24 ህዳር 2024, 09:22 EAT
ብሪታኒያ በሚገኙ ሶስት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መንደሮች አካባቢ ባለቤትነታቸው ያልታወቁ ድሮኖች እንደታዩ የአሜሪካ አየር ኃይል አስታወቀ።
ከረቡዕ እስከ አርብ ባሉት ቀናት “አነስተኛ ሰው አልባ በራሪዎች” ሰፎክ፣ ፌልትዌል እና ኖርፎክ በተባሉ የጦር መንደሮች አካባቢ መታየታቸውን አየር ኃይሉ ገልጿል።
አየር ኃይሉ በሶስቱ የአሜሪካ ጦር መንደሮች የታዩት ድሮኖች ጥቃት ለማድረስ የመጡ ስለመሆናቸው እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም ብሏል።
የአሜሪካ አየር ኃይል ድሮኖቹን ለመከላከል የተወሰደ እርምጃ ይኖር እንደሁ ከመለግፅ የተቆጠበ ቢሆንም “ራስን ለመከላከል” የሚያስፈልጉ ጥንቃቄዎች ማድረጉን አስታውቋል።
- ከኮማንዶ መሪ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር – ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ማናቸው?23 ህዳር 2024
- ስለ አዲሱ የሩሲያ ኦሬሽኒክ ሚሳዔል ምን እናውቃለን?23 ህዳር 2024
- “እኛ ሰዎች አይደለንም?” – እስራኤል ቤይሩት ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት 20 ሰዎች ተገደሉ24 ህዳር 2024
በአውሮፓ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ቃል አቀባይ “አነስተኛ ሰው አልባ በራሪዎች ብሪታኒያ በሚገኙ ሶስት የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያዎች መታየታቸውን አረጋግጠናል” ብለዋል።
“በተለያየ ጊዜ የመጡት እኒህ ድሮኖች ቁጥራቸው እና ግዝፈታቸው የተለያየ ነበር” ሲሉ አክለዋል።
“ወታደራዊ ደኅንነታችን ለመጠበቅ ሲባል ምን ዓይነት እርምጃ እንደወድን አንገልፅም። ነገር ግን ራሳችንን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንደምናደርግ እንሳውቃለን” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የጦር መንደሮችን አባላት እና ቁሳቁሶች ደኅንነት ለመጠበቅ ለማረጋገጥ ሲባል የአሜሪካ አየር ኃይል አካባቢውን እየቃኘ እንዳለ እና ከብሪታኒያ መንግሥት ጋር ተባብሮ እየሠራ እንደሆነም በመግለጫቸው አውስተዋል።
ሶስቱ የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ጣቢያዎች በርካታ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን የያዙ ናቸው። አልፎም የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያ መንደሮች አሏቸው።
የብሪታኒያ መከለካከይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “መሰል ጉዳዮችን በአትኩሮች ነው የምናያቸው። የጦር መንደሮቻችን ለመጠበቅ እርምጃ እንወስዳለን” ብለው ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሱፎክ ሚድንሆል የሚገኘው የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ በአውሮፓውያኑ 1934 የተገነባ ሲሆን በ2015 ይዘጋል የሚባል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር።
አሜሪካ በአውሮፓ ሀገራት በርካታ የጦር መንደሮች አሏት።