
ከ 5 ሰአት በፊት
ሩሲያ የዩክሬይኗ ዲኒፕሮ ከተማ ላይ አዲስ የባለስቲክ ሚሳኤል ካስወነጨፈች ከአንድ ቀን በኋላ፣ ፑቲን አገራቸው “ለመጠቀም ዝግጁ የሆኑ” አዳዲስ ሚሳኤሎች ክምችት እንዳላት ተናግረዋል ።
ፑቲን በድንገት በቴሌቪዥን ቀርበው የኦሬሽኒክ ሚሳይል በጸረ ሚሳኤል ሊጠለፍ እንደማይችል እና “የጦርነት ሁኔታዎችን” ጨምሮ ተጨማሪ ሙከራዎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ዩክሬን የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ሚሳኤሎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩሲያ ካስወነጨፈች በኋላ ሩሲያ ኦሬሽኒክን መጠቀሟ ጦርነቱ አንዲባባስ አድርጓል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ፑቲን “የድርጊታቸው ትክክለኛ መዘዝ እንዲሰማቸው” የዓለም መሪዎች “ከበድ ያለ ምላሽ” እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
አክለውም ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ዘመን አፈራሽ የአየር መከላከያ ሥርዓትን እንዲሰጧቸው መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
ኢንተርፋክስ-ዩክሬን የዜና ወኪል እንደዘገበው ኪየቭ አሜሪካ ሰራሹን ዘመናዊ የአየር መከላከያ (THAAD) ለማግኘት ወይም ያላትን ፀረ-ባለስቲክ ሚሳኤል መከላከያ ለማሻሻል ጠይቃለች።
አርብ ዕለት ፑቲን ለመገናኛ ብዙኃን የኦሬሽኒክ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምጽ ፍጥነት በአስር እጥፍ እንደሚበርሩ ገልጸው፣ በስፋት እንዲመረቱ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ብለው አገራቸው ሚሳኤሉን የተጠቀመችው ዩክሬን ስቶርም ሻዶ እና አታክምስ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፏ መሆኑን ተናግረዋል።
ሩሲያ ሐሙስ ዕለት በዲኒፕሮ ላይ የፈጸመችው ጥቃትን የዓይን እማኞች ያልተለመደ ሲሉ የገለጹት ሲሆን እና ለሦስት ሰዓታት ያህል የዘለቀም ፍንዳታ ማስከተሉን ተናግረዋል።
የዩክሬን ባለስልጣናት ከጥቃቱ በኋላ ፍንዳታው በጣም ኃይለኛ በሆነ ሚሳኤል ጥቃት የተከሰተ መሆኑን ጠቅሰው ከአህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳኤል (ICBM) ጋር እንደሚመሳሰል ተናግረው ነበር።
የአደጋ አማካሪ ድርጅት ሲቢላይን ዋና ስራ አስፈፃሚ እና መስራች የሆኑት ጀስቲን ክራምፕ ለቢቢሲ ሞስኮ ጥቃቱን የፈጸመችው እንደ ማስጠንቀቂያ ለመጠቀም ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ ሚሳይሉ ፈጣን እና ባሉት መሳርያዎች ከሌሎቹ እጅጉን የተሻሻለ መሆኑን ጠቅሰው የዩክሬንን አየር መቃወሚያዎች የመገዳደር አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
- የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን እና የጁባላንድ ግዛትን ውዝግብ ውስጥ ያስገባቸው ምንድነው?22 ህዳር 2024
- ቭላድሚር ፑቲን በሚሊዮን በርሜል የሚቆጠር ነዳጅ ለሰሜን ኮሪያ ሰጡ22 ህዳር 2024
- የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በመንግሥት ዕገዳ እንደተጣለበት አስታወቀ22 ህዳር 2024

በዚህ ሳምንት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለው ጦርነት መፋፋሙን ተከትሎ፣ የሌላ አገራት መሪዎች የጦርነቱ አቅጣጫ ወዴት እየሄደ ነው በሚል ማስጠንቀቂያዎችን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ዶናልድ ቱስክ ጦርነቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እየገባ ነው፤ ዓለም አቀፍ ግጭት የመሆን ስጋት አለው ብለዋል።
የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው በምዕራቡ ዓለም የቭላድሚር ፑቲንን ማስጠንቀቂያ “በቀጥታ” ሊወስዱት ይገባል፤ ምክንያቱም ሩሲያ “በዋነኛነት ፖሊሲዋን በወታደራዊ ኃይል ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኒውክሌር ጦርነት ስጋቱ “እንደ አሁኑ” ተባብሶ አያውቅም በማለት አስጠንቅቀው፤ አሜሪካ በፒዮንግያንግ ላይ “ኃይል የታከለበት እና አደፍራሽ” የሆነ ፖሊሲ ትከተላለች ሲሉ ከስሰዋል።
ሰሜን ኮሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ከሩሲያ ጎን እንዲሰለፉ የላከች ሲሆን፣ የዩክሬን ኃይሎች አንዳንድ ግዛቶችን በያዙበት በሩሲያ ኩርስክ ግዛት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን ሞስኮ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን በዚህ ጦርነት ውስጥ በማሰለፏ የተነሳ ዩክሬን ረጅም ርቀት የሚወነጨፉ አታክምስ የተሰኙ አሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤሎችን ሩሲያ ውስጥ ባሉ ዒላማዎች ላይ እንድትጠቀም ፍቃድ ሰጥተዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ የፈጸመችው በአውሮፓውያኑ የካቲት ወር 2022 ነበር። ሁለቱም ሀገራት በጥር ወር ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት በጦር ሜዳ ድል ለማግኘት እየሞከሩ ነው።
ትራምፕ ጦርነቱን በሰዓታት ውስጥ ለማስቆም ቃል ቢገቡም እንዴት እንደሆነ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ዜለንስኪ ከሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁሉም ወገኖች “እንዲረጋጉ እና ራሳቸውን እንዲያቅቡ” ጥሪ ማቅረባቸውን ተችተዋል።
የዩክሬን ፓርላማ አርብ ሊያደርግ የነበረውን ስብሰባ በዲኒፕሮ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በፀጥታ ስጋት ምክንያት በሚል ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉንም ተችተዋል።
በቴሌግራም ላይ በተለጠፈ መልዕክታቸው ላይ የአየር ጥቃት ምልክት እስካልተሰማ ድረስ ሁሉም ሰው እንደተለመደው የሥራ ገበታው ላይ መገኘት አለበት – እና የሩሲያ ዛቻዎችን እንደ “የእረፍት ቀን” አድርጎ መውሰድ አይገባም ብለዋል።
“የአደጋ ጊዜ ደወል ሲሰማ፤ ወደ መጠለያ እንሄዳለን። የአደጋ ጊዜ ደወል ካልተሰማ እንሰራለን። ሕዝባችንን እናገለግላለን። በጦርነት ውስጥ ሌላ መንገድ የለም” ብለዋል።