የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ማብራሪያ ሲሰጡ
ዜና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ስላለ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት የፓርቲ አባል ቢሆኑም…
ቀን: November 20, 2024
- የማኅበራዊ ሚዲያ ሕግ እንዲወጣ ጥያቄ ቀርቧል
ተሻሽሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን የለባቸውም የሚለው አንቀጽ በመሰረዙ፣ በአገሪቱ መድበለ ፓርቲ እስካለ ድረስ የቦርዱ አባላቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኑም አልሆኑም የሚያመጣው ለውጥ የለም ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ምላሽ ሰጡ፡፡
ኃላፊዎቹ ምላሽ የሰጡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ አባላት የመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባላት ባለው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ወይም ተቀጣሪ ያልሆኑ ተብሎ የተደነገገ ቢሆንም፣ በተሻሻለው አዋጅ ይህ ድንጋጌ መሰረዙንና የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል የሚለው ተቀይሮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል መባሉ ለምን አስፈለገ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ክፍል ባለሙያዋ ወ/ሪት ሃይማኖት ደበበ መገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው መደንገጉን በማውሳት፣ ይህ የማሻሻያ ረቂቅ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ምን ያህል ግምገማ ተደርጓል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ በነባሩ አዋጅ የቦርድ አባላት ዕጩዎች ምልመላ ለሕዝብ ክፍት ሊደረግ አንደሚገባው፣ የአመራረጥ ሒደቱ በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ተደራሽ መሆን እንዳለበትና ፍትሐዊ ውክልና ሊኖር እንደሚገባ ቢደነገግም ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ይህ ድንጋጌ መሻሩ መሠረታዊ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሚቃረንና የሕግ አወጣጥ መመርያውን የሚጋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወ/ሪት ሃይማኖት አክለውም በነባሩ አዋጅ የቦርድ አባላት ከሲቪል ማኅበረሰብ ሁለት፣ ለመገናኛ ብዙኃን ጠቀሜታ ያላቸው ሌሎች አካላትና የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚለው ድንጋጌ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርበትና አግባብነት ካላቸው የሚል አሻሚና ለትርጉም ተጋላጭ የሆነ ደንጋጌ የተካተተበት ምክንያት ምን ታስቦ ነው ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ድርሻ ከአዋጁ ለምን እንዲወጣ ተደረገ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍን አጠቃቀም የሚገራ ሕግ በዚህ አዋጅ እንዲካተት የጠየቁ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በአሁኑ ወቅት የአገርን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ የሚዲያ ዘርፉን መቆጣጠር የሚያስችል ሕግ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ኃላፊ ወ/ሪት ቆንጅት ታምራት አዋጁ ከመነሻው ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለሕግ አውጪው አካል በመሆኑ፣ በማሻሻያ የቀረቡት ነጥቦች ገለልተኛነትን የሚጥሱ አይደሉም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መታየት ያለበት ተጠሪነቱ ለማን ነው የሚለው ነው ያሉት ወ/ሪት ቆንጅት፣ የአፍሪካ የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካል በአብዛኛው ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ወይም በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ስለመሆኑ፣ በምዕራባውያን አገሮች ደግሞ ተጠሪነት ለፓርላማ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት የቦርድ አባላት ከማንኛውም ፓርቲ የተወጣጡ ስለሚሆኑ ዋናው መወሰድ ያለበት ነገር የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላለው የሕግ አውጭ አካል ተጠሪ ስለሚሆን፣ በዚህ አሠራር ስለሚኖር ስለሆነ የቦርድ አባላቱ የፖለቲከ ፓርቲ ሆኑም አልሆኑም የሚያመጣው ለውጥ ስለሌለ ይህ ከግምት ውስጥ እንዲገባ ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በሰጡት ምላሽ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የዕለት ተዕለት ተግባራት ለቦርድ የተሰጡ በመሆናቸው፣ ባለሥልጣኑ መቆጣጠር የማይችል ተቋም እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቅሬታ ሲቀርብ ‹‹ለበላይ አካል አሳውቄያለሁ እያልን ስንጠይቅ ቆይተናል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አሿሿምን በተመለከተ ሲያብራሩ በሥራ ላይ ያለው በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል እንደሚል፣ አሁን በተሻሻለው ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል እንደሚል ገልጸው፣ መንግሥት ሲያቀርብ ምንጊዜም በዚህ ዓይነት መንገድ ስለሆነ የአገላለጽ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ አዲስ ነገር የለውም ብለዋል፡፡
አቶ መሐመድ ቦርዱን የማመንና ባለሥልጣኑን ያለማመን አዝማሚያ መኖሩን ጠቅሰው፣ በዚህ መንገድ ባለሥልጣኑ ካልታመነ ማፍረስና ቦርዱ የመፈጸም አቅም እንዲኖረው ማድረግ ቀላሉ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ይፈጽም ከተባለ በተቀመጠለት ሕግና ሥርዓት እንዲፈጽም ሥልጣን ይሰጠው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
‹‹በአዋጅ ያቋቋምነውን ባለሥልጣን መጠርጠር ከየት እንደመጣ አልገባኝም፤›› ያሉት አቶ መሐመድ፣ ‹‹ሁለተኛው ጥርጣሬ፣ ፈተናና የገለልተኝነት ጉዳይ የሚነሳበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ኃላፊን መልምሎ ለፓርላማ ስላቀረበ ገለልተኛ አይሆንም ካልን፣ የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እኮ ለፓርላማው አቅርቦ የሚያሾመው መንግሥት ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥትን እንደ ውጭ አካል ማየት ተገቢ አይደለም፤›› ያሉት አቶ መሐመድ፣ መንግሥት ሕዝብ በጋራ ወጥቶ የመረጠው አካል መሆኑ መረሳት የለበትም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው የመሰየምና የመሾም መብት እንዳለውም አክለው ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የቦርድ አባል መሆን የሚዲያ ዘርፉን ይጎዳል የሚለውን ዕሳቤ ሲያስረዱ፣ በአሜሪካ የሚገኘው የፌዴራል ኮሙዩኒኬሽን ኮሚሽን ውስጥ ያሉትን የሰባት ኮሚሽነሮች ሹመት የሚያፀድቀው ፕሬዚዳንቱ መሆኑን፣ በአዋጅ የቦርድ አባላት አመራረጥ ከአንድ ፓርቲ ከሦስት ሰዎች በላይ አይሆንም እንጂ የፓርቲ አባል አይሆንም እንደማይባል፣ የፓርቲ አባል ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ቢታወቅ እንዲህ አይሆንም ነበር ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የፓርቲ አባልነት ተፅዕኖ ይፈጥራል ቢባል ኖሮ ሚዲያውንም፣ ቴሌኮምንም፣ ፖስታንም ሁሉንም የሚቆጣጠረው አካል ሲሾም የፓርቲ አባልነት ይገደብ እንደነበር አክለዋል፡፡
‹‹በሥርዓቱ ነው ማመን ያለብን እንጂ ሲቪል ማኅበረሰብ ሲሆን ይታመናል፣ የፓርቲ አባል ሲሆን አይታመንም የሚለው አያስኬድም፡፡ የሚገባው የቄሳርን ለቄሳር መስጠት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የባለሥልጣኑ የሕግ ክፍል ኃላፊ ወ/ሪት ቆንጅት ማኅበራዊ ሚዲያን የሚገዛ ሕግ መውጣት በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ በዚህ የማሻሻያ ረቂቅ ማኅበራዊ ሚዲያን የሚቆጣጠር ሕግ ማካተት የማኅበራዊ ሚዲያን የገዘፈ ጉዳይ ማሳነስ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ራሱን የቻለ ሕግ መውጣት እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በበኩላቸው ማኅበራዊ ሚዲያን የተመለከተ ሕግ ቀጣዩ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡