
ከ 5 ሰአት በፊት
በሱዳን 500 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ያስጠለለው እና በረሃብ የተጠቃው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከወራት በኋላ የመጀመሪያውን እርዳታ አግኝቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጭነት መኪናዎች በሱዳን ለ18 ወራት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ቀያቸውን ለቅቀው የተጠለሉበት ዛምዛም ስደተኞች ካምፕ አርብ ዕለት ደረሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) በአቅራቢያው በምትገኘው የዳርፉር ከተማ ኤል ፋሸር በተካሄደው ከባድ ጦርነት እንዲሁም ዝናባማ ወቅት ተከትሎ “ለመሻገር ፈታኝ በሆኑ” መንገዶች የተነሳ የምግብ አቅርቦቱ ለወራት ተቋርጦ ቆይቷል ብሏል።
በሱዳን ጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ባለው የሥልጣን ይገባኛል ሽኩቻ የተነሳ በዓለም ትልቁ የሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል።
ይህ የሱዳን ጦርነት10 ሚሊዮን ሰዎች ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ሲያደርግ ማህበረሰቡን ለረሃብ አጋልጧል።
በዛምዛም የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አል- ፋሸርን ከአገሪቱ መከላከያ ኃይል ለማስለቀቅ ያደረጉትን ከባድ ውጊያ ተከትሎ፣ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ተብሏል።
አል-ፋሸር በምዕራብ ዳርፉር ግዛት በአገሪቱ ወታደር ቁጥጥር ስር ያለች ብቸኛ ከተማ ነች።
በነሐሴ ወር፣ገለልተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች ጦርነቱ ዛምዛምን ወደ ረሃብ እንደገፋ ተናግረው ነበር።
በረሃብ የተጠቃን አካባቢ ለመመደብ የተቀመጡት መስፈርቶች ቢያንስ 20% የሚሆኑ አባወራዎች ለከፋ የምግብ እጦት የተጋለጡ መሆናቸውን፣30% ሕጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዱ እና ከ10 ሺህ ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ሰዎች በየቀኑ በረሃብ ወይም በምግብ እጦት አልያም በበሽታ ይሞታሉ ይላል።
ወደ ዛምዛም የምግብ እርዳታ ጭነው የተንቀሳቀሱ መኪኖች የዓለም የምግብ ድርጅት “ለችግር በከፍተኛ የተጋለጡ እና ከሌላው ተነጥለው ግጭት ያለባቸው አካባቢዎችን ” ለመድረስ የሚያደርገው ጥረት አካል ነው ሲል ገልጿል።
በአጠቃላይ ከ700 በላይ የጭነት መኪኖች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ከአንድ ወር በላይ ለመመገብ የሚያስችል በቂ እርዳታ ይዘው መላካቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የተወሰኑ የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ደቡብ ኮርዶፋን ግዛት እያመሩ መሆኑም ታውቋል።
- የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን እና የጁባላንድ ግዛትን ውዝግብ ውስጥ ያስገባቸው ምንድነው?22 ህዳር 2024
- የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በመንግሥት ዕገዳ እንደተጣለበት አስታወቀ22 ህዳር 2024
- ማንቸስተር ሲቲ ከቶተንሃም፣ ኢፕስዊች ከማንቸስተር ዩናይትድ…የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት22 ህዳር 2024
“እነዚህ መኪኖች ከእርዳታ እህል በላይ ነው የጫኑት፤ በግጭት እና በረሃብ ምክንያት ለተጎዱ ሰዎች የሕይወት አድን ነው የያዙት፤
“ለጭነት መኪናዎቻችን አስተማማኝ የሆነ መተላለፍያ መኖሩን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤ እናም ለአደጋ የተጋለጡ ቤተሰቦችን ለመድረስ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንፈልጋለን” ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ላውረንት ቡኬራ ተናግረዋል።
ሁለቱም ተፋላሚዎቹ ወገኖች ዕርዳታን በማገድ እና በመዝረፍ ቢከሰሱም፣ ሁለቱም ክሱን ውድቅ ያደርጉታል።
አርብ እለት ዛምዛም መጠለያ ጣብያ የደረሱ የእርዳታ መኪኖች፣ ጥቅምት 30 2017 ዓ.ም. ወደ ዳርፉር እርዳታ ለማድረስ ቁልፍ ከሆነችው የቻድ የድንበር ከተማ፣ አድሬ መነሳታቸው ታውቋል።
ይህ መስመር በየካቲት ወር ከአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል በተሰጠ ትእዛዝ ተዘግቶ በነሐሴ ወር ለሦስት ወራት ብቻ ተከፍቷል።
እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የመንግሥት አካላት አርኤስኤፍ የጦር መሳሪያ ለማጓጓዝ ይጠቀምበታል በሚል የመስመሩን መከፈት ተቃውመዋል ሲል ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት መንግሥት ለተጨማሪ ሦስት ወራት መስመሩ ክፍት እንዲሆን ተስማምቷል።
ሁለተኛው የዓለም ምግብ እርዳታን የጫኑ መኪኖች ከአገሪቱ መከላከያ ኃይል ጠንካራ ይዞታ እና የሱዳን ብቸኛ ወደብ፣ ፖርት ሱዳን፣ ወደ ዛምዛምፕ መጠለያ ጣቢያ ከ10 ቀናት በፊት ማምራት ጀምረዋል።