24 ህዳር 2024
ከጥቂት ወራት በፊት የነርቭ ሐኪም የሆነችው የ44 ዓመቷ ሕንዳዊት ሩቺካ ታንዱን ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ተከፍቶብሻል ተባለች።
በሕንድ ስመ ጥር ከሆኑት ሆስፒታሎች አንዱ በሆነው የምታገለግለው ዶክተር ሩቺካ ምርመራው ቢያስደነግጣትም ሐሰተኛ ይሆናል ብላ ፈጽሞ አላሳበችም ነበር።
ያልጠበቀችው ሆነ ዶክተሯ በዓይነቱ የተራቀቀ የማጭበርበር ሰለባ ሆነች።
ለሳምንት ያህል በቪዲዮ ሲከታተሏት የነበሩት አጭበርባሪዎች የዶክተሯን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው የእርሷን እና የቤተሰቧን ጥሪት አሟጠው ወሰዱ።
ለዓመታት የለፋችበትን ገንዘብ ተነጠቀች።
አጭበርባሪዎቹ “ዲጂታል እስረኛ ነሽ” በሚል ነበር ይሄንን ሁሉ ማጭበርበር የፈጸሙት።
ይህንን “ዲጂታል እስር ውስጥ ነው ያለሽው” የሚል እሳቤ በመፍጠር ዶክተር ታንዱን ከሥራዋ እረፍት እንድትወስድ እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋ ላይ ክትትል ያደርጉ ነበር።
ከፍተኛ ምርመራ ተከፍቶብሻል ያሏት አጭበርባሪዎች የስልኳን ቪዲዮ በመጠቀም ከጥዋት እስከ ማታ ያለውን ተግባሯን በመከታተል እንዲሁም ትዕዛዝ በመስጠት ነበር የሕይወት ዘመኗን ጥሪት የነጠቋት።
የዲጂታል እስር የተሰኘው ሃሳብ አጭበርባሪዎች የሕግ አስከባሪዎችን በመምሰል በቪዲዮ በመደወል፣ በሐሰተኛ ክስ በቁጥጥር ስር ውላችኋል ብሎ በማስፈራራት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲልኩላቸው የሚያድርጉበት የተራቀቀ ዘዴ ነው።
ዶክተሯን የራሷን እና የቤተሰቧን 25 ሚሊዮን ሩፒ (300 ሺህ ዶላር) ከባንክ ሂሳቧ፣ ከጡረታዋ፣ ከሕይወት ኢንሹራንሷ እና ከሌሎች የቁጠባ ሂሳቦቿ አሟጣ ነው የላከችላቸው።
ዶክተሯ ብቻ አይደለችም በዚህ መንገድ የተነጠቀችው።
በርካታ ሕንዳውያን ከ1.2 ቢሊዮን ሩፒ በላይ ‘ዲጂታል እስር’ በተሰኘው ማጭበርበር ባለፈው ዓመት ከጥር እስከ ሚያዝያ ድረስ ማጣታቸውን ይፋዊ አሃዞች ያመለክታሉ።
በርካታ የመጭበርበር ሰለባዎች እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን ሪፖርት ስለማያደርጉ አሃዙ ከዚህ በጣም ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።
በዚህ መንገድ ተጭበርብረው የተዘረፉ ገንዘቦች በውጭ አገራት ወዳሉ የባንክ አካውንች ይዛወራሉ ወይም ወደ ክሪፕቶከረንሲ ተቀይረው ይቀመጣሉ።
እነዚህ በማጭበርብር ከተወሰዱ ገንዘቦች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ሚያንማር፣ ካምቦዲያ እና ላኦስ እንደደረሱ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ።
ሁኔታው በጣም ከመክፋቱ የተነሳ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ስለዚህ ማጭበርበር በሚያደርጉት ወርሃዊ የሬድዮ ንግግራቸው መጥቀስ ነበረባቸው።
“እንዲህ ዓይነት ጥሪ ሲደርሳችሁ አትፍሩ። ማንኛውም የምርመራ ተቋም በስልክ ወይም በቪዲዮ ጥሪ ምርመራ እንደማይከፍት ማወቅ አለባችሁ” ብለዋል።
ሕንድ በሐሰተኛ ኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በፍቅር ግንኙነት ማጭበርበር የትየለሌ የሳይበር (የበይነ መረብ) ወንጀሎች የሚፈጸምባት አገር ናት። ሆኖም የዲጂታል እስርን ለየት የሚያደርገው በጥንቃቄ የታቀደ፣ ጭካኔ የተሞላበት እና የሰለባዎችን እያንዳንዷን ሕይወት በቁጥጥር ውስጥ አስገብቶ የሚደረግ ማጭበርበር መሆኑ ነው።
አንዳንድ ጊዜ አጭበርባሪዎቹ በቪዲዮ ሲደውሉ ራሳቸውን ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ድምጻቸው ብቻ ይሰማል።
የማጭበርበር ሴራው ሲሰማ የሆሊውድ ወይም የቦሊውድ ፊልም ሊመስል ይችላል።
- ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን የሚያበረታታው እና የሞት አጋር የሚያፈላልገው ድረ-ገፅ ተጋለጠ26 መስከረም 2024
- በ20 አገራት የሚገኙ ሴቶችን በበይነመረብ የወሲብ ብዝበዛ የፈፀመው አውስትራሊያዊ ተፈረደበት28 ነሐሴ 2024
- ከለንደን እስከ ኒው ዮርክ 2.5 ሚሊዮን ፓዎንድ ያጭበረበረው ወጣት25 ነሐሴ 2024
በዚያች በተረገመች ዕለት ዶክተሯ የሕንድ የቴሌኮም ተቆጣጣሪ የሆነው ሉክኖው ቤዝድ ባለሥልጣናት ነን የሚሉ ሰዎች ደወሉላቸው። እነዚህ ኃላፊዎች ከዶክተሯ የሞባይል ስልክ የትንኮሳ መልዕክቶች ደርሶናል የሚሉ 22 ቅሬታዎች ስለቀረቡ መስመሩን ልናቋርጠው ነው አሏት።
ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ ነኝ የሚል ሰው ስልኩን ተረከበ። ይህም የፖሊስ ኃላፊ ነኝ የሚለው ግለሰብ ዶክተሯ እና እናቷ ባላቸው የጋራ ባንክ አካውንት የሴቶች እና የሕጻናት ሕገወጥ ዝውውር ለማድረግ እየተጠቀምሽበት ነው ሲል ወነጀላት። ፖሊስ ነኝ ተብዬው ዶክተሯን እያናገረ በነበረበት ወቅት ከኋላም ‘እሰራት፣ ያዛት’ የሚሉ ድምጾች መሰማት ጀመሩ።
“ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውልሽ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ይመጣል። ለሁሉም የፖሊስ ጣቢያዎች ጥሪ ደርሷቸዋል” አላት ሐሰተኛው ፖሊስ።
“በጣም ተናድጄ እና ተበሳጭቼ ነበር። ይሄ በጭራሽ እውነት ሊሆን አይችልም እያልኩ ነበር” ትላለች ዶክተር ታንዶን።
ዶክተሯ በከፍተኛ ሁኔታ ስትናደድ ፖሊስ ተብዬው ድምጹን አለሳለሰ እና ይህ “ብሔራዊ ምሥጢር” ስለሆነ የሕንድ የፌደራል የምርመራ ኤጀንሲ የሆነው ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ምርመራውን ይረከበዋል አላት።
“በአካል እስር ቤት እንዳያስገቡሽ ላናግራቸው እና ላሳምናቸው እሞክራለሁ። ነገር ግን በዲጂታል እስር ውስጥ ትቆያለሽ” አላት።
ዶክተሯ የነበራት ስልክ ዘመናዊ ስላልነበር የቪዲዮ ጥሪ ማድረግ አይችልም። ይህም ለአጭበርባሪዎቹ መሰናክል ነበር። ሱቅ ሄዳ ዘመናዊ (ስማርት) ተንቀሳቃሽ ስልክ እንድትገዛ አስገደዷት።
ከዚህ በኋላ ነው መከራዋ የጀመረው። በሚቀጥሉት ስድስት ቀናት ውስጥ የፖሊስ ኃላፊዎች እና ዳኛ ነን ያሉ ሦስት ወንዶች እና አንዲት ሴት ሕይወቷን ማሸበር ጀመሩ።
የስልኳ የቪዲዮ ካሜራ 24 ሰዓት እንዳይጠፋ አድርገው በስካይፕ እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋ ላይ ክትትል ያደርጉ ጀመር። በአንድ ምሽት የኢንተርኔት ጥቅሏ ባለቀበት ወቅት ተማሪዋን ቀስቅሳ እንድትገዛ አስደርገዋታል።
ምግብ በምታበስልበት፣ በምትተኛበት ወቅት የቪዲዮ ካሜራዋ በርቶ አጠገቧ መሆን አለበት። መታጠቢያ ቤት በምትገባበት ወቅት ራሱ ውጭ ላይ አድርጋ መግባት ነበረባት።
የምትሠራበትን ሆስፒታል በጣም ስለታመመች ሥራ መምጣት አልችልም ብላ መዋሸት ነበረባት። ዘመዶቿንም እንዲሁ ላለማግኘት የውሸት ታሪክ መፍጠር ነበረባት። አጎቷ ድንገት ቤቷ ሲመጡ የስልኳን ካሜራ ቪዲዮ እንዳታጠፋ እና አልጋ ስር እንድትደበቅ አዘዟት።
ዶክተሯ ለአንድ ሳምንት ያህል ስለ ሕይወቷ እና ስለ ሥራዋ ከ700 በላይ ጥያቄዎች መመለስ ነበረባት።
በቪዲዮም ሐሰተኛ ፍርድ ቤት፣ ችሎት፣ እንዲሁም የተጭበረበሩ የፍርድ ሰነዶች እንዲሁም ከዲጂታል እስር ለመውጣት ዋስትናዋን ለማስከበር ጥሪቷን በሙሉ እንድታስይዝ ተጠየቀች።
በዚህ ሐሰተኛ የፍርድ ሂደት ለዳኛው ክብር ለማሳየት ነጭ እንድትለብስ ትዕዛዝ ተላልፎላት ነበር። በእነዚህ ቀናት አጭበርባሪዎቹ ቪዲዮዋቸውን አጥፍተው ሐሰተኛ ስማቸው እና ትክክለኛ የሚመስለው መለዮቻቸው በጥቁሩ ስክሪን ላይ ይታይ ነበር።
በአንደኛው ሐሰተኛ ችሎት ወቅት እነዚህ አጭበርባሪዎች የዶክተሯን የ70 ዓመት እናት “ለልጇ ስትል” ዝም እንድትል አጥብቀው አሳስበዋታል።
ዶክተሯ በእነዚህ መከረኛ የሐሰተኛ ችሎቶች ወቅት ስታለቅስ እና ስትብረከረክ አጭበርባሪዎቹ “ትንፋሽ ውሰጂ፣ ዘና በይ። ግድያ አልፈጸምሽም፤ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንጂ” ይሏት ነበር።
ከዚህ የዲጂታል እስር ነጻ ለመውጣት ባደረገችው ተስፋ አስቆራጭ ትግል በተለያዩ የባንክ ሂሳቦች ያጠራቀመችውን የሕይወት ዘመኗ ጥሪት አጭበርባሪዎቹ ወደሚቆጣጠሩት አካውንቶች ማስተላለፍ ነበረባት።
ዶክተሯ ገንዘቡን ስታዘዋውር እነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሁሉን ነገር መርምረው፣ አጣርተው እና አረጋግጠው እንደሚመልሱላት በማመን ነበር።
ያሰበችው ሳይሆን ሕይወቷን በሙሉ የለፋችበትን ገንዘብ አጣች። ዝውውሩ ሲጠናቀቅ ስልኩም ተዘጋ።
ዶክተር ታንዶን ከመከረኛው ሳምንት በኋላ ወደ ሥራ ስትመለስ ‘የዲጂታል እስር’ እና የፌደራል የምርመራ ቢሮ አዲስ የምርመራ ዘዴዎችን በኢንተርኔት ላይ መፈለግ ጀመረች።
በዚህም ወቅት ነው እሷ የደረሰባት ተመሳሳይ የማጭበርበር ዘዴ ‘ዲጂታል እስር’ በመላው አገሪቱ እየተፈጸመ እንደሆነ የሚዘረዝር የጋዜጣ ዘገባዎች አገኘች።
በእንዲህ ዓይነት የረቀቀ የማጭበርበር ዘዴ ሰለባ መሆኗን ያላመነችው ዶክተሯ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራች። ቢያንስ የስልኩ ፖሊስ ጣቢያ እና ኃላፊዎች እውነተኛ ናቸው በሚል እሳቤ ነበር።
ወደ ፖሊስ ጣቢያው ስትቃረብም በሽብር ስሜት ነበር።
“ለቀናት እንግዳ የሆኑ የስልክ ጥሪዎች እየደረሱኝ ነበር” በማለት ገና መግለጽ ስትጀምር።
አንዲት ሴት ፖሊስ መሃል ላይ ጣልቃ ገባች እና “ገንዘብ ልከሻል?” ስትል ጠየቀቻት።
ሌላ ፖሊስ ጣቢያ ደግሞ የደረሰባትን ጉዳይ ስታስረዳ “ፖሊሶቹ መሳቅ” እንደጀመሩ ዶክተሯ ታስረዳለች።
ፖሊሶቹ ይህ እንዴት የተለመደ ማጭበርበር እንደሆነ ነገሯት።
ኒላንጃን ሙክሆፓድሃይ የሚባል ፀሐፊ እና ጋዜጠኛ ከዚህ የዲጂታል እስር ማጭበርበር ለጥቂት ነው ያመለጠው።
የቀድሞ የተዘጋ የባንክ አካውንቱ ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር እየዋለ ነው በሚል ነበር የደወሉለት። አጭበርባሪዎቹ በዴስክቶፕ ኮምፒውተሩ ለ28 ቀናት ክትትል ያደርጉበት ጀመር። ሁኔታውን ለባለቤቱ አማከራት። እሷም ለጓደኞቹ ነገረቻቸው ኢንተርኔቱን በአስቸኳይ እንድታጠፋው እና እንድታቋርጠው በማድረግ ነጻ አወጡት።
“ጓደኞቼ ይህንን ማጭበርበር እስኪያጋልጡ ድረስ የዲጂታል ባሪያ ሆኜ ነበር። ገንዘቤን በሙሉ ወደ አካውንቴ አንቀሳቅሼ ሁሉንም ጥሪቴን ለእነርሱ ለማዛወር ተዘጋጅቼ ነበር” ብሏል።
አክሎም “ሁሉ ነገር ሲቋጭ ሞኝ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ” ይላል።
እነዚህን አጭበርባሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት ግልጽ አይደለም እንዲሁም ዘገምተኛ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ።
ዶክተር ታንዶንን አጭበርብረዋታል የተባሉ 18 ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። በማጭበርበር ከተዘረፈው ገንዘብ ውስጥ 1/3ኛው በጥሬ ገንዘብ በተለያዩ የባንክ ሂሳቦች ተይዟል። ከተዘረፈችው 25 ሚሊዮን ሩፒ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብ ተመልሶላታል።
የፖሊስ መርማሪ ኃላፊው ዲፓክ ኩማር ሲንግ እንደሚሉት አጭበርባሪዎቹ ሰፊ እና የተራቀቀ ሥራ እየሠሩ ነበር ይላሉ።
“አጭበርባሪዎቹ የተማሩ ግለሰቦች ናቸው። እንግሊዝኛን ጨምሮ የተለዩ የሕንድ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚያውቁ፣ የምህንድስና ምሩቃን፣ የሳይበር የደኅንነት ባለሙያዎች እና የባንክ ባለሙያዎች የተካቱባቸው ናቸው። አብዛኞቹ የሚንቀሳቀሱት በቴሌግራም ቻናል ነው” ሲሉ ከፍተኛ የፖሊስ ባለሥልጣን የሆኑት ሲንግ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሰለባ የሚያደርጓቸውን ሰዎች ክትትል በማድረግ፣ ስለ ግል ሕይወታቸው መረጃ ይሰብስባሉ እንዲሁም ድክመታቸውን ያጠናሉ።
ኒላንጃን የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የሕይወት ታሪክን እንደጻፈ አጭበርባሪዎቹ ያውቁ ነበር። ዶክተር ታንዶንም የሕክምና ባለሙያ እንደሆነች እንዲሁ። የብሔራዊ መታወቂያ ቁጥራቸውን፣ የሚሄዱባቸውን ስፍራዎች፣ የት እንደሚሠሩ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸውን እና ሌሎች መረጃዎችን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናቅረው ነው ሰለባ የሚያደርጓቸው።
ዶክተር ታንዶን ሕይወቷን ያጨለመውን ማጭበርበር ስታስብ ህልም ህልም ይመስላታል።
ለፖሊስ አቤቱታ ስታቀርብ “ፖሊስ ጣቢያው የውሸት ይሆን?” የሚል ጥያቄ ፈጥሮባታል።
እያንዳንዱ የስልክ ጥሪ ያበረግጋታል።
“አንዳንድ ጊዜ ሥራ ላይ ሆኜ በፍርሃት እዋጣለሁ። ቀን ላይ እሻላለሁ። ምሸቶቼ በሰቀቀን የተሞሉ ናቸው” ትላለች።