November 23, 2024 

በድንጋይ ከሰል ምርት ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል የተባለለት ፕሮጀክት የማዕድን ስፍራው ከህግ አግባብ ውጪ ሊወሰድብኝ ነው አለ

(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ በድንጋይ ከሰል ምርት ቀዳሚ ያደርጋታል የተባለለት ፕሮጀክት እክል ገጠመው ተባለ። በማዕድን ፍለጋና ልማት ላይ የተሰማራ አንድ ድርጅት ሕጋዊ ፈቃድ ቢኖረኝም በሕገወጥ መንገድና የፍርድ ቤት እግድ ተጥሶ የተሰጠኝ የማዕድን ስፍራ ለሌሎች ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብሏል።

‘ማራ ማይነርስ’ የተባለ በማዕድን ፍለጋ፤ ምርመራ፤ ማምረትና እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሠማራ ድርጅት ባለቤት በሕጋዊ መንገድ የተረከብኩት የማዕድን ፍለጋና ማውጫ ቦታ በሕገወጥ መንገድ ተወስዶ ለሌሎች ባለሃብቶች ለመስጠት በተወሰኑ የመንግስት ባለስልጣናት እየተሰራ ነው በማለት ለመሠረት ሚዲያ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ፤ በተጨማሪም በወላይታ ዞን አበላ አባያ ወረዳ ማረቃ ቀበሌ ላይ በሰዓት አምስት መቶ ቶን በዓመት ደግሞ አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም ያለውና በማምረት አቅሙ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የድንጋይ ከሠል ማዕድንን ፓልቨራይዝ በማድረግ ብቸኛ እንደስትሪ ባለቤት የሚያደርጋት የኢንደስትሪ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወነ መቆየቱን የማራ ማይነርስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃነ መስቀል ክንፈ ለመሠረት ሚዲያ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ግን የክልሉ ውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ በድርጅቱ ላይ ተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር በህጋዊ መንገድ የተረከብነውን የማዕድን ቦታ በመንጠቅ እና ከኤጀንሲው ጋር የገባነውን ውል ከህግ አግባብ ውጪ በማቋረጥ የአካባቢ አልሚዎች ለሚላቸው እና ከቢሮው እና ከክልሉ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ትስስር ያላቸው ለሚመስል አካላት ለመስጠት ተደጋጋሚ ሙከራ እንደተደረገ ነው ያለው ድርጅቱ ጥያቄያችን ያልተገባ የፖለቲካዊ እንድምታ እንዲኖረው በማድረግ “የህዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም እንዲውል” የሚል ያልተገባ የፖለቲካ ሽፋን በመስጠት የውንጀላ ምላሽ ተሠጥቶናል ብለዋል።

ድርጅታችን ከሐምሌ 3 ቀን 2015 ጀምሮ ያለበትን በደል በማስመልከት በተለያየ እርከን ለሚገኙ የፍትህ አካላት አቅርበን ሕገ ወጥ ድርጊቱ እንዲቆም የፍርድ ቤት አግድ ቢወጣም የአካባቢው ባለስልጣናት ግን ፈቃድ ያገኘንበትን ሕጋዊ ሒደትና ሰነድ እንዲሁም የፍርድ ቤት እግድን በመጣስ የስር ፍርድ ቤቱን የፍርድ አፈጻጸም ይግባኝ ብለው የፍርድ ሂደቱን ሳይጠብቁ ጉዳዩ በእግድ ላይ ባለበት ሁኔታ የማዕድን ልማት ስፍራውን ከ50 በላይ ለሚሆኑ በጥቅም እና በከባቢያዊነት ለተሳሰሯቸው የአካባቢው አልሚዎች የሚል ሽፈን ለተሰጣቸው አካላት ለመስጠት እየተሰራ ያለው ጉዳይ አግባብ እንዳይደለ የድርጅቱ ባለቤት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ውሃ ቢሮና የዞኑ እና የወረዳው ማዕድን ቢሮ በመተባበር ሲስተም ላይ ሳይመዘገብ የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያና ደንብ ከሚያዘው ውጪ በማኑዋል ፈቃድ እየሰጡ ነው ያለው ማራ ማይነርስ፤ ሕጋዊ ቦታችን በግፍ እየተሞከረ ነው፣ ጉዳዩንም በተመለከተ  ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታችንንም አሰምተናል ብሏል፡፡

አክለውም ፍርድ ቤት ያወጣውን የእግድ ትእዛዝ በመጣሱ ፍርድ ቤቱ ሕግ እንዲያስከብር አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸው በተጨማሪም ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጸፋቸውን ገልጸዋል፡፡