ወደ 126 ሚሊዮን ደርሷል ከሚባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው አብላጫው ቁጥር ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች የሆነ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል መሆኑ ይታወቃል
November 20, 2024
ለሥራ አጥ ወጣቶች ሥልጠና የመስጠትና መቋቋሚያ ድጋፍ የማድረግ ሥራ የሚያከናውን ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ፣ ሥልጠና እየሰጣቸው ካሉ ወጣቶች መካከል ሦስቱ ከሰሞኑ በድንገት ጠፍተው እንደ ነበር ይናገራል፡፡ ከቀናት ፍለጋ በኋላ ራሳቸው የጠፉት ልጆች በሰው ስልክ ደውለው መታፈሳቸውን እንደነገሩትና የሚገኙበትን ቦታ ገልጸው እንዲያስፈታቸው እንደጠየቁት ይገልጻል፡፡
በወረዳ በኩል ለወጣቶቹ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የሚገልጽ ደብዳቤ በማጻፍ ዋስ ሆኖና ኃላፊነት ወስዶ አሠልጥኖ ወደ ሥራ እንደሚያሰማራቸው የሚዘረዝር ወረቀት በማዘጋጀት፣ ልጆቹን ለማስፈታት ጥረት ማድረጉንም ያስረዳል፡፡ ‹‹እነዚያ ወጣቶች በፖሊሶች ትብብር ስልክ ባይደውሉልኝ ኖሮ ያሉበትንም ቦታ ሳላውቅ እቀር ነበር፤›› የሚለው ግለሰቡ፣ በስተመጨረሻ ቃሊቲ ማረሚያ ቤትን አልፎ ከሚገኝ ቦታ በቆርቆሮ ከተገነባ ማቆያ ሄዶ እንዳገኛቸው ይናገራል፡፡
ወጣቶቹ መንገድ ላይ ሲሄዱ በድንገት በፖሊሶች ተይዘው ወደ እዚያ ቦታ እንደተወሰዱ እንደነገሩት ግለሰቡ ገልጿል፡፡ ከመላው አዲስ አበባ ልክ እንደእነሱ በድንገት ከታፈሱ ሰዎች ጋር በቆርቆሮ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው እንዲቀመጡ መደረጉን እንደገለጹለትም ጠቁሟል፡፡ ቢጮሁም ሆነ ቢንጫጩ የሚሰማቸው እንዳልነበር፣ በቀን ጥቂት ዳቦ እየተሰጣቸው ለመቆየት መገደዳቸውንና ለምን ተይዘው ወደ እዚያ ቦታ እንደተወሰዱ የሚነግራቸው አጥተው በጭንቀት መሰንበታቸውን እንደነገሩትም ይገልጻል፡፡
የወረዳ ደብዳቤ አሳይቶ ለወጣቶቹ ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ በብዙ ጥረት አሳምኖ ታፍሰው ከሰነበቱበት የቃሊቲው ማቆያ እንዳስወጣቸው ግለሰቡ ይናገራል፡፡ በዚያ ማቆያ ግቢ ብዙ ቤቶች እንደተመለከተና በእነዚያ ቤቶችም ከአዲስ አበባ ከተማ ከየጎዳናው የታፈሱ በረንዳ አዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎችን ጨምሮ በድንገት የፀጥታ ኃይሎች እጅ ላይ የወደቁ ሰዎች ተሰብስበው እንደተቀመጡባቸው መታዘቡንም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ሰዎች ባላሰቡበትና ባልጠበቁት ሁኔታ ከመንገድ ላይ ተይዘው እንደ ወንጀለኛ በአንድ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ የሚታጎሩ ከሆነ በይፋ አፈሳ እየተካሄደ መሆኑን አመልካች ነው፤›› ሲልም ያክላል፡፡
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል አፈሳ በሰፊው እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል፡፡ መንግሥት ወጣቶችን እያፈሰ በግዳጅ ወደ ወታደራዊ ማሠልጠኛዎች እንደሚያስገባ በሰፊው ሲነገር ሰንብቷል፡፡ መንግሥት አፈሳውን ያጠናከረው ደግሞ በአገሪቱ በየቦታው በቀጠለው ጦርነት የሚያሠልፈው ሠራዊት ፍለጋ መሆኑን ነው በሰፊው ሲነገር የተደመጠው፡፡
በቅርቡ ስለአፈሳና ከአፈሳ ጉዳይ ጋር የተገናኙ በርካታ መረጃዎች እየተሰሙ ነው፡፡ የታፈሱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋገጥን የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው ስለመታፈሳቸው የሚናገሩ ሰዎች ብቅ ብቅ ሲሉም እየታየ ነው፡፡
ማንነቱና የግል ሁኔታው በሚስጥር እንዲያዝ የጠየቀ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት በቅርቡ ያለ ምክንያት ለሦስት ወራት ታስሮ መውጣቱን ይናገራል፡፡ መቂ አካባቢ መያዙን የሚናገረው ወጣቱ የራስ ፀጉሩ ‹‹ድሬድ›› የሚባለው አሠራር ያለው መሆኑን ያዩት የፀጥታ ኃይሎች፣ ‹‹አንተማ ደንበኛ የኦነግ ሸኔ አባል ነህ›› ብለው ወደ እስር ቤት እንዳስገቡት ይገልጻል፡፡ በብዙ ጥረት ከቤተሰብና ከዘመድ አዝማድ የተገኘ 300 ሺሕ ብር ለፀጥታ ኃይሎች ከፍሎ ከእስር መለቀቁን የተናገረው ወጣቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪነቱን የሚያመለክት መታወቂያ አሳይቶም ያመነው አካል አለመኖሩን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
በሰሜን ሸዋ ሸኖ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ለአካለ መጠን የደረሰ ወጣት ልጅ ያለው ቤተሰብ ልጅህን አምጣ እየተባለ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የአካባቢው ሚሊሻዎች ጭምር ልጆቻቸውን ካላመጡ ራሳቸው ወደ ጦርነት እንደሚላኩ ተነግሯቸዋል ይላሉ፡፡
አዳማ አካባቢ የፋኖ ደጋፊ ተብለው የታፈሱ ወጣቶች መኖራቸውን አንዳንድ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የኦነግ ሸኔ አባልና ደጋፊ ተብሎ ብቻ ሳይሆን፣ የፋኖ ደጋፊና የፋኖ አባል እየተባለ ባልታሰበ ቦታና ሁኔታ የተያዘ ወጣት በርካታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን፣ ከኮሪደር ልማት ጋር በተገናኘ ጭምር የታፈሱ ሰዎች መኖራቸው ሲነገር ነው የሰነበተው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በፓርቲ ደረጃ ግምገማ በማድረግ የደረሱበት ግኝት ካለ የተጠየቁት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጀቤሳ ገቢሳ፣ ፓርቲያቸው በጉዳዩ ላይ የራሱን ጥናት እያደረገ በመሆኑ የተደራጀ መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ መግለጫ እንደሚሰጥ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም ሁኔታውን በግል መስማታቸውን የጠቀሱት አቶ ጀቤሳ ቤተሰባቸው የታሰረባቸው አንዳንድ ሰዎችን ማናገራቸውን ተናግረዋል፡፡ አናገርኳቸው ካሏቸው ሰዎች ውስጥ ደግሞ የታላቁ ሩጫ መርሐ ግብር እስኪጠናቀቅ ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸው እንደተነገራቸው አንዳንዶቹ እንደገለጹላቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ፍርድ ቤት መሄድም ሆነ ዋስትና መጠየቅ አያስፈልግም፣ እኛው ራሳችን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንለቃቸዋለን፤›› ተብሎ በፀጥታ ኃይሎች ምላሽ እንደተሰጣቸው እንደነገሯቸውም አክለዋል፡፡
ስለዚሁ ስለአፈሳ ጉዳይ ፓርቲያቸው ተከታትሎ ከሆነ የተጠየቁት ሌላኛው ፖለቲከኛ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም በበኩላቸው፣ የአፈሳውንም ሆነ የኮሪደር ልማቱንም ተፅዕኖ ፓርቲያቸው ማጥናቱን ገልጸዋል፡፡ ፓርቲው በሁለቱም ጉዳይ ላይ የደረሰበትን ድምዳሜ በአጭር ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡
‹‹ስለጉዳዩ መረጃዎች አሰባስበናል፡፡ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ተነጋግረን የደረስንበትን ውጤት በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ችግሩ በግምገማችን እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ በተራዘመው ጦርነት ምክንያት ወጣቶች እየታፈሱ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ከቤት መውጣት እስኪፈሩ ድረስ ወጣቶች እየታፈሱ በማይፈልጉት ጦርነት ውስጥ እንዲማገዱ እየተደረገ መሆኑን ነው ቤተሰቦቻቸው የሚናገሩት፡፡ ብዙ ወጣቶች እየታፈሱ ለማስፈታት ብዙ ገንዘብ እንደሚጠየቅም ደርሰንበታል፡፡ ጦርነቱ የእርስ በእርስ ነው፡፡ መቆም ያለበትም በንግግርና በሰላም ብቻ ነው፡፡ ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ወደፊትም ከዚህ በላይ ዋጋ እንዳያስከፍለን ሥጋት አለን፤›› በማለት የፓርቲው በግምገማ አሳሳቢ ውጤቶችን ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡
የኦፌኮው ታዋቂ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ፣ ወጣቶች በተገኙበት እየታፈሱ ወደ ውትድርና እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግሯል፡፡
‹‹የእርስ በርስ ጦርነቱ ተባብሶ በመቀጠሉ የተነሳ መንግሥት ወጣቶችን እያፈሰ በግዳጅ ውትድርና ውስጥ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ የደሃ ልጆችን በተለይም ከትውልድ ቀዬአቸው ርቀው በቀን ሥራ ላይ ተሰማርተው ኑሮን የሚገፉ ወጣቶችን በማፈስ ነበር አፈሳው የተጀመረው፡፡ ሆኖም በሒደት የደህና ቤተሰብ ልጆች የሚባሉ ወጣቶችም ሲታፈሱ እየታየ ነው፤›› በማለት ጃዋር ከትቧል፡፡
ጃዋር ከዚህ በተጨማሪም በታጣቂ ቡድኖች እየታገቱ ማስለቀቂያ ገንዘብ ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍሉ ስለሚጠየቁ ሰዎችም ጽፏል፡፡ በሌላ በኩል ይህ የዕገታ ልምምድ ወደ ፀጥታ ኃይሎች መንደርም መግባቱን የገለጸ ሲሆን፣ ልጆቻቸው ወይ ዘመዶቻቸው የታሰሩባቸው ሰዎች እስከ 500 ሺሕ ብር ማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠየቁ ጠቁሟል፡፡ ሰዎች የታሰሩባቸውን ቤተሰቦች ለማስለቀቅ ገንዘብ ስለሚቸግራቸውም ዕድሮቻቸውንና ማኅበሮቻቸውን ጭምር ገንዘብ እስከማስቸገር ድረስ ሄደዋል ሲል ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ስለጦርነት ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ለረዥም ጊዜ እየተዋጋ የሚቀጥልበት በቂ የሰውም ሆነ ቁሳዊ ሀብት ያለው ስለመሆኑ ተናግረው ነበር፡፡ እሳቸው ወደ ሥልጠና ከመጡ በኋላ በተሻሻለው የመከላከያ ሚኒስቴር አዋጅ የሰው ሀብት ምልመላን በሚመለከት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የብሔራዊ ውትድርና አገልገሎት መስጠትን አካቶ መቅረቡ ብዙ ሲያወያይ ቆይቷል፡፡
በደርግ መንግሥት ዘመን የብሔራዊ ውትድርና ምልመላ በግዳጅ የሚካሄድ እንደነበር በማስታወስ፣ ነገር ግን አሁን በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ እንዲካሄድ በአዋጅ መቅረቡ መከላከያውን ከማጠናከር ባለፈ ትውልዱ በሥነ ምግባር ተኮትኩቶ እንዲቀርፅ የሚያደርግ ሐሳብ ነው በሚል ሲደነቅ ቆይቷል፡፡
በደርግ ዘመን የመንግሥት ክፋት መገለጫ ሆኖ ሲቀርብ የነበረው ደርግ ከወደቀ በኋላም ቢሆን ለረዥም ዘመን ኢሕአዴግ ደርግን ለማጥላላት ሲጠቀምበት የቆየው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጉዳይ፣ በዓብይ (ዶ/ር) የሥልጣን ዘመን ግን የሚጠቅም ሆኖ እስከ መታየት ደርሶ ነበር፡፡
ያም ቢሆን ግን ከሰሞኑ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ተከሰተ የተባለው የአፈሳ ዘመቻ የደርጉ ዘመን የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ተመልሶ መጣ ወይ የሚል ጥያቄ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እንዲነሳ ሲጋብዝ ታይቷል፡፡
በዚህ ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት፣ የአዲስ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በይፋ የሰጡት መግለጫ ባለመኖሩ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡