የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ
የምስሉ መግለጫ,ኔታኒያሁ ስድስት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል

23 ህዳር 2024

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚያን ኔታኒያሁ ሰብዓዊነት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ተከሰው የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው አራተኛው የዓለማችን መሪ ሆነዋል።

የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን፣ የሱዳኑ ኦማር አል-በሽር እና የሊቢያው ሙአማር ጋዳፊ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው መሪዎች ናቸው።

የእስራኤል ጦር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፍልስጤም ፈፅሞታል ከተባለው ወታደራዊ እርምጃ ጋር በተያያዘ ነው የእስር ማዘዣው የወጣው። ሰላማዊ ዜጎች ላይ ረሀብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም፣ ግድያ፣ ሰላማዊ ዜጎች የሚኖሩበት ሥፍራ ላይ ሆን ብሎ ጥቃት መፈጸም እና ማጥፋት የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

የኔታኒያሁ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እና ሦስት የሐማስ ወታደራዊ መሪዎች ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል።

የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ውሳኔ እስራኤላውያንን ያስቆጣ ነው። ኔታኒያሁ በእስራኤል ከፋፋይ መሪ ናቸው ይባላሉ። ነገር ግን ተቃዋሚዎቻቸው ሳይቀሩ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቃውመውታል።

ኔታኒያሁ በእስራኤል ታሪክ ብዙ ዘመን ያስተዳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። በጋዛ በኩል ከሐማስ፣ በሌባኖስ በኩል ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ገጥመዋል። ወዲህ ደግሞ ከእስራኤል ዋነኛ ጠላት ኢራን ጋር እሰጥ አገባ ላይ ናቸው።

እስራኤል ውስጥ ደግሞ በሙስና እና ጉቦ በመስጠት ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸዋል። ኔታኒያሁ ይህን ክስ በፍፁም ሐሰት ሲሉ ያስተባብሉታል።

ይህ ክስ በጦርነቶች ምክንያት ተጓትቷል። አንዳንዶች ኔታኒያሁ በዚህም በዚያም ጦርነት ውስጥ የገቡት ችሎት ፊት ላለመቅረብ ነው የሚል ጥርጣሬ አላቸው።

ባለፈው ዓመት መስከረም 26/2016 ሐማስ በእስራኤል ምድር ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል በየሳምንቱ ይካሄዱ የነበሩ ሰልፎች ቀርተዋል። ሰልፎቹ ኔታኒያሁ ያቀዱትን ለውጥ በመቃወም የሚደረጉ ነበሩ። የኔታኒያሁ ተቃዋሚዎች ሰውዬው ሀገሪቱን በታትነዋል፤ የዲሞክራሲም ፀር ናቸው ሲሉ ይወቅሷቸዋል።

ከዚህም ከዚያም በሚወረወሩ ወቀሳዎች እና ክሶች ያልተበገሩት ኔታኒያሁ አሁንም ከሥልጣናቸው ንቅንቅ የሚሉ አይመስሉም። ብዙዎች የሚያውቋቸው ፖለቲካዊ ነውጥን ተቋቁሞ በማለፍ ነው።

ኔታኒያሁ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 ነው በእስራኤል ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ለአምስተኛ ጊዜ መሪ ሆነው የተመረጡት። የአክራሪው እና ቀኝ ዘመሙ ሊኩድ ፓርቲ መሪ ናቸው።

ለ12 ዓመታት ያህል እስራኤልን ካስተዳደሩ በኋላ ለአጭር ጊዜ ተቃዋሚ ሆነው ቆይተው ድራማ በተሞላው መንገድ መልሰው መንበረ ሥልጣን ሲጨብጡ ደጋፊዎቻቸው በቁልምጫ ስማቸው “ንጉሥ ቢቢን” የሚገረስስ የለም ሲሉ አሞግሰዋቸዋል።

ቢቢ ከዚህ ቀደም የእስራኤል ጠባቂ ሆኜ ነው መዘከር የምፈልገው ሲሉ ተናግረው ነበር።

የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኔታኒያሁ አመራር ዘመን እጅግ አሰቃቂው ተብሎ ይቆጠራል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ተዋጊዎች ከጋዛ ድንበር መጥተው 1200 ሰዎች ገድለው 251 ሰዎች አግተው ወስደዋል።

በምላሹ ኔታኒያሁ ሐማስን ለማጥፋት ቃል ገብተው ተነሱ። ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላም ይህ ጦርነታቸው እንደቀጠለ ነው። በእስራኤል ጥቃት ምክንያት ጋዛ ውስጥ ከ44 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል ይላል በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር። በዚህ ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል ላይ ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል።

በሐማስ ታግተው ጋዛ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ለማስለቀቅ እንዲቻል ኔታኒያሁ ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም እንዲደርሱ በሀገር ውስጥ ከባድ ጫና ቢደረግባቸውም ሳይቀበሉት ቀርተዋል። እስራኤል እና ሐማስ ከስምምነት እንዳይደረስ አንዳቸው ሌላኛቸውን እንቅፋት በመሆን ይከሳሉ።

በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ለሐማስ እና ለፍልስጤማውያን ያለውን አጋርነት ለማሳየት እስራኤል ላይ ጥቃት ሲዘነዝር ቆይቷል። በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ከሰሜናዊ እስራኤል ተፈናቅለዋል።

በሐማሱ ጥቃት ማግስት የኔታኒያሁ ተቀባይነት አሽቆለቆለ። ደጋፊዎቻቸው ሳይቀሩ ኔታኒያሁ የደኅንነት ምንጮቻቸው ከፍተኛ ስኅተት በመፈፀማቸው ይህን አምነው ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ሲሉ ወቀሱ። ኔታኒያሁ ግን በእሳቸው ላይ ያነጣጠሩትን ወቀሳዎች ገሸሽ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ቢሆንም የሐማሱ መሪ ያህያ ሲንዋር እና የሄዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህ መገደላቸው እንዲሁም ሄዝቦላህ ላይ የእስራኤል ጦር ያደረሰው ከባድ ውድመት የኔታኒያሁ ተቀባይነት መልሶ እንዲያንስራራ ያደረገ ይመስላል።

ኔታኒያሁ (በስተቀኝ) የኮማንዶ መሪ ሆነው ሲያገለግሉ
የምስሉ መግለጫ,ኔታኒያሁ (በስተቀኝ) የኮማንዶ መሪ ሆነው አገልግለዋል

የወንድማቸው ውርስ

ኔታኒያሁ በቴል-አቪቭ ከተማ በአውሮፓውያኑ 1949 ነው የተወለዱት። አባታቸው ቤንዚዮን ታዋቂ የታሪክ ምሑር እና የፅዮናዊነት አራማጅ ነበሩ። ቤንዚዮን ቤተሰቡን ይዘው በ1963 ወደ አሜሪካ አቀኑ።

ኔታኒያሁ በ18 ዓመታቸው ወደ እስራኤል ተመለሱ። ለአምስት ዓመታት ያክል ሳየረት ማትካል በተባለ ኮማንዶ ክፍል ውስጥ ኃላፊ ሆነው አገለገሉ። በ1972 በፍልስጤማውያን ሚሊሻዎች የተጠለፈ አውሮፕላንን ለማስለቀቅ በሚደረግ ሙከራ ቆስለዋል። በ1973 ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተሳትፈዋል።

ወንድማቸው ጆናታን ደግሞ ምሥራቅ አፍሪካ ኡጋንዳ ውስጥ ነው የተገደሉት። ጆናታን ኢንቴቤ ውስጥ አንድ የተጠለፈ አውሮፕላንን ለማስለቀቅ በተካሄደ የኮማንዶ ተልዕኮ መካከል ነው የተገደሉት። ሞታቸው ኔታኒያሁ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው።

ኔታኒያሁ በወንድማቸው ስም የፀረ-ሽብር ተቋም አቋቋሙ። በአውሮፓውያኑ 1982 የእስራኤል ምክትል አምባሳደር በመሆን ወደ ዋሺንግተን አቀኑ።

በዚህም የአደባባይ ሕይወታቸው በይፋ ጀመረ። ልዩ በሆነው የአሜሪካ እንግሊዝኛ ዘይቤ ሐሳባቸውን በሚገባ መግለጽ ስለሚችሉ በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ለመታወቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ለሀገራቸውም ጥሩ ተጠሪ መሆን ቻሉ።

በአውሮፓውያኑ 1984 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል ቋሚ ተወካይ ሆነው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመንግሥታቱ ዋና ቢሮ ተሾሙ።

ኔታኒያሁ በሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው
የምስሉ መግለጫ,ኔታኒያሁ በሊኩድ ፓርቲ ደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው

ወደ ሥልጣን ከፍታ

ኔታኒያሁ በ1988 ወደ እስራኤል ከተመለሱ በኋላ ነው ፖለቲካውን የተቀላቀሉት። ሊኩድ ፓርቲን ወክለው በእስራኤል ምክር ቤት (ክኔሴት) ውስጥ መቀመጫ ማግኘት አሉ። ቀጥለው ደግሞ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ።

ኔታኒያሁ እስራኤል ከተቋቋመችበት ከ1948 በኋላ ተወልደው የእስራኤል መሪ የሆኑ የመጀመሪያው እና እስካሁንም ብቸኛው ሰው ናቸው። በእስራኤል ታሪክ በዕድሜ ወጣቱ መሪም መሆን ችለዋል።

ምንም እንኳ በ1993 የተፈረመውን የኦስሎ ስምምነት ቢቃወሙም ከዌስት ባንክ ለመውጣት ፊርማ ያኖሩት እሳቸው ናቸው። ይህ ድርጊታቸው ከቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ተቃውሞ እንዲነሳባቸው አድርጓል።

ኔታኒያሁ በ1999 ሥልጣናቸውን ለቀቁ። ምርጫ ከመድረሱ ከ17 ወራት በፊት ምርጫ መደረግ አለበት ብለው የሌበር ፓርቲ መሪ እና የኔታኒያሁ የቀድሞ አዛዥ በሆኑት ኢሁድ ባራክ ተሸነፉ።

ትራምፕ እና ኔታኒያሁ
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ እና ኔታኒያሁ የቅብር የሚባል ግንኙነት አላቸው

ፖለቲካዊ ማንሰራራት

ኔታኒያሁ ከሊኩድ ፓርቲ መሪነታቸው ወርደው በአሪዬል ሻሮን ተተኩ።

በ2001 ሻሮን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ኔታኒያሁ ወደ ሥልጣን ተመለሱ። መጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። ቀጥሎ ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትር ሆኑ። በ2005 እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ መውጣቷን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ከሥልጣናቸው ራሳቸውን አገለሉ።

በ2009 ድጋሚ የሊኩድ ፓርቲ መሪ ሆነው በመወዳደር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መልሰው ወደ አገሪቱ መንበረ ሥልጣን መጡ።

በ2009 ፍልስጤም ከእስራኤል እኩል ሀገር የምትሆንበት ሁኔታ ይመቻቻል የሚል ቃል ቢገቡም በኋላ ግን “ፍልስጤም የምትባል ሀገር አትፈጠርም። በፍፁም አይሆንም” ሲሉ በ2019 ለአንድ የእስራኤል ራድዮ ጣቢያ ተናግረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የእስራኤል የቅርብ አጋር ናት። ነገር ግን በባራክ ኦባማ እና በኔታኒያሁ መካከል የነበረው ግንኙነት የተወሳሰበ ነበር። ኔታኒያሁ ወደ አሜሪካ መጥተው ለኮንግረስ ባደረጉት ንግግር አሜሪካ ከኢራን ጋር የምትገባው የኑክሌር ስምምነት “አያዋጣም” ማለታቸውን ተከትሎ ይበልጥ የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ሻከረ።

ዶናልድ ትራምፕ በ2017 ሥልጣን ሲጨብጡ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት ሲሉ ዕውቅና ሰጡ። ይህ የትራምፕ ውሳኔ ሁለቱ መሪዎችን እጅግ አቀራረባቸው።

የትራምፕ ድርጊት የአረቡን ዓለም ያስቆጣ ነበር። ፍልስጤም የምሥራቁን የእየሩሳሌም ክፍል ይገባኛል ጥያቄ ስለምታነሳ ነው የትራምፕ ውሳኔ ቁጣን የቀሰቀሰው።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከወጡ በኋላ አሜሪካ ከኢራን ጋር ገብታ የነበረችውን ውል አፍርሰው ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀብ ጣሉ። ይህ ለኔታኒያሁ መልካም ዜና ነበር።

ነገር ግን ባይደን ትራምፕን በምርጫ ማሸነፋቻውን ተከትሎ ኔታኒያሁ ባይደንን እንኳን ደስ አልዎ በማለታቸው ትራምፕ ኔታኒያሁን የሚታመኑ አይደሉም ሲሉ ወቅሰዋቸው ነበር።

ተደራራቢ ክሶች

ከአውሮፓውያኑ 2016 በኋላ ኔታንያሁ የሙስና ምርመራ የተካሄደባቸው ሲሆን፣ ከዚያም በኅዳር 2019 ከሦስት የተለያዩ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በጉቦ፣ በማጭበርበር እና እምነትን በማጉደል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ኔታንያሁ ከሀብታም ነጋዴዎች ስጦታዎችን ተቀብለዋል እንዲሁም የበለጠ አዎንታዊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ለማግኘት ውለታን ሞክረዋል ተብለው ይከሰሳሉ።

ነገር ግን ኔታኒያሁ የሌለ ነገር ለማግኘት በተቀናቃኞቻቸው የተቀነባበረ ፖለቲካዊ ግብ ያለው ደባ ሰለባ መሆናቸውን በመግለጽ የሚቀርቡባቸውን ክሶች ሲያስተባብሉ ቆይተዋል። በአውሮፓውያኑ በግንቦት 2020 ፍርድ ቤት የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሙስና ክስ ዳኞች ፊት በመቅረብ የመጀመሪያው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።