
November 24, 2024

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻ ዊም ቫንሄለፑት ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ
- በየዓመቱ ለቴሌኮም መሠረተ ልማት ኪራይ 25 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮ ቴሌኮም እንደሚከፍል ገልጿል
ከፍተኛ ሀብት ከመቆጠብ ባለፈ የከተማ መሬት ብክነትን ለመቀነስ፣ የቴሌኮም ማማዎችን ለሚገነቡ ገለልተኛ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ገንቢ ኩባንያዎች መንግሥት ፈቃድ እንዲሰጥ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጥያቄ አቀረበ፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል ያለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ለአብነትም ለቴሌኮም ተደራሽነት ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ተጨማሪ 25‚000 የሞባይል ጣቢያዎችን ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡
የግል የቴሌኮም ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የሥራ አፈጻጸሙንና እስካሁን ድረስ የሄደበትን ርቀት የተመለከተ የመስክ ጉብኝት ሐሙስ ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ አድርገዋል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ካቀረቧቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ በተለይም ከቴሌኮም ተደራሽነት አኳያ ተፈላጊውን የመሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያስፈልገው ከፍተኛ የሚባል ካፒታል የሚለው ይገኝበታል፡፡
ምንም እንኳን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተር ፈቃድ ያለውና የራሱን ቴሌኮም ማማ (ታወር)የሚችል ቢሆንም፣ ነገር ግን ትልልቅ የፋይናንስ ኩባንያዎች ድጋፍ የሚያደርጉላቸው መገንባት ገንቢ ኩባንያዎች ገብተው ቢሠሩ ተጨማሪ ኦፕሬተሮች በሚመጡበት ጊዜ አዳዲሰ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታዎች ሳያከናውኑ አገልግሎት በቀጥታ እንዲጀምሩ የሚያስችላቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የታወር ኩባንያዎች ከመገንባት ባሻገር ተፈላጊውን አገልግሎት የማመቻቸት ሥራ መከናወናቸው የቴሌኮም ኩባንያዎች መሠረተ ልማቱን ለመገንባት የሚያውሉትን የጊዜና የገንዘብ ወጪ እንደሚቀንስ ያስረዱት፣ በቅርቡ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ለአብነትም ሳፋሪኮም ከኢትዮ ቴሌኮም ከ1‚300 በላይ ጣቢያዎችን እንደተከራየ፣ በየዓመቱ 25 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንደሚፈጽም በማስታወስ የታወር ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ ቢገቡ መሬት ለመፈለግ የሚያባክኑት ጊዜ እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን የከተማ መሬት እያጣበብን ነው፡፡ እኛም የራሳችን ሳይት አለን፡፡ ሌላም ኦፕሬተር ሲመጣ ሌላ ሳይት ይወስዳል፡፡ ነገር ግን የታወር ኩባንያ ቢመጣ የሦስት አራት ኦፕሬተርን ሥራ በአንድ ጊዜ ይሸከማል፤›› ሲሉ ያስረዱት አንዷለም (ዶ/ር)፣ ሳፋሪኮምም ሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ግንባታ የማድረግ ፈቃድ ቢኖራቸውም ገለልተኛ ሌላ ኩባንያ ቢገባ ተጨማሪ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች እንዲገቡ የሚስብና ለአገርም ይጠቅማል ብለዋል፡፡
ሳፋሪኮም በተጨማሪም መንግሥት ሊመለከታቸው ይገባል ያላቸውን ጥያቄዎች ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ያቀረበ ሲሆን፣ በአገሪቱ የቴሌኮምና የፋይናንስ የውድድር መድረክ እኩል የሆነ ምኅዳር ሊፈጠር ይገባል የሚለው ይገኝበታል፡፡
ለአብነትም ኩባንያው ከፍተኛ ተስፋ በሰነቀበት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ኤምፔሳ (M-Pesa) በጠበቀው ልክ እየተጓዘ አለመሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም በብሔራዊ ባንክ ከተጣሉ ክልከላዎች ጋር እንደሚገናኝ ተመላክቷል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቫንሄለፑት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ኩባንያቸው ለብሔራዊ ባንክ በተለይም ከኢንተር ኦፕሬብሊቲ ማለትም ተገልጋዮች ከኤምፔሳ ወደ ቴሌብር፣ ከቴሌብር ወደ ኤምፔሳ ገንዘብ ማስተላለፍ በተመለከተ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የነዳጅ ክፍያን በተመለከተ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው አሠራር ኤምፔሳን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች በአማራጭ ክፍያ ውስጥ እንዲካተቱ ሳፋሪኮም ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸው፣ መሰል ክፍያዎችን ጨምሮ ሌሎችን በአንድ አገልግሎት አቅራቢ ብቻ የዲጂታል ክፍያ እንዲፈጸም የሚደረግ ከሆነ አገሪቱ ባሰበችው ፍጥነት የዲጂታል ኢትዮጵያ ዕቅድን ዕውን ማድረግ እንደሚያዳግት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዕልባት ቢሰጥበት ተብሎ የቀረበው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ቴሌኮም ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የሳፋሪኮም አንድ ደንበኛ ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ሲደውል የሚጠየቀው ታሪፍ ኩባንያው በራሱ ደንበኞች መካከል ከሚደረገው ጥሪ የተለየ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ከሌላው ኦፕሬተር ወደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለሚደረገው ጥሪ የተለየ የክፍያ ታሪፍ እንደሚጠይቅ፣ ይህም ደንበኛውን የማያበረታታ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ጉዳዩን እንዲመለከተው ሳፋሪኮም ጠይቋል፡፡
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ መንግሥት በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከጅምሩ ደስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለቋሚ ኮሚቴው ተጠሪ ከሆነው የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ጋር በቀረቡት ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ጋር የተያያዙትን ጥያቄዎች ከበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት እንደሚደረግበት አቶ እውነቱ አስረድተዋል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከደንበኛ ቁጥርና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በመላ አገሪቱ ሥርጭቱን በከፍተኛ ፍጥነት እያስፋፋ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ እስካሁንም 46 በመቶ የሚሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል በ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽ ማድረጉን፣ 6.1 ሚሊዮን ንቁ ደንበኞች ማፍራቱን፣ እንዲሁም በመላ አገሪቱ ከሦስት ሺሕ በላይ የኔትወርክ ጣቢያዎች መክፈቱ ተጠቅሷል፡፡