
ከ 1 ሰአት በፊት
ቺዮማ ያቀፈችው ‘ሆፕ’ ተሰኘው ህጻን ልጅ የኔ ነው ብላ አጥብቃ ታምናለች።
ከስምንት ዓመታት የከሸፉ ሙከራዎች በኋላ አገኘሁት የምትለውን ህጻን እንደ ተዓምር ነው የምታየው።
“የልጁ ባለቤት እኔ ነኝ” ብላ ስትናገር በሙሉ ልብ ነው።
ቺዮማ ስለ ልጁ የተነሱ አወዛጋቢ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከባለቤቷ አይኬ ጋር በናይጄሪያ የሴቶች እና ማህበራዊ ደህንነነት ኮሚሽን ባለስልጣን ቢሮ ውስጥ ተገኝታለች።
በናምብራ ግዛት የኮሚሽኑ ባለስልጣን የሆኑት ኢፊ አቢናቦ የቤተሰብ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ብዙ ልምድ ቢኖራቸውም ይህ ግን የለመዱት አልነበረም።
በዚህች ክፍል ውስጥ የተገኙት አምስት የባለቤቷ አይኬ ቤተሰብ አባላት ወላጆች ነን ያሉት እነ ቺዮማ ይህንን ህጻን ልጅ እንደወለዱት አያምኑም።
ቺዮማ በበኩሏ ልጁን ለ15 ወራት አርግዤ ነው የወለድኩት ትላለች።
ኮሚሽነሯ እና የአይኬ ቤተሰቦች ይህንን ንግግር የሚሰሙት በድንጋጤ ውስጥ ሆነው ነው።
ልጅ እምቢ ብሏት የነበረው ቺዮማ ከባለቤቷ ቤተሰቦች ከፍተኛ ጫና ደርሶብኛል ትላለች። እንዲያውም እሷን ፈተህ ሌላ ሴት አግባ ብለው ቤተሰቦቹ መክረውታል ስትል ታስረዳለች።
በዚህ ተስፋ መቁረጥ መካከል ሆናም ነው ቺዮማ “ያልተለመደ ህክምና” የሚሰጥ ክሊኒክ የጎበኝችው። የናይጄሪያው ‘ተዓምራዊው ክሊኒክ’ ግን እናቶች መሆንን ከምንም በላይ አጥብቀው የሚሹ መውለድ የተሳናቸው ሴቶችን ኢላማ በማድረግ ያጭበረብራል።
እነዚህ እናቶች በማያውቁት መልኩ የራሳቸው ያልሆኑ ህጻናት ወልዳችኋችኋል ይባላሉ። ህገወጥ የህጻናት ዝውውር በዋናነት ይካሄድበታል።
ከማህበረሰባቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለመጠበቅ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተካተቱትን የቺዮማ፣ አይኬ እና ሌሎችን ስሞች ተቀይሯል።
- ሚሊዮኖችን በማጭበርበር የሚዘርፈው ‘የሕንዱ የዲጂታል እስር’24 ህዳር 2024
- ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን የሚያበረታታው እና የሞት አጋር የሚያፈላልገው ድረ-ገፅ ተጋለጠ26 መስከረም 2024
- ለዘጠኝ ዓመታት በሐሰተኛ ማንነት በኢንተርኔት የተታለለችው አፍቃሪ23 ጥቅምት 2024

“ተዓምራዊው ሕክምና”
ናይጄሪያ በዓለም ላይ ከፍተኛ የወሊድ መጠን ካላቸው አገራት አንዷ ናት። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሴቶች በትዳር ውስጥ ልጅ መውለድ ካልቻሉ ከፍተኛ የማህበራዊ ጫና፣ መገለልና እንዲሁም ይባስ ብሎ እንግልት ያጋጥማቸዋል።
ይህንን ጫና መቋቋም የከበዳቸው ሴቶች የእናትነት ህልማቸውን እውን ለማድረግ የማይሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ይገባሉ።
ከአንድ ዓመት በላይ ቢቢሲ አፍሪካ አይ የተሰኘው በምርመራ ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም በናይጄሪያ “ሚስጥራዊ እርግዝና” (ክሪፕቲክ ፕሬግናንሲ) ተብሎ የሚጠራውን ሲመረምር ቆይቷል። አጭበርባሪዎች ዶክተሮች እና ነርሶች ነን በማለት ሴቶችን የሚያስረግዝ “ተዓምራዊ የወሊድ ህክምና” እንዳላቸው ያሳምኗቸዋል።
የመጀመሪያው “ህክምና” መርፌ፣ መጠጥ ወይም በሴት ብልት ውስጥ የሚከተቱ ንጥረ ነገሮችን የሚያካትት ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር ያስወጣል።
በምርመራችን ወቅት ካነጋገርናቸው ሴቶች ወይም ባለስልጣናት መካከል አንዳቸውም እነዚህ መድኃኒቶች የተሰሩባቸውን ወይም የያዙዋቸውን ንጥረ ነገሮች በትክክል አያውቁም።
ነገር ግን አንዳንዶቹ ሴቶች ሆዳቸው ማበጥን ጨምሮ ሌሎች አካላዊ ለውጦች እንዳዩ ተናግረዋል። ይህም ለመጽነሳቸው አሳማኝ ምክንያት ሆኗቸዋል።
“ህክምናው” የተሰጣቸው ሴቶች በሌሎች የጤና ማዕከላት የእርግዝና ምርመራም ሆነ ዶክተሮችን እንዳያዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ለዚህም የተሰጣቸው ምክንያት “ጽንሱ” ከማህጸን ውጭ እያደገ ስለሆነ የትኛውም የምርመራ መሳሪያ እርግዝና መኖሩን አያውቅም የሚል ነው።
ለመውለድ ጊዜያቸው ሲቀርብ ምጥ የሚጀምራቸው “የማይገኝ እና ውድ መድሃኒት” ሲወጉ እንደሆነ ይነገራቸዋል። ሴቶቹ ይህንን መድኃኒት ለማግኘት ተጨማሪ ክፍያ መክፈል አለባቸው።
ሴቶቹ እንዴት ወለዱ? ለሚለው የተለያዩ የሚረብሹ ሁኔታዎችን ቢቢሲ ሰምቷል፥ አንዳንዶቹ ማደንዘዣ ከተሰጣቸው በኋላ ሲነቁ በሆዳቸው ላይ የሲ-ሴክሽን ቀዶ ጥገና ምልክቶች በሆዳቸው ላይ አግኝተዋል።
ሌሎቹ ደግሞ መርፌ ከተወጉ በኋላ የመደንዘዝ እና እንዲሁም እየወለዱ እንደሆነ ነው እንደተሰማቸው የሚያደርግ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸዋል። ያም ሆነ ይህ ሴቶቹ ወለዷቸው የተባሉ ህጻናትን ይዘዋል።
ቺዮማ የመውለጃዋ ሰዓት በተቃረበ ወቅት ዶክተር ተብዬው ወገቧ ላይ መርፌ ወጋትና እንድታምጥ እንደነገራት ለኮሚሽነር ኢፊ ገልጻለች። ምጧ በህመም የተሞላ እንደነበር ቺዮማ አክላ አስረድታለች።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ጋዜጠኞች ቡድን በዚህ ሚስጥራዊ ክሊኒኮች ውስጥ በአንዱ “ሰርጎ” መግባት ችሎ ነበር። ለስምንት ዓመታት ያህል ሞክረው ልጅ እምቢ ያላቸውን ጥንዶችን በመምሰል ነበር “ዶክተር ሩት” የተሰኘች ሴት ያገኙት።
ይህ ዶክተር ሩት የተሰኘችው ግለሰብ ኢሂያላ በተሰኘች ከተማ ውስጥ በሚገኝ በአንድ በፈራረሰ ሆቴል ውስጥ ነው ክሊኒኳ የሚገኘው።
ወሩ በገባ በሁለተኛው ቅዳሜ ነው የምትገኘው። ከክፍሏ ውጭ በሚገኘው የሆቴሉ መተላለፊያ በርካታ ሴቶች እየጠበቋት ነበር።
አንዳንዶቹም ሆዳቸው አብጦ ይታያል። አካባቢው በደስታ የተሞላ ነው። የቢቢሲ ጋዜጠኞች ማዕከሉን ሊጎበኙ በሄዱባት በአንዷ ዕለት ነፍሰ ጡር መሆኗ የተነገራት ሴት ከክፍሉ ስትወጣ በሆይታ እና በእልልታ ተሞላ።
የቢቢሲ ጋዜጠኞች ተራቸው ሲደርስ ዶክተር ሩት ክፍል ውስጥ ገቡ። እሷም ህክምናው ለመስራቱ ሙሉ በሙሉ ዋስትና ሰጠቻቸው።
ዶክተር ሩት ባለትዳር ሆነው ለቀረቡት የቢቢሲ ጋዜጠኞች የጽንሳቸውን ጾታ እንዲመርጡ ያስችላችኋል ያለቻቸውን መርፌ ሴቷ እንድትወጋ ጠየቀቻት።
የልጅ ጾታን መምረጥ ህክምና ያልደረሰበት ሳይንስ ነው።
ጥንዶቹ መርፌውን አልቀበልም ካሉ በኋላ ዶክተር ሩት የደቀቁ ክኒኖች በአንድ ከረጢት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ እንክብሎችን እና ወሲብ መቼ መፈጸም እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ ሰጠቻቸው። ይህ የመጀመሪያ ህክምና በናይጄሪያ መገበያያ 350 ሺህ ናይራ ወይም 200 ዶላር ነው።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ መድኃኒቱን ሳትወስድ እንዲሁም የዶክተር ሩት የትኛውንም መመሪያ ሳትከተል ከአራት ሳምንታት በኋላ በቀጠሮዋ መጣች። ዶክተር ነኝ ባይዋ ግለሰብ የአልትራሳውንድ የሚመስል የስካነር መሳሪያ በሪፖርተሯ ሆድ ላይ ካደረገች በኋላ የልብ ምት የሚመስል ድምጽ ተሰማ። ዶክተር ሩትም ጥንዶቹን እንኳን ደስ አላችሁ አለቻቸው። ጋዜጠኞቹም ለማስመሰል በደስታ ተዋጡ።
ምስራቹን ያሰማችው ዶክተር ሩት ህጻኑ እንዲወለድ በመሰረታዊነት የሚያስፈልገው ብርቅ እና ውድ የሆነ መድኃኒት መግዛት አለባችሁ አለቻቸው። መድኃኒቱም 1.5 ሚሊዮን ናይራ ወይም 1 ሺህ ዶላር ዋጋ አለው ተባለ።
ይህንን መድኃኒት ካልተወሰደ እርግዝናው ከዘጠኝ ወራት በላይ ሊራዘም እንደሚችል ነው ዶክተር ነኝ ባይዋ ግለሰብ ከሳይንሳዊ እውነታ በተጻራሪ መልኩ የተናገረችው። እንደ ግለሰቧ “ጽንሱ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ያጋጥመዋል እንደገና ማፋፋት አለብን” በማለት እንዴት እርግዝና እንደሚራዘም ተናገረች።
ዶክተር ሩት ቢቢሲ ዘገባውን ሲያጠናቅር ለቀረቡባት ክሶች ምላሽ አልሰጠችም።
እነዚህ ሴቶች እርግዝናችሁ ከዘጠኝ ወራት በላይ ነው ሲባሉ ለምን እንዳመኑ ግልጽ ባይሆንም ነገር ግን ለምን እንዲህ ላለው አሳፋሪ ውሸቶች ሊጋለጡ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ፍንጮች አሉ።
በእርግዝና ዙሪያ የተዛመቱ ሃሰተኛ እና የተሳሳቱ መረጃዎች በኢንተርኔት ላይ መገኘት ለዚህ በከፊል አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል።
ስለ “ምስጢራዊ እርግዝና” የተሳሳቱ መረጃዎች
ማርገዛቸውን ሳያዉቁ ከወራት በኋላ ወይም ምጥ ሲጀምራቸው ወይም ሊወልዱ ሳምንታት ሲቀራቸው የሚታወቅ እርግዝና የታወቀ የህክምና ክስተት ነው።
ክሪፕቲክ ፕሬግናንሲ ወይም “ምሥጢራዊ እርግዝና” ይሰኛል።
ነገር ግን በምርመራችን ወቅት ቢቢሲ ምስጢራዊ እርግዝናን በተመለከተ በርካታ የተሳሳቱ መረጃዎችን በፌስቡክ ገጾች ተነዝተው አግኝቷል።
ሚስጥራዊ እርግዝና አጋጥሞኛል ያለች አንዲት አሜሪካዊት ሴት ለዓመታት ነፍሰ ጡር ሆና መቆየቷን እና ይህ ሁኔታዋ በሳይንሳዊ መንገድ ሊገለጽ እንደማይችል በፌስቡክ ገጿ አጋርታለች።
አባላት ላልሆኑ ዝግ የሆኑ ቢቢሲ ያገኛቸው የፌስቡክ ገጾች በናይጄሪያ እየተካሄደ ያለውን ማጭበርበር መጸነስ ላልቻሉ ሴቶች ተዓምራዊ ህክምና ሲሉ ነው የጠሩት። እነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ሴቶች በዚህ የማጭበርበር ተግባር ላይ ያላቸውን እምነት ያጠናከረ ነው። የፌስቡክ ገጾቹ አባላት ከናይጄሪያ ብቻ ሳይሆኑ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከካሪቢያን እና ከአሜሪካም ጭምር ናቸው።
አጭበርባሪዎቹ ጭምር እነዚህን ገጾች ሰለባቸውን ለማግኘት ይጠቀሙበታል።
ሴቶቹ በነዚህ የፌስቡክ ገጾች ላይ በዚህ የማጭበርበር ህክምና ዝግጁ ነን ካሉ ይበልጥ ደህንነታቸው ወደተጠበቁ የዋትስአፕ የቡድን ገጽ ላይ እንዲገቡ ይጋበዛሉ። እነዚህን የዋትስአፕ ገጾችን የሚያስታዳድሩ ግለሰቦች ስለ “ሚስጥራዊ ክሊኒኮች” እና ሂደቱ ምን እንደሚያካትት በዝርዝር መረጃን ያጋራሉ።
“ግራ ተጋብቻለሁ”
ሴቶቹ ሳያረግዙ እንዴት ልጅ አገኙ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
እነዚህ አጭበርባሪዎች “ህክምናውን ለማጠናቀቅ” የተወለዱ አራስ ህጻናት ያስፈልጋቸዋል።
እነዚህንም አራስ ህጻናት የሚያገኙት ጽንስ ማቋረጥ ካልቻሉ በአብዛኛው ተጋላጭ ወጣት ሴቶች ወይም ደሃ ከሆኑ ነፍሰጡት ሴቶች እንደሆነ ባለስልጣናቱ ይናገራሉ። በናይጄሪያ ጽንስ ማቋረጥ ህገወጥ ነው።
በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ የአናምብራ ግዛት የጤና ሚኒስቴር ቺዮማ ሆፕን “የወለደችበትን” ማዕከል ላይ ድንገተኛ ፍተሻ እና ወረራ አድርጓል። ቢቢሲ ይህንን ወረራ የሚያሳይ ቪዲዮ አግኝቷል። ማዕከሉ ሁለት ህንጻዎችን የያዘ ነው። አንደኛው ክፍል ውስጥ የህክምና መሳሪያዎችን ይዟል። ሌላኛው ክፍል ደግሞ ያለፍቃዳቸው የተቀመጡ በርካታ ነፍሰ ጡሮችን የያዘ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ 17 ዓመታቸው የሆኑ ነፍሰጡሮች ነበሩበት።
ነፍሰ ጡሮቹ ልጆቻቸው ለነዚህ አጭበርባሪ ደንበኞች እንደሚሸጡ አያውቁም። በዚህ ክፍል ውስጥም የተገኙት ተታልለው ነው።
ቢቢሲ ለደህንነቷ ሲል ኡጁ ሲል የሚጠራት ግለሰብ ለቤተሰቦቿ ነፍሰ ጡር መሆኗን ለመንገር በጣም ስለፈራት መውጫ መንገድ እየፈለገች ነበር። ለጽንሷ 800 ሺህ ናይራ (500 ዶላር) እንሰጥሻለን ተባለች።
ልጇን ለመሸጥ ባደረገችው ውሳኔ ተጸጽታ እንደሆነ ቢቢሲ በጠየቃት ወቅት “አሁንም ግራ ተጋብቻለሁ” ብላለች።
በግዛቲቷ ያሉትን እንዲህ አይነት ማጭበርበሮችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ዋነኛ አስተባባሪ የሆኑት ኮሚሽነሯ አጭበርባሪዎቹ አራስ ህጻናትን ለማግኘት እንደ ኡጁ ያሉ ተጋላጭ ሴቶችን ኢላማ ያደርጋሉ ይላሉ።
በኮሚሽነሯ ቢሮ ውስጥ የነበረው ምርመራ ሲጠናቀቅ ህጻኑ እንደሚወሰድ ለነቺዮማ ተነገራቸው።
ቺዮማ በበኩሏ ራሷ የዚህ ማጭበርበር ሰለባ እንደሆነች እና ምን እየተከናወነ እንደነበር እንዳላወቀች ለኮሚሽነሯ በመንገር ልጇን እንዳይወስዱ ተማጸነች።
ጉዳዩን የሰሙት ኮሚሽነሯ የሆፕ ትክክለኛ ወላጆች እስካልመጡ ድረስ እነ ቺዮማ እንደ ልጃቸው ማሳደግ እንደሚችሉ ውሳኔያቸውን ሰጡ።
ነገር ግን በሴቶች ላይ ያለው አመለካከት፣ መሃንነት፣ የስነ ተዋልዶ መብት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ለውጥ እሰካልመጣ ድረስ እንደዚህ አይነት ማጭበርበሮች እንደሚስፋፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።