ዜና የባንክ ሥራዎች ረቂቅ አዋጅ በአካል ጉዳተኞች ተቃውሞ ገጠመው

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: November 20, 2024

ለሕዝብ ውይይት የቀረበው የባንክ ሥራዎች ረቂቅ አዋጅ ለአካል ጉዳተኞች የሚቀርቡ የባንክ አገልግሎቶችን በተመለከተ ያሠፈረው አንቀጽ ተቃውሞ ገጠመው። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ባንክ ገዥና ሌሎች ከፍተኛ የባንኩ ኃላፊዎች በተገኙበት የሕዝብ ውይይት ወቅት ነው ይህ የተገለጸው። 

ከኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ገብሬ ተሾመ የተባሉ ተሳታፊ፣ ‹‹ረቂቅ አዋጁ የአካል ጉዳተኞችን መብት በሕግ ማረጋገጥ የደረሰበትን ደረጃ ወደኋላ የሚመልስ ነው፤›› ብለዋል።

አቶ ገብሬ ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት በቅድሚያ በረቂቁ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 1 አንድ ላይ፣ ‹‹ማንኛውም ባንክ ለአካል ጉዳተኛ ደንበኞች ምቹና ተደራሽ የባንክ አገልግሎት ሊያቀርብ ይችላል፤›› በሚል የሠፈረው ድንጋጌ እንደሆነ ገልጸዋል። 

በማስከተልም በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ የባንክ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መመርያ ሊያወጣ ይችላል፤›› በሚል የተቀመጠውን የማሻሻያ ክፍል ጠቅሰዋል። 

‹‹ይህ ማሻሻያ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተመለከተ ‹ይችላል› በሚል አገላለጽ በአማራጭ ያስቀመጠበት ምክንያት አልገባንም። ‹አለበት› በሚል አሁን በሥራ ላይ ባለው አዋጅ አንቀጽ 56 ላይ እንደተቀመጠው በአስገዳጅነት መደንገግ አለበት፤›› ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ምሁር ዓይነ ሥውራን ሴቶች ማኅበርን መወከላቸውን የገለጹት በቀለች ጥሩዬ (ዶ/ር) የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው፣ ‹‹ረቂቅ አዋጁ ምቹና ተደራሽ ከሚለው ባሻገር አካታች የሚል አገላለጽም ሊታከልበት ይገባል፤›› የሚል ሐሳብ አንስተዋል። 

በተጨማሪም የአዋጁ ማሻሻያ በጥቅል ከመጥቀስ ይልቅ፣ ‹‹ማነው አካል ጉዳተኛ? ምቹ የሚለው ምን ማለት ነው? እንዲሁም ተደራሽ የሚባለው ምን መሥፈርቶችን ሲያሟላ ነው? በሚለው ላይ ግልጽ ትርጓሜ ማቅረብ አለበት፤›› ብለዋል። 

በቀለች (ዶ/ር)፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ዓይነ ሥውራን ከባንክ ገንዘባቸውን ለማውጣት መከተል ያለባቸው የፊርማ አሠራር መብታችንን የሚጥስ ነው። የማኅበሬ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብሆንም ዓይነ ሥውር ስለሆንኩ ቼክ መፈረም አልችልም፤›› ሲሉ የገጠማቸውን ችግር አስረድተዋል። 

ዓይነ ሥውራን ከባንኮች ገንዘባቸውን ለማውጣት የሌላ ሰው መታወቂያ ግልባጭ (Copy) እና ፊርማ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ፊርማውን የሚፈርምላቸው የትዳር አጋራቸው ከሆነም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ ግልባጭ ለባንኩ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አክለዋል፡፡ 

‹‹ባንኮች ገንዘብ ስናስገባ ዝም ይሉና ስናወጣ ነው ከባድ መከራ ያለው። እዚህ አገር ሕጎች ሲወጡ አካል ጉዳተኞችም እንዳለን ታሳቢ አድርጉ ነው ጥያቄያችን፤›› ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ ረታ የአስተያየት ሰጪዎችን ሐሳብ ተጋርተዋል። 

‹‹ሕጉ አካል ጉዳተኞች ከየትኛውም ሰው እኩል ያለ ምንም መገለልም ሆነ ቅድመ ሁኔታ የባንክ አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ዕውቅና በመስጠት ይጀምር፤›› ሲሉ ጠይቀዋል። 

አቶ አበራ በቀለ የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው፣ አዋጁ የአካል ጉዳተኛ አገልግሎትን በተመለከተ ፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ገዳቢ ሕጎች በአዋጁ እንዲታዩ አሳስበዋል።

ለአብነት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1728 የተዋዋይ ወገኖች ፊርማ በተመለከተ የሠፈረው ድንጋጌ ታሳቢ እንደደረግ ጠይቀዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ የአካል ጉዳተኛ ዜጎችን መብት ወደኋላ ለመመለስ ታስቦ የሠራው ነገር እንደሌለ እንዲታወቅ፣ ይቻላል በሚል የሠፈረው አለበት በሚል አስገዳጅ ይሁን የሚለውን ሙሉ ለሙሉ እንቀበላለን፤›› ብለዋል። 

የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በበኩላቸው፣ የአካል ጉዳተኞችን የባንክ አገልግሎት መብቶች ለማረጋገጥ ረቂቅ መመርያ በሒደት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ዝርዝር አሠራሮችን በተመለከተ ያሉ ድንጋጌዎች ቴክኒካዊ ስለሆኑ በጥንቃቄ መታየት ስላለባቸው መመርያው መዘግየቱን አስረድተዋል።