ተመስገን ተጋፋው

November 20, 2024

የወትሮው የግብይት እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘበት የመርካቶ ገበያ

በደረሰኝ ምክንያት ከሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ አድማ ያደረጉ የመርካቶ ነጋዴዎች፣ በፀጥታ አካላት የተነሳ ሱቃቸውን በከፊል ቢከፍቱም ሽያጭ ግን እያከናወኑ አልነበሩም፡፡

ሪፖርተር ሰኞና በማግሥቱ ማክሰኞ ዕለት በመርካቶ ባደረገው ቅኝት ሚሊተሪ ተራ፣ አዲስ አበባ የገበያ ማዕከል፣ ተወከል ሕንፃ፣ ዱባይ ተራ፣ ሲዳሞ ተራ የገበያ ማዕከል፣ አንዋር መስጊድ አካባቢና ሌሎች ሥፍራዎች የሚገኙ ነጋዴዎች ሱቃቸውን መዝጋታቸውን መመልከት ችሏል፡፡

ነገር ግን ማክሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከ5፡00 ሰዓት ጀምሮ በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት ነጋዴዎች ሱቃቸውን በከፊል ቢከፍቱም፣ ምንም ዓይነት ሽያጭ እያከናወኑ አልነበሩም፡፡

በርካታ የመርካቶ ነጋዴዎች ከአስመጪዎች ዕቃ ሲረከቡ ደረሰኝ እንደማያገኙ ለሪፖርተር ገልጸው፣ መንግሥት ከላይ ጥርት ያለ አሠራር ሳይዘረጋ ማንኛውም ነጋዴ ደረሰኝ ሳይቆርጥ ምንም ዓይነት ግብይት እንዳይፈጽም ማለቱ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡

ለአብነት አንድ ነጋዴ ከአመጪዎች የ100 ሺሕ ብር ዕቃ ቢገዛ ከአስመጪዎቹ የሚያገኘው ደረሰኝ ከአምስት ሺሕ ብር የበለጠ እንደማይሆን የጠቀሱት ነጋዴዎቹ፣ በዚህ ምክንያት ነጋዴው የሚሸጠውን ዕቃ ያለ ደረሰኝ ለሸማች ለመሸጥ እንደሚገደድ አክለው ገልጸዋል፡፡   

በቅርቡ ነጋዴዎች በደረሰኝ ግብይት እንዲፈጽሙ የወጣው አስገዳጅ መመርያ በነጋዴዎችና በመንግሥት መካከል አለመግባባትን እንዳስከተለ ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

በተለይ የትኛውም ነጋዴ ያለ ደረሰኝ ሲሸጥ ከተገኘ እስከ መቶ ሺሕ ብር እንዲቀጣ የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ መንግሥት ከጉምሩክ ጀምሮ እስከ ታች ያለውን አሠራር ወጥ ማድረግ አለበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ደረሰኝ ሳይቆርጡ የሚገበያዩ ነጋዴዎች አሉ የተባለው ነገር በግልጽ ቢታወቅም፣ ችግሩን ለመፍታት የተመደቡ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት የመጡት በጉቦ ለመደራደር እንጂ፣ ችግሩ በተባለው ልክ ሊፈታ እንዳልቻለ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በገቢዎች ቢሮ ሥር ተሰማርተው ቁጥጥር የሚያደርጉ ሠራተኞች የሚፈልጉትን ገንዘብ ከነጋዴው አምጣ በማለት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ፣ ነጋዴው የተጠየቀውን ካላመጣ ሱቁ እንደሚታሸግ በመግለጽ እንደሚያስፈራሩ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

በቀበሌ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቃቸው እንደሚወረስ በመሥጋት የከፈቱ ሲሆን፣ በአክሲዮን ማኅበራት በተገነቡ የገበያ ማዕከላት ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎች ደግሞ በማኅበራቱ ግፊት ሱቆቻቸውን እንደከፈቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ የተከፈቱት ሱቆች እንደ ወትሮው ግብይት እያደረጉ አለመሆኑን ሪፖርተር መታዘብ ችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ያለ ደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ ነጋዴዎች 20 ሺሕ ብር እንደሚቀጡ በቅርቡ በወጣው መመርያ ቅጣቱ 100 ሺሕ ብር መደረጉ ታውቋል፡፡

መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገውን የቅጣት መጠን ነጋዴው መክፈል እንደማይችል የጠቀሱት ነጋዴዎቹ፣ መርካቶ ትልቅ የገበያ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ያሉትን ችግሮች ከነጋዴው ጋር ተወያይቶ በመፍታት ዘርፉ ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አስመጪዎችና አምራቾች ላይ በቂ ሥራ ሳይሠራ ወደ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴው ላይ የበዛ ቁጥጥር ማድረግ የፈጠረው ጫና የንግድ ሒደቱን እያስተጓጎለው መሆኑንም ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡

ማክሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት በርካታ የቀን ሠራተኞች፣ ማለትም ጫኝና አውራጆች ሥራ ፈተው ነበር፡፡

በሌላ በኩል ከተማ ውስጥ ላሉ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ዕቃ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎች ሌላ ጊዜ በቀን አምስት ጊዜ እየተመላለሱ ዕቃ እንደሚጭኑ ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት ሱቆቹ ዝግ በመሆናቸውና ምንም ዓይነት ግብይት ስለሌለ አንድ ዙር እንኳን የጭነት ሥራ አለመሥታቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩም በዚሁ ከቀጠለ ችርቻሮ ንግዱ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ነጋዴዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ማክሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የግብይት ሥርዓቱን በዘላቂነት ለማስተካከል በጥናት ላይ ተመርኩዞ በተከናወነ ሥራ በርካታ ሕገወጥ የሆኑ አሠራሮች መኖራቸውን ተመልክተናል ብለዋል፡፡  

በመርካቶ ሕጋዊ ግብይት እንዲደረግና ለእያንዳንዱ ግብይት ነጋዴው ደረሰኝ እንዲቆርጥ በጥናት ላይ የተመሠረተ ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

መርካቶ ትልቅ የገበያ ማዕከል መሆኑን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ ለኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ቢሆንም፣ ቦታው የሕገወጥ መደበቂያ ሆኗል ብለዋል፡፡

መርካቶን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ለማስገባት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን፣ በጥናቱም አብዛኛው የሚመለከታቸው የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ደረሰኝ እንዲቆረጥና ግብር እንዲከፈል ለማድረግ በተደረገው ሒደት መጋዘኖችን በመዝጋት በምሽት ዕቃዎች ሲጫኑ እንደነበርም አስታውቋል፡፡

በመተማመን መሥራት አገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተናገሩት ከንቲባዋ፣ በቀጣይም ሕጋዊ ሥርዓትን በመዘርጋትና ለእያንዳንዱ ግብይት ደረሰኝ እንዲቆረጥ በማድረግ ግብር በአግባቡ የመሰብሰብና ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰውነት አየለ፣ ከዚህ በፊትም በመርካቶ በሕገወጥ ነጋዴዎችና በሕገወጥ ግብይት ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውሰው፣ ሰሞኑን የተጀመረው የቁጥጥር ዕርምጃ ለየት የሚያደርገው አዳዲስ ተቆጣጣሪዎች መሰማራታቸው ብቻ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በመርካቶ ገበያ ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተሰማሩ ተቆጣጣሪዎች ከነጋዴዎች ጋር በመላመድና ጉቦ በመቀበል ወቀሳ ይቀርብባቸው ስለነበር፣ ቀደም ሲል የነበሩትን የቁጥጥር ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ከዚህ ሥራ እንዲወጡ በማድረግ በአዲስ መተካታቸውን ማስረዳታቸው አይዘነጋም፡፡ አዲሶቹ ተቆጣጣሪዎች ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ምሩቃን መሆናቸውን፣ የተወሰነ ሥልጠና ወስደው እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረው ነበር፡፡