
24 ህዳር 2024
ያለፈው ዓመትን የፓሪስ ኦሊምፒክ ያደምቃሉ ተብለው ከተጠበቁ አዳዲስ ፈጠራዎች አንዱ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የበራሪ ታክሲዎች አገልግሎት መጀመር ነበር።
የጀርመኑ ቮሎኮፕተር በኤሌክትሪክ የሚሠራው እና ሁለት ሰው የሚጭነው ቮሎሲቲ የተባለው በራሪ ታክሲው በከተማዋ መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ ቃል ገብቶ ነበር።
ዕቅዱ አልተሳካም። ኩባንያው የሙከራ በረራዎችን ብቻ ለማድረግ ተገዷል።
ዕቅዱ አለመሳካቱ ኪሣራ ነው ቢባልም ከመጋረጃ ጀርባ አንድ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነበር። ኩባንያውን ከሥራ ውጭ ላለመሆነ ቮልኮፕተር አዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እየሞከረ ነበር።
ከመንግሥት 106 ሚሊዮን ዶላር ለመበደር የተደረጉት ንግግሮች አልተሳኩም።
አሁን ብቸኛ ተስፋው በቻይናው ጂሊ ላይ የተንጠለጠለ ሆኗል። ጂሊ 85 በመቶ የቮልኮፕተርን ድርሻ ለመውሰድ በንግግር ላይ ይገኛል። ለዚህም 95 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል። በድርድሩ መሠረት ከዚህ በኋላ ማምረቻውን ወደ ቻይና እንዲዞር የሚያስገድድ ይሆናል።
በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በራሪ ታክሲዎች ሳይንደረደሩ የሚነሱ እና ሲያርፉም በአንዴ የሚቀመጡ (ኢቪቶል) በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውሮፕላኖችን ከሚሠሩ በደርዘን ከሚቆጠሩ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ቮልኮፕተር ነው።
እንደ ሄሊኮፕተር የሚያገለግል ይህ በራሪ ወጪ፣ ድምጽ እና የአየር ብክለትን የሚቀንስ እንደሚሆን ቃል ገብተው ነበር።
እንዲህ ዓይነቱን አውሮፕላን ለመሥራት ከተቆጣጣሪዎች ፈቃድ ማግኘት ከባድ ነበር። የማምረት አቅምን ለማዳበር የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆንም አንዳንድ ባለሀብቶችን እንዲሸሹ አድርጓል።

ከእነዚህ መካከል በምሳሌነት ከሚጠቀሱት አንዱ ሊሊየም ነው።
የጀርመኑ ኩባንያ በኢቪቶል ጭብጥ ላይ ዳብሯል።
የሊሊየም አውሮፕላን 30 የኤሌትሪክ ጄቶች የሚጠቀመውን አንድ ላይ በመውሰድ ይጠቀምበታል።
ፅንሰ ሐሳቡ ማራኪ ሆኖ ከመገኘቱም በላይ ኩባንያው ከዓለም ዙሪያ የ780 ጄቶች ግዢ ትዕዛዝ እና የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ተናግሯል።
የርቀት መቆጣጠሪያን በመጠቀም የቴክኖሎጂውን ሞዴል ማሳየት ችሏል። የመጀመሪያው ጄት ግንባታ ከመጀመሩም በላይ ሙከራው በ2025 መጀመሪያ ላይ መደረግ ነበረበት።
በሐምሌ ወር በተደረገው የፋርንቦሮ የአየር ትርዒት ላይ ጭምር የሊሊየም ሥራ አስፈጻሚ ሴባስቲያን በዕቅዳቸው መሠረት እንደሚያሳኩት እርግጠኛ ነበሩ።
“በእርግጠኝነት ገንዘብ እያቃጠልን ነው። አውሮፕላኑን እያመረተን በመሆኑ ይህ ጥሩ ምልክት ነው ማለት ነው። በዓመቱ መጨረሻ ላይ ሦስት አውሮፕላኖች ይኖሩናል። ተጨማሪ 1.5 ቢሊዮን ፓውንድም አሰባስበናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኋላ ላይ ግን ገንዘቡ አለቀ።
ሊሊየም ከጀርመን ልማት ባንክ ኬኤፍደብሊው 100 ሚሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ብድር ለማግኘት ሞክሮ ነበር። ብድሩን ለማግኘት ከመንግሥት ዋስትና ቢያስፈልገውም ይህንን ማሳካት አልቻለም።
በኅዳር መጀመሪያ ላይ ደግሞ ኩባንያው መክሰሩን አሳወቀ። የአክሲዮኖቹ ሽያጭም ከናስዳክ የአክሲዮን ገበያ ላይ ተነሱ።
በአሁኑ ጊዜ ኩባንያውን ለመሸጥ ወይም አዲስ ገንዘብ ለማግኘት የባለሙያዎችን መዋቅር እየሠራ ጎን ለጎን ደግሞ የአዲሱን አውሮፕላን ሥራ ቀጥሏል። አዲሱን ኢ-ጄት ወደ ገበያ ለማቅረብ ግን ፈታኝ ጊዜ የተደቀነበት ይመስላል።
- በአሜሪካ መነጋገሪያ የሆኑት የትራምፕን ቅንጡ መኖሪያ እና መዝናኛ የሚጠብቁት የሮቦት ውሾች18 ህዳር 2024
- ያለአብራሪ በሚበረው የሰማይ ታክሲ ይጠቀማሉ?1 መስከረም 2017
- ናሳ ‘ታክሲ ተከራይቶ’ ወደ ህዋ በመወንጨፍ አዲስ ታሪክ ሊያስመዘግብ ነው27 ግንቦት 2020

በኢቭቶል ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ስም ካላቸው መካከል አንዱ የብሪታንያው ቨርቲካል ኤሮስፔስ ነው። ተቋሙ መቀመጫውን ብሪስቶል አድርጎ በስቴፈን ፊትዝፓትሪክ ከስምንት ዓመት በፊት ነበር ተመሠረተው። ባለሃብቱ ኦቮ ኢነርጂንም አቋቋመዋል።
አስደናቂው የቪኤክስ4 ዲዛይን ለመነሳት እንዲሆነው እንደ አውሮፕላን ባሉ ክንፍ ላይ ስምንት ትላልቅ ተሽከርካሪ ክንፎችን ይጠቀማል። ይህ ከሄሊኮፕተር የበለጠ “100 ጊዜ” ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ድምጹ የማይረብሽ፤ ዋጋው ደግሞ 20 በመቶ የሚቀንስ ነው በማለት ፊትዝፓትሪክ ተናግረዋል።
ኩባንያው ለውጥ አስመዝገቧል። የርቀት መቆጣጠሪያ ሙከራውን ካጠናቀቀ በኋላ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በአብራሪዎች ሙከራዎችን ማድረግ ጀምሯል።
መጀመሪያ ላይ አውሮፕላኖቹን ከመሬት ጋር በማጣበቅ ሙከራዎቹ ተከናውነዋል። በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ ከመሬት ጋር ሳይታሰር ለመጀመሪያ ጊዜ የመነሳት እና የማረፍ ሙከራ አደረገ።
ብዙ ወደ ኋላ የጎተቱት ነገሮችም ነበሩ። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በኮትወልድ አየር ማረፊያ በተደረገ ሙከራ ተሽከርካሪ ክንፉ በመገንጠሉ ወድቆ ክፉኛ ተጎድቷል።
በግንቦት ላይ ደግሞ ዋና አጋር የሆነው ግዙፉ የምህንድስና ኩባንያ ሮልስ ሮይስ ለአውሮፕላኑ የኤሌክትሪክ ሞተሮችን ለማቅረብ ከገባው ከስምምነት ወጣ።
ከፍተኛ ተስፋ ነበር። ቨርቲካል ኤሮስፔስ በ2030 ገደማ 150 አውሮፕላኖችን ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብ ተናግሯል። በዚያ ጊዜ በዓመት 200 አውሮፕላኖችን የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። ከገንዘብ አኳያም ከኪሣራ ይወጣል።
የገንዘብ ችግሮች ግን እየተጠናከሩ መጡ። ፊትዝፓትሪክ በመጋቢት ወር ተጨማሪ 25 ሚሊዮን ዶላር ለኩባንያው ፈሰስ አደረጉ።
ተጨማሪ ገንዘብ ባለመገኘቱ ግን በነሐሴ ወር ሊከፈል የሚገባው 25 ሚሊዮን ዶላር ሳይከፈል ቀረ። ከመስከረም ጀምሮ ቨርቲካል ኤሮስፔስ 57.4 ሚሊዮን ዶላር በእጁ ነበረው። በቀጣይ የአውሮፓውያን ዓመት ግን ከዚህ እጥፍ የሚሆን ገንዘብ ወጪ ማድረግ ይጠበቅበታል።
ኩባንያው አሁን ተስፋ ያደረገበት አማራጭ በሙድሪክ ካፒታል ማኔጅመንት በኩል ዋና አበዳሪ ከሆኑት ከአሜሪካዊው ጄሰን ሙድሪክ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ነው።
75 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ሃሳብ አቅርቧል። ዕቅዱን አለመቀበል ደግሞ ኪሳራ እንደሚያስከትል የቨርቲካል ቦርድን አስጠንቅቋል። የመሠረቱትን ኩባንያ የመቆጣጠር ሥልጣናቸውን የሚያሳጣቸው ፊትዝፓትሪክ ዕቅዱን ውድቅ አድርገዋል።
ለንግግሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አሁን ስምምነቱ ሊደረስ ከጫፍ መድረሱን ተናግረዋል። ስምምነት መድረስ ከተቻለ ተጨማሪ የገንዘብ ማሰባሰብ ዕድሎች እንደሚኖሩ ኩባንያው ያምናል።

በዚህ ሁሉ መካከል ግን አንድ የአውሮፓ ፕሮጀክት በጥሩ ጎዳና ላይ ነው ሲል በኤሮኖቲካል ምህንድስና ልምድ ያለው እና ለስዊድን አየር ኃይል የውጊያ ጄቶች ያበረረው ዮርን ፌርም ተናግሯል። በዘአሁኑ ወቅት ለኤሮስፔስ አማካሪው ሊሃም በመሥራት ላይ ይገኛል።
በኤርባስ እየተካሄደ ያለው የኢቪቶል ፕሮጀክት ችግሮችን የመቋቋም ዕድል እንዳለውተናግሯል።
ሲቲኤርባስ ኔክቴክ ጄን ተብሎ የሚጠራው ይህ ባለ አራት መቀመጫ አውሮፕላን ስምንት ተሽከርካሪ ክንፎች እና 80 ኪሜ መጓዝ ይችላል።
“ይህ ለመሃንዲሶቻቸው የቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ነው። ገንዘብ አላቸው። እንዴት እንደሚሠራም ያውቁታል” ሲል ፌርም ተናግሯል።
በተቀረው ዓለም ያሉ እና ጥሩ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ጀማሪዎችም አውሮፕላኖቻቸውን ወደ ምርት በማምጣት ረገድ ጥሩ ለውጥ አሳይተዋል። በዚህ ረገድ የአሜሪካኖቹ ጆቢ እና አርቸር ተጠቃሽ ናቸው።
አውሮፕላኑ ከተመረተ በኋላ ትርፋማ ገበያ መኖሩን ማረጋገጥ ደግሞ ቀጣዩ ፈተና ይሆናል።
የመጀመሪያዎቹ መስመሮች ከአውሮፕላን ማረፊያዎች ወደ ከተማ ማዕከሎች የሚደረጉ በረራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ገንዘብ ግን ያስገኛሉ?
“የሥራ ማስኬጃ ወጪን በተመለከተ ትልቁ ችግር ሚሆነው አብራሪው እና ባትሪዎቹ ጉዳይ ነው። ባትሪዎቹን በዓመት ሁለት ጊዜ መለወጥ ያስፈልጋል” ብሏል ፌርም።
ሁሉንም ጥርጣሬዎች እና ወጪዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለሃብቶች ለምን ገንዘባቸው ወደ እነዚህ አዳዲስ የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖች ያስገባሉ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።
“የሚቀጥለውን የቴስላ ዕድል ማንም እንዲያመልጠው አይፈልገም” ሲል እየሳቀ ፌርም መልሷል።