ኤልያስ ተገኝ

November 24, 2024

ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ ለፓርላማው ልኮታል

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ መቋቋምን ተከትሎ የሕዝብ ጥቅም ላለባቸው ሪፖርት አቅራቢ አካላት፣ የኦዲት አገልግሎት ለሚሰጡ ፐብሊክ ኦዲተሮች ፈቃድ መስጠት የሚያስችል ረቂቅ መመርያ ለግምገማ አቀረበ፡፡

ቦርዱ ከዚህ ቀደም የሒሳብና የኦዲት ባለሙያዎችንና የሒሳብ የሙያ ማኅበራትን በተመለከተ ተግባራዊ ሲያደርገው የቆየው መመርያ በአፈጻጸም ላይ ከታዩበት ክፍተት ባሻገር፣ በመመርያው ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን ለማካተት ረቂቅ የሒሳብና የኦዲት ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥና የሒሳብ ሙያ ማኅበራት ምዝገባ መመርያ መውጣቱ ተገልጿል፡፡

በረቀቅ መመርያው በቦርዱ የሚሰጡ የሙያ ፈቃድ ዓይነቶች አራት ሲሆኑ እነዚህም የሒሳብ ሥራ አገልግሎት፣ የተመሰከረለት ኦዲተር፣ የፐብሊክ ኦዲተርና ጣምራ ፈቃዶች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በግል የሒሳብ ወይም የኦዲት አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ፈቃድ ለማግኘት የፈለገ ጠያቂ፣ የሒሳብ ሙያ ማኅበር አባል ከመሆኑ በፊት ወይም ከሆነ በኋላ ለሦስት ዓመታት በሒሳብ ሥራ ወይም በኦዲተርነት የሥራ ልምድ ያለው መሆን እንደሚገባው የተደነገገ ሲሆን፣ በተጨማሪም 500 ሺሕ ብር የሙያ መድን የገንዘብ ዋስትና ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የተመሰከረለት ኦዲተር ፈቃድ ለማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም የተመሰከረለት የሒሳብ ባለሙያ የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ያዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ ከመሙላት በተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ብር የሙያ መድን የገንዘብ ዋስትና እንደሚያስፈልገው በረቂቁ ተመላክቷል፡፡

የፐብሊክ ኦዲተር ፈቃድ ለማግኘት የሦስት ሚሊዮን ብር የሙያ መድን ዋስትና፣ እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ብር የተመዘገበ የመሥሪያ ካፒታል የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የፐብሊክ ኦዲተር ወይም የተመሰከረለት ኦዲተር ፈቃድ ያለው ባለሙያ ወይም ድርጅት ከሚሰጠው የኦዲት አገልግሎት በተጨማሪ፣ የሒሳብ ሥራ አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ ከሆነ የጣምራ ፈቃድ እንዲሰጠው ተደንግጓል፡፡

የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በረቀቀው መመርያ ማንኛውም የውጭ አገር ዜግነት ያለው ግለሰብ ወይም ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሒሳብ ወይም የኦዲት አገልግሎት መስጠት የሚችለው፣ ግለሰቡ ወይም ድርጅቱ በማኅበሩ ላይ ሊኖረው የሚችለው ድርሻ ከ49 በመቶ ሊበልጥ ካልቻለ ነው፡፡ የውጭ አገር ዜግነት ባለውና ኢትዮጵያዊ በሆነ ባለሙያ ወይም ድርጅት በጥምረት የሚቋቋመው የሽርክና ማኅበር ሥራ አስኪያጅ መሆን የሚችለው፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሸሪክ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የሒሳብና የኦዲት ሙያ በየጊዜው እየሰፋና እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ወቅቱን በሚመጥን ባለሙያ ሙያዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ተብሎ ረቂቅ መመርያው መዘጋጀቱን ያስታወቀው ቦርዱ፣ ረቂቅ መመርያው እንዲዳብር ፍላጎት ያላቸው ባለድርሻ አካላት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በረቂቁ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በተያያዘም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ በኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተጠቃሽ ነው።

የሚቋቋመው ኢንስቲትዩት ብቁና ብዛት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት በመንግሥትና በግል ተቋማት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል፡፡