ተመስገን ተጋፋው

November 24, 2024

ከወለድ ነፃ አገልግሎት ከሚሰጡ ባንኮች አንዱ በሆነው ዘምዘም ባንክ ደንበኞች ሲስተናገዱ

በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች እርስ በርስ እንዲበዳደሩ የሚያስችል መመርያ ቢያወጣም፣ መመርያው ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን ያማከለ አይደለም ተብሎ ቅሬታ ቀረበበት፡፡

የዘምዘም ባንክ ስትራቴጂ ኦፊሰር ኃላፊ አቶ እንድሪስ ዑመር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ከሌሎች ባንኮች ለመበደር ቢፈልጉ ብሔራዊ ባንክ የዘረጋው ሥርዓት አይፈቅድም፡፡

ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ባለሁለት ገጽ መመርያ የብድሩን ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም የመመለሻ ቀናትን፣ የወለድ መጠንን፣ ለተበዳሪ የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችንና ሌሎች ጉዳዮችን የሚገልጽ ቢሆንም፣ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች እንዴት እንደሚሳተፉ እንደማይገልጽ አስረድተዋል፡፡

ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸው ከሌሎች ባንኮች ለመበደር ቢፈልጉ፣ በወለድ እንጂ ከወለድ ነፃ መበደር እንደማይችሉ መመርያው እንደሚደነግግ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ይህንኑ አገልግሎት ለማግኘት ብሔራዊ ባንክ ዘንድ ቢሄዱም፣ ብሔራዊ ባንክ 18 በመቶ ወለድ ከፍለው መበደር እንዲችሉ የሚፈቅድ ሕግ እንጂ የተለየ አሠራር እንደሌለው አስታውሰዋል፡፡  

በተለይ በኢኮኖሚው ውስጥ የቢዝነስ ፖሊሲው ከወለድና ከወለድ ነፃ ባንኮችን ያካተተ ሥርዓት መሆን ሲኖርበት፣ አሁን እየወጡ ያሉ መመርያዎች ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ችላ የሚሉና በወለድ የሚሠሩትን ባንኮች ደግሞ የሚደግፉ ናቸው ብለዋል፡፡

ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ቢያጋጥማቸው፣ ምንም ዓይነት አማራጭን የሚጠቀሙበት ዘዴ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መፍትሔ አበጅለታለሁ እንዳለ፣ ነገር ግን ጊዜው በሄደ ቁጥር ከወለድ ነፃ የሆኑ ባንኮች ከመደበኛ አገልግሎት ከሚሰጡ ባንኮች ጋር ሲነፃፀሩ እኩል የመጫወቻ ሜዳ እንደማያገኙ ጠቁመዋል፡፡

በዋናነት መደበኛ ባንኮቹ ወለድ ላይ የተመሠረቱ እንደሆነ፣ ነገር ግን ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሠሩ ባንኮች ደግሞ ገዝቶ በመሸጥ የሚመጣ ትርፍ ወይም ከተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት የሚመጣ ትርፍን የመጠቀም ሥርዓትን እንደሚከተሉ፣ የሒጅራ ባንክ የስትራቴጂና ማርኬቲንግ ሲኒየር ዳይሬክተር አቶ ጅሬን ሺስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ከተመሠረቱ የአሥር ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ እስካሁን ከሕግና ከሸሪዓ ሕግ አንፃር ታይቶ ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ እንኳን መበደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በአገር ደረጃ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለሚሰጡ ባንኮች ምንም ዓይነት ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ሲኒየር ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ሌላ ዓይነት ሥርዓት እንደሚዘረጋላቸው ቃል መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የሚተዳደሩት በሁለት ሕጎች እንደሆነ ጠቅሰው፣ ባንኮቹ ከሸሪዓ አንፃር እንዴት መሥራት አለባቸው ለሚለው ወጥ የሆነ መዋቅር መኖር አለበት ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በቂ የተማረ የሰው ኃይል እንደሌለ፣ ምክንያቱ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች ስለእስላሚክ ፋይናንስ የሚያስተምር ተቋም አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በእስላሚክ ፋይናንስ ኪሳራና ትርፍን አብሮ ሠርቶ ማጋራት ነው እንጂ ወለድ እንደሌለ ገልጸው፣ ለአብነትም በጣም የሚወደዱና በሸሪዓ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ሙሻረካና ሙባረክ በተሰኙ አገልግሎቶች ለመሥራት አሁን ያለው የብሔራዊ ባንክ ሕግ እንደማያሠራ ጠቅሰው፣ የብሔራዊ ባንክ ሕጉም ከባንክ ሥራ ተወጥቶ እንዲሠራ የማይፈቅድ መሆኑን አክለዋል፡፡