በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት ምክንያት የወደሙ ሕንፃዎች ፍርስራሽ

24 ህዳር 2024, 08:27 EAT

እስራኤል የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ላይ በፈፀመችው የአየር ድብደባ 20 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

እስራኤል ጥቃቱን ያደረሰችው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሲሆን ጥቃቱ ቅዳሜ ንጋት 10 ሰዓት ገደማ ነው የተፈፀመው። ጥቃቱ የተፈፀመው የሔዝቦላሕ መሪዎችን ለመግደል ነው ሲሉ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ፍንዳታው በመላው ቤይሩት ተሰምቷል። ባስታ በተባለው አካባቢው የሚገኝ ባለስምንት ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል እንዳስታወቀው እስራኤል ‘ባንከር ባስተር’ በመባል በሚታወቀው ቦምብ ነው ጥቃቱን የፈፀመችው። ይህ ቦምብ ሐሰን ናስራላሕን ጨምሮ ሌሎች የሔዝቦላሕ መሪዎችን ለመግደል ጥቅም ላይ ውሏል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በተለያዩ ከባድ የግንባታ መሣሪያዎች ታግዘው በሕንፃው ፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ውለዋል።

የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንደገለፀው ከ60 በላይ ሰዎች ከመቁሰላቸውም በላይ የሟቾች ቁጥር አሁን ከተነገረው እጅግ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

“በጣም አሰቃቂ ፍንዳታ ነበር። የመስኮቶቹ መስታወቶች ተሰባብረው ወደቁብን። በወቅቱ ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር ነበርኩ። መኖሪያ ቤቴ አሁን የጦርነት አውድማ ሆኗል” ይላል ጥቃቱ የደረሰበት አካባቢ የሚኖረው የ55 ዓመቱ አሊ ናሳር።

“አንድ ሰው እንኳ ተደብቆ ቢሆን እንዴት ሰዎች የሚኖሩበትን ሕንፃ ይወድማል? እኒህን ሁሉ ሰዎች ለአንድ ሰው ብሎ መግደል ተገቢ ነው? እኛ እኛ ሰዎች አይደለንም?”

ካን የተባለው የእስራኤል የዜና ጣቢያ ጥቃቱ የተፈፀመው ሞሐመድ ሐይዳር የተባለውን ከፍተኛ የሔዝቦላሕ መሪ ለመግደል መሆኑን ዘግቧል። የሔዝቦላሕ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አሚን ሼሪ ሕንፃው ውስጥ ማንም የቡድኑ አባል እንዳልተደበቀ ተናግረዋል። ሐይዳር ይሙት ይኑር አይታወቅም።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) እስካሁን ስለጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።

አይዲኤፍ ቅዳሜ ዕለት ዳሂየህ በተባላው የደቡባዊ ቤይሩት መንደር ሌሎች ጥቃቶች የፈፀመ ሲሆን ከሔዝቦላሕ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሕንፃዎች ዒላማው አድርጓል።

በሌላ በኩል በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል እስራኤል በፈፀመችው የአየር ድብደባ 4 ሕፃናትን ጨምሮ 15 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት እስራኤል ሔዝቦላሕ ላይ የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች። እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሚሊሻ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጋር የገባችውን ጦርነት ረገብ እንድታደርግና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እያሳደረ ይገኛል።

በተገባደደው ሳምንት የባይደን አስተዳደር ተወካይ የሆኑት አሞስ ሆችስታይን በሊባኖስ እና እስራኤል ተመላልሰው ከሁለቱ ወገኖች ጋር ንግግር አድርገዋል። አሞስ በእስራኤል እና ሔዝቦላሕ መካከል ስምምነት እንዲፈረም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የሊባኖስ ባለሥልጣናት በአውሮፓውያኑ 2006 በእስራኤል እና ሔዝቦላሕ መካከል የተፈረመው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የመፍትሔ ሐሳብ 1701 ተብሎ በሚታወቀው ስምምነት መሠረት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ይፈልጋሉ።

አሁን የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ እስራኤል ከሊባኖስ ምድር እንድትወጣ እና የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እንዲሁም ሔዝቦላሕ ከደቡባዊ ሊባኖስ ገሸሽ እንዲል ያትታል። በምትኩ የሊባኖስ ጦር ደቡባዊውን የሀገሪቱ ክፍል ይቆጣጠራል ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ዲፕሎማት ተናግረዋል።

አንድ ከፍተኛ የሊባኖስ ባለሥልጣን እንደሚሉት ሔዝቦላሕ እና ኢራን ስምምነቱን ለመፈረም ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። ነገር ግን እስራኤል በምን ያክል ጊዜ ከሊባኖስ ትወጣለች በሚለው ጉዳይ አለመስማማት እንዳለ ተናግረዋል።

ባለፈው መስከረም ከእስራአል ከፍተኛ ጥቃት የደረሰበት ሔዝቦላሕ አገግሞ አሁንም እስራኤል ላይ ጥቃት እያደረሰ ይገኛል።

ረቡዕ ዕለት የሔዝቦላሕ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሴም ቡድኑ በአሜሪካ የቀረበውን ሐሳብ እንደሚቀበለው እና ውጤት የሚያመጣ ከሆነ ውይይቶች እንዲቀጥሉ እንደሚሻ ተናግረዋል።

ቡድኑ ያቀረበው ቅደመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና የሊባኖስ የግዛት ወሰን እንዲከበር መሆኑን አሳውቀው ነገር ግን አስፈላጊ ከሆነ ሔዝቦላሕ ለመወጋት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በእስራኤል ጥቃት ምክንያት እስካሁን 3670 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጥቅምት ጀምሮ 15 ሺህ 400 ሰዎች ቆስለዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።