ገና በኢትዮጵያ

24 ህዳር 2024, 09:27 EAT

ከአርባ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ የሚያሳይ ምሥል ቢቢሲ ካስተላለፈ በኋላ ታዋቂ ሙዚቀኞች ገቢ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት አዘጋጅተው ነበር።

የእንግሊዝ እና አየርላንድ ድብልቅ የሆነው ባንድ ‘ኢትዮጵያውያን የገና በዓል መሆኑን ያውቁ ይሆን?’ ማለቱ አይዘነጋም።

ሙዚቀኞቹ ቦብ ጊልዶፍ እና ሚጅ ኡር ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር በመሆን ገቢ ማሰባሰቢያ ሙዚቃ ለቀቁ። ነጠላ ዜማው ተለቆ በስምንት ወሩ ኮንሰርት ተዘጋጀ።

‘Do They Know It’s Christmas?’ ወይም ‘ገና መሆኑን ያውቁ ይሆን?’ የሚለው ሙዚቃ ጉዳይ ከአርባ ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተመልሷል።

አራት የተለያዩ የዘፈኑ ዓይነቶች ተዘጋጅተዋል።

ሆኖም ግን አፍሪካን የሚያጠለሽ አገላለጽ ነው የሚሉ ትችቶች ተሰንዝረዋል።

አፍሪካን ‘ምንም የማይበቅልባት፣ ዝናብ የሌለባት፣ ወንዝ የማይፈስባት’ በሚል በተዛባ ሁኔታ የመሳል ሌላ ገጽታ ተደርጎ ተወስዷል።

አፍሪካውያን እርዳታ ጠባቂ እንደሆኑ አድርጎ በማቅረብም ይተቻል።

በረሃቡ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ በመናገር የሚታወቁት የወቅቱ የመንግሥት ባለሥልጣን ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ “ገና መሆኑን ያውቃሉ? ብሎ መጠየቅ ለእኛ ስድብ ነው። እውነተኛ አይደለም። ኢትዮጵያን በተዛባ መንገድ ይስላል። ኢትዮጵያ ክርስቲያን አገር የሆነችው ከእንግሊዝ ቀድማ ነው። እኛ ገናን የምናውቀው ከእነሱ ቅድመ አያቶች በፊት ነው” ይላሉ።

በዚህ አገላለጽ የሚሰማቸው ቁጣ ድምጻቸው ውስጥ ያስተጋባል። ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው እንዴት ዘፈኑን እንደተቹ ያስታውሳሉ።

የእንግሊዙ ጋዜጠኛ ማይክል ቡሬክ እና ኬንያዊው ፎቶ አንሺ መሐመድ አሚን የሠሩት ዘገባ በወቅቱ በርካታ ሕይወት እንዳተረፈ ግን ሳይጠቅሱ አያልፉም።

ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚሽን ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ የወቅቱ መንግሥት የረሃቡ ዜና እንዲወጣ ባይፈቅድም፣ የቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ወደ አገሪቱ ደብቀው አስገቡ።

አሁን ናሚቢያ የሚኖሩት ዳዊት “የእንግሊዝ ሕዝብ በደግነት ምላሽ መስጠቱ ለሰብአዊነት ያለኝን አመለካከት አጠንክሮታል” ይላሉ።

ከባንድ ኤይድ ጀርባ ያሉትን ሰዎች “ወጣት፣ አስደናቂ እና የሚያደርጉትን የሚወዱ” ሲሉ ይገልጿቸዋል።

በዚህ ሙዚቃ ምክንያት የተረፈው የሰው ሕይወት እንዳለ ሆኖ በሙዚቃ ውስጥ ኢትዮጵያ እንዲሁም አጠቃላይ አፍሪካ የተሳሉበት መንገድ ግን አጠያያቂ ነው።

በቅርቡ በዘ ኮንቨርሴሽን ላይ በወጣ ዘገባ ቦብ ጊልዶፍ “ፖፕ ሙዚቃ ነው። ከዚህ ቀደምም አደገኛ አካሄድ ነው በሚል ተተችቷል። ይህ ሙዚቃ በመቶ ሺዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፍስ አድኗል” ብሏል ።

ኢትዮጵያውያን ገናን እንደሚያከብሩ ቢያውቁም በረሃቡ ወቅት ግን “በዓል ማክበር አልተቻለም ነበር” ይላል።

የባንድ ኤድ ትረስት ዋና የገንዘብ ኃላፊ ጆ ካኖን እንዳሉት ባለፉት ሰባት ወራት 3.8 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በማሰባሰብ 350 ሺህ ሰዎችን በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በሶማሊላንድ እና በቻድ መርዳት ችለዋል።

ሙዚቀኞቹ ቦብ ጊልዶፍና ሚጅ ኡር ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር በመሆን ገቢ ማሰባሰቢያ ሙዚቃ ለቀቁ።
የምስሉ መግለጫ,ሙዚቀኞቹ ቦብ ጊልዶፍና ሚጅ ኡር ከታዋቂ ድምጻውያን ጋር በመሆን ገቢ ማሰባሰቢያ ሙዚቃ ለቀቁ።

ከእርስ በእርስ ጦርነት ለወጣው ሰሜን ኢትዮጵያ ባንድ ኤድ “ቀዳሚ የችግር ጊዜ ደራሽ” በመሆን ሌሎችም እርዳታ እንዲያሰባስቡ እንደሚያበረታታ አክለዋል።

ሆኖም ግን ዘፈኑ ላይ የሚነሳውን ጥያቄ አያጠፋውም።

በምዕራብ አፍሪካ ለኢቦላ መከላከያ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተሠራ ሙዚቃ ላይ የተካተተበት መንገድ ላይ ደስተኛ እንዳልሆነ ድምጻዊ ኤድ ሺረን ባለፈው ሳምንት ተናግሮ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2014 ሙዚቃው ቢሠራም አሁን ግን “ስለሚፈጥረው ትርክት ያለኝ አመለካከት ተለውጧል” ብሏል ሙዚቃኛው።

እንግሊዛዊ ጋናዊው ራፐር ፉስ ኦዲጂ በዚህ ሙዚቃ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልነበረም።

“ዓለም ቢለወጥም ባንድ ኤድ አልተቀየረም። በዚህ የገና በዓል አፍሪካ ውስጥ ሰላም እና ደስታ የለም እያሉ ነው። አሁንም አፍሪካውያን በሞት ተከበዋል እያሉ ነው” ብሏል ለቢቢሲ።

“በየዓመቱ ጋና ለገና እሄዳለሁ። በዘንድሮው ገና ሰላም እና ደስታ አፍሪካ እንዳለ እናውቃለን። ሞት በየቦታው እንደሌለም እናውቃለን። ባንድ ኤድ የአንድን አገር ችግር ወስዶ መላው አህጉሪቱን በዚያ መነጽን ያሳያል” ሲልም ራፐሩ ተችቷል።

አፍሪካውያን በእርዳታ ሙዚቃዎች የሚሳሉበት መንገድ ተጽዕኖ እንዳሳደረበትም ይናገራል።

“ሰዎች እኔን እያዩ ይቀልዱብኛል” ይላል።

በኪንግስ ኮሌጅ መምህር የሆነው እንግሊዛዊ ናይጄሪያዊው ኤድዋርድ አድሞሉ በጉዳዩ ላይ ጥናት ሠርቷል።

ባንድ ኤድን ተከትሎ ኮሚክ ሪሊፍ በአፍሪካ የሠራውን አጭር ፊልም አይቷል።

“አፍሪካውያንን አላዋቂ፣ መጥፎ ጠረን ያላቸው እና ከዱር እንስሳት እኩል አድርጎ መሳል ነው። ትምህርት ቤት ሳለሁ ሁኔታው አፍሪካውያን ጓደኞቼ አፍሪካዊ መሆናቸውን እስኪክዱ ድረስ ያደርሳል” ይላል።

በጣም ሰውነታቸው የመነመነ አፍሪካውያን ምሥል ለእርዳታ ማሰባሰቢያ ይውላል።

የእንግሊዙ ጋዜጠኛ ማይክል ቡሬክና ኬንያዊው ፎቶ አንሺ መሐመድ አሚን የሠሩት ዘገባ በወቅቱ በርካታ ሕይወት እንዳተረፈ ግን ሳይጠቅሱ አያልፉም።
የምስሉ መግለጫ,የእንግሊዙ ጋዜጠኛ ማይክል ቡሬክ እና ኬንያዊው ፎቶ አንሺ መሐመድ አሚን የሠሩት ዘገባ በወቅቱ በርካታ ሕይወት እንዳተረፈ ግን ሳይጠቅሱ አያልፉም።

ሰር ፒተር ብሌክ የሠራው የባንድ ኤድ ነጠላ ዜማ ሁለት ኢትዮጵያውያን ልጆች ጥቁር እና ነጭ ለብሰው ነፍስ አድን ብስኩት ሲበሉ ያሳያል።

ላይቭ ኤድ ኮንሰርት ሲዘጋጅ ደግሞ አንድ እርቃኑን ያለ ሰውነቱ የመነመነ ሕጻን ከጀርባው የተነሳው ፎቶ ተካቷል።

እአአ በ2004 ይህ ምሥል በጥነ ጥበብ ሥራ ውስጥ ተካቷል። አሁንም በዘንድሮው የሙዚቃ ሥራ በድጋሚ ምሥሉ ገብቷል።

እርዳታ በማሰባሰብ የሚሠሩ ሰዎች እና ስለ እርዳታ ጥናት የሚያደርጉ ሰዎች ለምን እነዚህ ምሥሎች ደጋግመው እንደሚመጡ ጥያቄ ያነሳሉ።

ከክርስቲያን ኤድ፣ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ኦክስፋም እና ሌሎችም ከ300 በላይ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር የሚሠራው ቦንድ፣ ሙዚቃው እንደ አዲስ መለቀቁን ተችቷል።

የቦንድ የፀረ ዘረኛነ እትና የእኩልነት ኃላፊ ሊና ብሬሆ “እንደ ባንድ ኤድ 40 ያሉ ስብስቦች ጊዜ ያለፈባቸው ትርክቶችን ያስተጋባሉ። ዘረኛነትን እና የቅኝ ግዛት አስተሳሰብን ያጠናክራሉ። ሰዎችን ባለቤትነት ነፍገው ክብር ያሳጣሉ” ትላለች።

ቦብ ጊልዶፍ ባንድ ኤድ የሚሠራው “በቅኝ ግዛት እሳቤ ነው” የሚለውን አስተያየት እንደማይቀበል ከዚህ ቀደም ተናግሯል።

ኬንያዊው አርቲስት እና ደራሲ ፓትሪክ ጋታራ ምዕራባውያን ስለ አፍሪካ ባላቸው አመለካከት ላይ በመሳለቅ ይታወቃል።

“የሰብአዊ እርዳታ ተቋማት እያደረጉ ባሉት ጫና ለውጦች እየታዩ ነው። ቀውስ ውስጥ የሚገቡ ሰዎችን እንደ ሰው እንጂ እንደ ተጎጂ አለማየት መጀመሩ እጅግ ትልቅ ለውጥ ነው” ይላል።

“ላይቭ ኤድ በሚንቀሳቀስበት ዘመን የሚታየው ምሥል የተራቡ እና የሚሰቃዩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም የሚለው ምልከታ የተዛባ ነው” ሲልም ያክላል።

ከአሥር ዓመት በፊት የኖርዌዩ ተቋም ራዲ ኤድ፣ አፍሪካ እና አፍሪካውያን ከእርዳታ ጋር በተያያዘ የሚሳሉበትን መንገድ በስላቅ የመቀየር ንቅናቄ ጀምሯል።

በቅዝቃዜ እየተሰቃዩ ላሉ የኖርዌይ ዜጎች አፍሪካውያን ማሞቂያ እንዲልኩ ማድረግ አንደኛው የንቅናቄው አካል ነው።

ድምጻዊው ኤድ ሺረን በላይቤሪያ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆቴል እንዲያድሩ በማድረጉ በድርጅቱ ተሸልሟል።

ኮሚክ ሪሊፍ በላይቤሪያ የሠራውን ቪድዮ በተመለከተ ድርጅቱ “ኤድ ሺረን እሱ እንዴት እርዳታ እንደሚሰጥ ከማሳየት ይልቅ ሰዎች እንዴት መተባበር እንደሚችሉ አሳይቷል” ብሏል።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኢስት አንግሊያ የሚያስትምረው ፕሮፌሰር ዴቪድ ጊርሊንግ እንዳለው የራዲ ኤድ ንቅናቄ ለውጥ አምጥቷል።

የእርዳታ ተቋማት የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እየቀረጹ ነው።

“ሰዎች ይደርስ የነበረውን ጉዳት ተገንዝበው እየነቁ ነው” ሲል ያስረዳል።

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የተጨናነቀ መንደር ኪቤራ ላይ ጥናት የሠራው ባለሙያው፣ እርዳታ የሚሰጣቸው ሰዎች ተቀባይ ከመሆን ይልቅ የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበትን አካሄድ አሳይቷል።

የእርዳታ ተቋማት ታዋቂ ሰዎች የንቅናቄ ሥራ እንዲሠሩላቸው ይፈልጋሉ። አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ታዋቂ ሰዎች የሌሉባቸውን የእርዳታ ዘገባዎች መሥራትም አይሹም።

ሆኖም ግን ማርቲን ስኮት የተባለው ባለሙያ በሠራው ጥናት መሠረት፣ ታዋቂ ሰዎች እርዳታ ማሰባሰብ ውስጥ ሲገቡ ትኩረቱ እነሱ ላይ እንጂ ንቅናቄው ላይ አይሆንም።

ዝነኞች በዚህ ሊጠቀሙ ቢችሉም እርዳታ የሚሹ ሰዎች ግን እምብዛም ጥቅም አያገኙም።

ባንድ ኤድ በድጋሚ መሥራት ከፈለገ በአፍሪካ ታዋቂ ከሆኑ አርቲስቶች ጋር መጣመር እንደሚችል የሙዚቃ ጋዜጠኛዋ ክርስቲን ኢቼፉ ትናገራለች።

“የአፍሪካ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ተቀይረዋል። አዲስ ነገር መሥራት ሲፈለግ ከአፍሮቢት ወይም አማፒያኖ አርቲስቶች ጋር በመጣመር ነው የሚሆነው” ትላለች።

“ሰዎች የእርዳታ ፕሮጀክታቸው ይዞት ከሚመጣው ትርክት እና ምሥል ማምለጥ አይችሉም። ባንድ ኤድ አሁንም መጥቶ ሰዎችን የመታደግ ትርክትን ሊያስቀጥል አይችልም” ስትልም ታክላለች።

በኪንግስ ኮሌጅ መምህር የሆነው እንግሊዛዊ ናይጄሪያዊው ኤድዋርድ አድሞሉ ደግሞ “ምናልባትም የቀድሞውን የቸከ ትርክት ወደኋላ ብሎ አዲስ አካሄድ መፍጠር ያስፈልጋል። አፍሪካ ተቀባይ ሳትሆን የራሷን ታሪክ የምትጽፍ ናት” ይላል።