ኤልያስ ተገኝ

November 20, 2024

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሀና ተኸልቁ

በምሥረታ ላይ ካለ ኩባንያ የተገዙ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ኩባንያው ከተቋቋመ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል ለግብይት መቅረብ፣ ወይም በሌላ መንገድ መተላለፍ እንደይማችሉ በመመርያ ተወሰነ፡፡

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በተጨማሪም በምሥረታ ላይ ያለ የአክሲዮን ኩባንያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለሕዝብ ሽያጭ ከማቅረቡ በፊት፣ ሊሰበስብ ካቀደው ካፒታል ቢያንስ አሥር በመቶ የሚሆነውን በግል ሽያጭ አቅርቦ መሰብሰብ እንዳለበት  ባዘጋጀው አዲስ መመርያ ደንግጓል፡፡

በምሥረታ ላይ ያለ ኩባንያ ከተመሠረተ በኋላ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚቆይ የሕግ ማስከበር አማካሪ መሰየም እንዳለበት በመመርያው የተገለጸ ሲሆን፣ ከአማካሪው ጋር የሚኖር ውል በጽሑፍ ሆኖ በባለሥልጣኑ እንዲፅድቅና የዝግ አካውንቱ እንዲለቀቅ ከሚቀርብ ማመልከቻ ጋር መቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል።

በምሥረታ ላይ ያለ ኩባንያ የቀረበ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ በባለሥልጣኑ ከፀደቀ በኋላ ፅኑ ሆኖ የሚቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ እንደሆነ የሠፈረ ሲሆን፣ የአቅርቦት ጊዜው ክፍት ሆኖ የሚቆየው ከአንድ ዓመት በላይ ነው፡፡ አውጪው ነባሩ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ጊዜው ሳያልቅ ቢያንስ አንድ ወር ቀደም ብሎ፣ አዲስ የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ለባለሥልጣኑ ማቅረብና ማፀደቅ አለበት ተብሏል።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የአውጪውን የሥራ ዘርፍ፣ አቅርቦቱን፣ በአቅርቦቱ ለመሰብሰብ የታሰበውን መጠንና የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጭውን የሥራ ባህሪ መሠረት በማድረግ በምሥረታ ላይ ባለ ኩባንያ ይዞ ሊመጣ የሚገባውን የካፒታል መጠን ሊቀንስ እንደሚችል በመመርያው ተጠቅሷል፡፡

ሌላው በመመርያው የተገለጸው የጥቅል ምዝገባ ሲሆን፣ ይህ ማለት የሰነደ ሙዓለ ንዋይ አውጪው በባለሥልጣኑ በተፈቀደ የጊዜ ገደብ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን እንዲያቀርቡ የሚያስችል የምዝገባ መግለጫ መሆኑ ተገልጿል።

በጥቅል ምዝገባ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለማቅረብ ብቁ የሆነ ሕዝባዊ ኩባንያ አውጪ፣ በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ላይ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ያህል ተመዝግቦ የቆየ፣ በቋሚ መረጃ ይፋ የማድረግ ግዴታዎቹን የተወጣ፣ የጥቅል ምዝገባው ከመፅደቁ በፊት ባሉት 12 ወራት ውስጥ መክፈል ካልቻለው ዕዳ ጋር በተያያዘ የተቀመጡ ደንብና ሁኔታዎችን ያልጣሰና ከካፒታል ገበያ ጋር የተያያዙ ሕጎችን ያልጣሰ ከሚሉት መሥፈርቶች መካከል አንዱ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

በሌላ በኩል በጥቅል ምዝገባ የቀረቡ ወይም የሚሸጡት ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ድምር ዋጋ ከአምስት ቢሊዮን ብር ማነስ የለበትም የተባለ ሲሆን፣ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን በባለሥልጣኑ ለማስመዝገብ የሚፈልግ አውጪም በባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ግዴታዎች በሟሟላት ረገድ ጥሩ አቋም ላይ ያለ የግብይት አማካሪ መሾም አለበት፡፡

የግብይት አማካሪው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮቹ አቅርቦት ከአዋጁ፣ ከተዘጋጀው መመርያና ከሌሎች ባለሥልጣኑ የሚያወጣቸው መመርያዎች ድንጋጌዎች ጋር የማይቃረን መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አሳስቧል።

አስቀድሞ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ሳያገኝ ለሕዝብ ሽያጭ አቅርቦትን በተመለከተ ማንኛውም ሰው ማስታወቂያ ማውጣት እንደማይችል በመመርያው የተደነገገ ሲሆን፣ ማንኛውም ማስታወቂያ የደንበኛ ሳቢ መግለጫው እንደወጣ ወይም እንደሚወጣ ካልጠቀሰና ኢንቨስተሮች የመግለጫውን ቅጂ የት እንደሚያገኙ ወይም ሊያገኙ እንደሚችሉ ካላመላከተ በስተቀር፣ ለሕዝብ መውጣት ወይም እንዲወጣ መደረግ እንደሌለበት ተገልጿል።

ማንኛውም ማስታወቂያ ስለኩባንያው የሥራ አፈጻጸም ወይም እንቅስቃሴዎች አስፈላጊው ማብራሪያ ወይም ማስታወሻዎች ሳያካትት፣ ስለኩባንያው የተጋነነ ምሥል የሚሰጡ ገለጻዎችን ያካተተ ከሆነ ወይም የኩባንያውን የቀደመ አፈጻጸም በተሳሳተ መልኩ የሚሥል፣ የቀደሙ ትርፎች ወይም ገቢዎች ወደፊት እንደሚደገሙ የሚሥል ከሆነ አሳሳች ተደርጎ እንደሚቆጠር መመርያው አስታውቋል፡፡

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሀና ተኸልቁ ስለመመርያው በሰጡት ገለጻ እንደስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ለሕዝብ ሽያጭ ከመቅረባቸወ በፊት የደንበኛ ሳቢ መግለጫ መዘጋጀት ቢኖርበትም፣ ይህ ለኢንቨስተር የሚቀርበው መግለጫ ይዘት አንድ ኢንቬስተር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ውሳኔ ሊያስወስዱት የሚችሉትን መረጃዎች በበቂ ሁኔታ የማያካትት ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሚቀርቡት መረጃዎች እውነተኛ፣ የተሟሉና ግልጽ መሆናቸው የሚመረመርበት ምን ዓይነት ሒደት እንዳልነበረ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው የሰነደ ሙዓለ ንዋይን ለሕዝብ የማቅረብና የግብይት መመርያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዝብ ሽያጭ በሚቀርቡ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች አቅርቦት ላይ፣ እንዲሁም በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያም ሆነ ባልተማከለ የጠረጴዛ ዙሪያ ገበያ በሚደረጉ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይቶች ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።