ዝንቅ ኢያሱ..እንደ ተርታ ሰው

ቀን: November 24, 2024

አቤቶ ኢያሱ ሥልጣን እንደጨበጡ፣ በችሎት እየተገኙ፣ ‹‹ፍርድ ጎደለብኝ፣ በደል ደረሰብኝ›› እያለ የሚጮኸውን አቤት ባይ በመስማት፣ ጥፋተኛ ኾኖ የተገኘውን በመቅጣት ‹‹የደኻ እንባ አባሽ›› ተሰኝተው ነበር፡፡ ወጣቱ መስፍን ከተርታው ሰው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ከቤተ መንግሥት አደባባይ እስከ መንደር፣ ከዚያም ባለፍ እስከ ጠረፍ የዘለቀ ነበር፡፡

አንድ ጊዜ፣ አቤቶ ኢያሱ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ፣ መንዝ ላይ፣ አቶ ናደው ከተባሉ አዛውንት ቤት አዳር አደረጉ፡፡ አስተናጋጃቸውን የፊታውራሪነት ማዕረግ ሰጥተው፣ እዚያው ውለው አደሩ፡፡ አንድ ቀን፣ አንድ አሽከር ብቻ አስከትለው፣ ባላገሩን ሲጎበኙ፣ አንድ ባላገር ዶማውን ይዞ ሲቆፍር አገኙና እርሳቸው ዶማውን ተቀብለው ቁፋሮውን ጥቂት እንደ ረዱት፣ ‹ይህስ በዶማ መቆፈር ብዙ ድካም ያለበት ሥራ ነው፡፡ በሬ ገዝተኽ ለምን አታርስም?› አሉት፡፡

‹‹ጌታው! በሬ የምገዛበት ተየት አገኛለኹ፣ ለዚሁም ለጾመኛ አዳሬ መልከኛና ጭቃሹም አጥር እጠር፣ ሁዳድ ቆፍር፣ አሥራት አውጣ፣ መጥን አምጣ፣ እያሉ ሊያስወጡኝ ነው›› አላቸው፡፡

እርሳቸውም ‹‹ለልጅ እያሱ አትነግርምን?›› አሉት፡፡

እርሱም ‹‹ዋ!›› አዬ! ማን አቅርቦኝ›› አለ፡፡

‹‹ነገ ማለዳ ወደ ልጅ ኢያሱ ብትጮኽ፣ እኔ አቀርብኻለኹ›› ብለውት ኼዱ፡፡

ገበሬውም እኹን የተነጋገሩት አቤቶ ኢያሱ እንደ ኾኑ አላወቀምና በበነጋታው ማለዳ ተነስቶ ወደ ሠፈር ኼዶ፣ በሩቅ ኾኖ ‹አቤት!› እያለ ጮኸ፡፡

አቤቶ ኢያሱም ከልካዮች ሲገፉት አይተው ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ አምጡልኝ›› ብለው እንዳላወቀ መስለው ጠየቁት፡፡

ትላንትም በቁፋሮው ላይ የነገራቸውን ከተናገረ በኋላ፣ ለበሬ መግዣ አምሳ ብር ሰጥተው፣ ጭቃሹም እንዳያስቸግረው ግብሩን መልምለው ሲመልሱት እልልታውን እያቀለጠ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ ሕዝቡም የት ያውቁትና ለዚህ ደኻ ይህን ችሮታ አደረጉለት! እያለ ተደነቀ፡፡

ደግሞ ከዕለታት አንድ ቀን፣ እንዲሁ ከሠራዊቱ ተለይተው፣ አንድ ፈረሰኛ ብቻ አስከትለው ሲገሰግሱ፣ አንዲት ሴት የሚሸጥ ዳቦ ይዛ፣ በመንገድ ዳር ተቀምጣ አገኟትና፣ ‹‹አንቺ ሴት! ዳቦ ይሸጣል?›› ብለው ከፈረስ ወርደው፣ ዳቦውን አንስተው ‹‹ዋጋውን ንገሪኝ›› አሏት፡፡

እርሷም ምንም አቤቶ ኢያሱ መኾናቸውን ባታውቅ፣ ከአቤቶ ኢያሱ አሽከሮች አንዱ ይኾናሉ በማለት ጠርጥራ ‹‹ዋጋው ምን ያረጋል!›› ግድ የለም ብሉት አለቻቸው፡፡

እርሳቸውም ጥቂት ቀምሰው ለተከተላቸውም አጉርሰው

‹‹ርስት የለሽምን?›› አሏት፡፡

‹‹ርስት አለኝ፡፡ ግብር ሊነቅለኝ ነው›› ብላ መለሰች፡፡

‹‹ባልስ የለሽምን?›› አሏት፡፡

‹‹ባሌስ ብዙ ልጆች ወልደን ሞተብኝ፡፡ አኹን ቢቸግረኝ ዳቦ እየሸጥኹ ልጆቼን አሳድጋለሁ›› አለቻቸው፡፡

‹‹ነገ ወደ ሠፈር ነይ፣ ለጌታዬ ለአቤቶ ኢያሱ እነግርልሻለኹ›› ብለዋት ኼዱ፡፡

እርስዋም ማለዳ ተነስታ ወደ ሠፈራቸው ኼዳ፣ በሩቅ ቆማ ሳለች አስጠርተው ‹‹ትላንትና ዳቦሽን በልቶ ዋጋውን ሳይከፍልሽ የኼደውን ሰው ታውቂዋለሽን? እስቲ! እዚጋ ካሉት ሰዎች መካከል እንዳለ አሳይኝና የዳቦሽን ዋጋ ላሰጥሽ›› አሏት፡፡

ሴቲቱም ባጠገባቸው ያሉትን መኳንንት በዓይኗ ቃኘችና ወደ አቤቶ ኢያሱ ዘወር ብላ አንገቷን ደፍታ በለስላሳ ድምፅ ‹‹እርሰዎ ነዎ›› አለች፡፡

አቤቶ ኢያሱም በንግግሯ ስቀው አንድ መቶ ብርና አምስት ዳውላ እኽል ዳረጓት፡፡ መሬቷንም መለመሉላትና እርሷም ዕልል እያለች ወደ ቤቷ ኼደች፡፡