ሰማንያ በመቶ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ውሳኔ በዛሬው ዕለት ይፋ ይደረጋል

ዜና የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ተግባር በይፋ ተጀመረ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: November 20, 2024

የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተንና (ዲሞብላይዝ የማድረግና) ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ የመቀላቀል የመጀመሪያ ዙር ትግበራ በዛሬው ዕለት በይፋ እንደሚጀመር ተገለጸ።

የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ የመቀላቀል ተግባር የመጀመሪያው ዙር በዛሬው ዕለት በይፋ እንደሚጀምርና ይህንንም የተመለከተ መግለጫ በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙኃን እንደሚሰጥ፣ ተግባሩን ለመፈጸም ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል።

ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞብላይዝ ለማድረግና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀል የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለሚያከናውነው ተግባርም የፌዴራል መንግሥት አንድ ቢሊዮን ብር በጀት እንደመደበለት ታውቋል። 

የፌዴራል መንግሥት ለ2017 በጀት ዓመት ለኮሚሽኑ ከመደበው በጀት በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአውሮፓና የእስያ አገሮች እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የተያዘውን ዕቅድ ለመደገፍ የበጀት ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል። 

የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይል (በሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው) በሠራዊቱ ውስጥ መቀጠል የለባቸውም ብሎ ያመነባቸው 80 በመቶ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ ፈትተው የቀድሞ ተዋጊዎች እንዲበተኑ ከተደረገ በኋላ የተሃድሶ ሥልጠና የሚወስዱ ሲሆን፣ ይህንን ካለፉ በኋላ ዲጂታል መታወቂያ ወስደው ወደ ማኅበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ተብሏል። ወደ ማኅበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅትም የመቋቋሚያ ክፍያ የሚያገኙ ሲሆን፣ ይህንንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አሠራር በጋራ እንደሚፈጽሙ ታውቋል። 

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሦስትዮሽ መግባቢያ ስምምነት ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ተፈራርሟል። 

ይህ የመግባቢያ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የተገኙት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፣ የመጀመሪያ ዙር ትግበራ በትግራይ ክልል ከሚገኙ የቀድሞ ተዋጊዎች መካከል 75 ሺሕ የሚሆኑትን በመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ በመቀላቀል እንደሚጀመር ተናግረው ነበር።

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀል በፕራቶሪያው የሰላም ስምምነት የተፈራረሙ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ እዚህ ፕሮግራም ማስገባት ትክክል አይደለም የሚል ቅሬታ በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን በኩል እየተሰነዘረ ነው።

የፖለቲካ ልሂቃኑ ቅሬታ፣ የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ወደ ቀደመ ይዞታው ባልተመለሰበትና የውጭ ኃይሎች ከክልሉ ባልወጡበት ሁኔታ የክልሉን ተዋጊዎች ትጥቅ በማስፈታት እንዲበተኑ ማድረግ ትክክል አይደለም የሚል ነው።

ይኸው ቅሬታ ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ የትግራይ ክልል የጊዜያዊ አስተዳደርን ሕጋዊ መሠረትና ኃላፊነት የተመለከተ ውይይት በተካሄደበት መድረክ ላይም ተነስቶ ነበር። 

በመድረኩ የተገኙት የቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምና በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የዴሞክራታይዜሽንና መልካም አስተዳደር ካቢኔ ኃላፊ ሌተና ጄነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የመበተንና ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል በተያዘው ዕቅድና ከክልሉ ልሂቃን በተነሳው ቅሬታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። 

ሌተና ጄነራል ፃድቃን በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፣ የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች ወይም በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሠራዊት በመባል ከሚታወቁት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት ትጥቅ ፈትተው እንዲበተኑና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይል መወሰኑን ተናግረዋል።

የክልሉ የፀጥታ ኃይል (በጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመራው) በሠራዊቱ ውስጥ መቀጠል የለባቸውም ብሎ ያመነባቸውን 80 በመቶ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች፣ ትጥቅ ፈትተው እንዲበተኑና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደወሰነ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገልጸዋል።

አክለውም የፀጥታ ኃይሉ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከዕድሜ፣ ከፆታና ከአካል ጉዳት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የክልሉን የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ፈተው እንዲበተኑና ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ ላይ በተደጋጋሚ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል ላይ፣ ‹‹የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ባልተመለሰበትና በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባሉበት ሁኔታ ትጥቅ ማስፈታት ለምን አስፈለገ? ትጥቅ ማስፈታት የትግራይን የመደራደር ከቅም ያዳክማል›› የሚሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ መነሳታቸውን ያስታወሱት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን፣ ‹‹ይህ አካሄድ ራስን የመከላከል አቅምን ቢጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም፤›› ብለዋል።

አክለውም ፣ ‹‹የትግራይ ደኅንነት ዋስትና በሠራዊት አቅም ብቻ የሚለካ ሳይሆን በፖለቲካዊ አንድነት የሚመዘን ነው›› ብለዋል።

የትግራይን የመደራደር አቅም ለማጠናከር ፖለቲካዊ አቅምና አንድነት ላይ መሥራት እንጂ ከአንድ አካባቢ ብቻ የሚመጣ ሐሳብና መመርያን መቀበል መፍትሔ እንደማይሆን፣ ከዚህ ይልቅ በትግራይ የተለያዩ አመለካከቶች የሚስተናገዱበትን ምኅዳር ለመፈጠር መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመላ አገሪቱ ትጥቅ በመፍታት ወደ ማኅበረሰቡ ይቀላቀላሉ ተብለው የሚጠበቁ 375 ሺሕ የቀድሞ ተዋጊዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 270 ሺሕ የሚሆኑት በትግራይ ክልል እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።