመክንዮ ወይም የትራምፕ ዕቅድ ይሉታል፡፡ የትራምፕ እንደገና መመረጥ ዕውን ከሆነ በኋላ፣ የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው በነደፈው ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በአጠቃላይ በአውሮፓ ደኅንነትና በየትኛውም ግጭት የአሜሪካን ተሳትፎ መቀነስ የሚል ይገኝበታል፡፡

ቀደም ብሎ የተጠቀሰው የ800 ማይል ነፃ የጦር ቀጣና እንዲሁም ዩክሬን ለሃያ ዓመታት የኔቶ አባልነት ውጥኗን ማሳረፍ የሚሉት እዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ትራምፕም ዩክሬንን ከቀጣይ የሩሲያ ጥቃት ለመከላከል በመሣሪያ ያግዛሉ እንጂ የአሜሪካን ጦር አያሰማሩም፡፡ ዩክሬን ውስጥ የአውሮፓውያን ጦር ሥምሪት ይኖር ዘንድ የገንዘብ ድጋፍ አያደርጉም፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ምሥራቅ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ቼኮዝላቫኪያና ሃንጋሪ የመሳሰሉ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፣ በሶቪዬት ኅብረትና በኔቶ ድንበሮች መካከል ሽብልቅ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ለመከላከያ ሚኒስትርነት በትራምፕ የታጩት ፒት ሄግሴት በኔቶ ተቀናቃኝነት አቋማቸው የሚታወቁ ሲሆኑ፣ የውጭ ጉዳይ ዕጩ ሚኒስትሩ ማርኮ ሮቢዮ ደግሞ ዩክሬን በየትኛውም ዋጋ ከሩሲያ ጋር የሰላም ስምምነት መፈረም እንደሚኖርባት አቋም የያዙ ናቸው፡፡

ሮበርት ዶቨር ያስቀመጡት ሁለተኛ ሁኔታ የአውሮፓ ድጋፍ ለዩክሬን ይሰኛል፡፡ የአውሮፓ መሪዎች፣ በተለይም የእንግሊዝና የፈረንሣይ መሪዎች ለዩክሬን ‹‹የማያወላውል ድጋፍ›› ቃል ገብተዋል፡፡ ሆኖም የእነዚህ አገሮች ድጋፍ ዘላቂነት ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ምክንያቱም አሜሪካ ለዩክሬን ከምታደርገው ድጋፍ ብሎም ለአውሮፓ ደኅንነት ከምታደርገው ድጎማ ልታፈገፍግ ትችላለች፡፡ ለበርካታ አሠርት ዓመታት በተለምዶ የአውሮፓ መከላከያ መዋቅርና ደኅንነት በአሜሪካ ድርጎ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያለ አሜሪካ ቀጣይ ዕርዳታና ተሳትፎ ኔቶ የአሁናዊ ጠንካራ አቋሙን ይዞ የመቀጠሉና የአውሮፓ አገሮችም ዩክሬንን በመደገፍ የሚያሳዩት የተባበረ አቋም ዘላቂነት አጠያያቂ ነው፡፡

የፕሮፌሰር ዶቨር ሦስተኛ መላምታዊ ሁኔታ ዘሌንስኪ ለትራምፕ የሚያቀርቡትን መውጫ መንገድን ይመለከታል፡፡ እንደ እኚህ ምሁር፣ ዘሌኒስኪ ለትራምፕ ሁለት ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ሁለቱም ሐሳቦች የትራምፕን ቀልብ ለመግዛት ያለሙ ናቸው ይላሉ፡፡

አንደኛው ሐሳብ ከጦርነቱ በኋላ አውሮፓ ውስጥ ካሉ የአሜሪካ የጦር ሥምሪቶች አንዳንዶች በዩክሬን ጦር በመተካት የአሜሪካውያንን ወጪ መቀነስ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የዩክሬንን አንዳንድ ሀብቶች ለአሜሪካና ለአጋሮቿ ክፍት ማድረግ የሚል ነው፡፡ የዩክሬን ሐሳቦች ከሩሲያ የገጠመችውን ጦርነት አሸናፊ ሆና መውጣት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አሁናዊ ሁነቶች ደግሞ ይህን አያመላክቱም ይላሉ ዶቨር፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ራሳቸውን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ከተዋል፡፡ የትራምፕ መጪው አስተዳደር ለዩክሬን የሚሰጡት ድጋፍ ገና ግልጽ ካለመሆኑም ባሻገር፣ በዩክሬናውያን ዘንድ ለዘሌኒስኪና ለጦራቸው ያለው ስሜት ወደ ውጥረት ማዘንበል ጀምሯል፡፡ ለዩክሬን የበሚደረግ አጠቃላይ ድጋፍን በተመለከተም በአውሮፓ መሰላቸት እየታየ ነው ይላሉ ምሁሩ፡፡

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ ዘሌኒስኪ አገራቸውን በድኅረ ጦርነት ወቅት በአውሮፓ ደኅንነት ዓይነተኛ ሚና የምትጫወት እንደምትሆን በትራምፕ ዕዝነ ልቦና ለመሳል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ይላሉ ተመራማሪው፡፡ ይህ ደግሞ አሜሪካ ለአውሮፓ መከላከያ የምታደርገውን አስተዋጽኦ መቀነስ ስለሚያስችላት፣ ጉዳዩ የትራምፕን ይሁንታ ያገኛል ከሚል የመነጨ ነው፡፡ ሆኖም የዩክሬን አስተዋጽኦ ዕውን ሊሆን የሚችለው ኔቶን ከተቀላቀለች ብቻ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ከአሁናዊ ሁነት የራቀ ነው፡፡

የፕሮፌሰሩ ቁጥር አራት ሁኔታ የሩሲያ ጦር ግስጋሴን ይመለከታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በምሥራቃዊ ዩክሬን በእጅጉ በመስፋፋት በለስ እየቀናት ነው፡፡ በቅርቡም የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ጠልቆ እንዲገሰግስ መንገድ የጠረገ ድል አግኝቷል፡፡ ምክንያቱም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋ ከፍተኛ ነው የሚባልላትን ብህለዳር ከተማ ተቆጣጥሯል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም ሞስኮ 11,000 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችንና 40,000 የራሷን ጦር አባላት በማሰማራት ዩክሬን በብራው ወቅት በከርስክ ግምባር ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች ወደኋላ የሚመልስ ሁኔታ ተጋርጦባታል ይላሉ፡፡ ዘ ኮንቨርሴሽን ለተባለ ድረ ገጽ በጻፉት ትንተናም፣ ሁኔታው በዩክሬን አጠቃላይ መከላከል ጥረት ላይ ከባድ ጫና የፈጠረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ትራምፕ በዚህ አቋማቸው ብቻ ይዘልቃሉ ተብሎም ማስረዳት እንደማይቻል ይጠቁማሉ፡፡ የትራምፕ የውጭ ፖሊሲ ‹‹የእከክልኝ ልከክልህ›› በመሆኑ ለአሜሪካ ትቅደም መፈክራቸው ይበጃል ብለው ካሰቡ ዩክሬንን እንዲሁም የአውሮፓ ኃይሎችን ፍላጎቶች የሚያረኩ ፖሊሲዎችንም ሊከተሉ ይችላሉ ይላሉ ፕሮፌሰር ዶቨር፡፡

ትራምፕ በአውሮፓ ያለውን የአሜሪካ ጦር ሥምሪት መቀነስ ይሻሉ፡፡ ይህንን ማድረጋቸውንና ለአካባቢው ሰላም ማስፈናቸውን ለዓለም ያውጃሉ፡፡ በዚህም ሁሉም አሸናፊ እንደሆነ ይቆጥራሉ፡፡