November 25, 2024 

እናት ፓርቲ፣ በሰሜን ሸዋ ደራ ወረዳ ባንድ ወጣት ላይ ከተፈጸመው ዘግናኝ ግድያ ጋር በተያያዘ መንግሥትና የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን “ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት” እንዲያቆሙ ጠይቋል።

ፓርቲው፣ ግድያው በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ፍትህ እንዲሰፍን ጥሪ አድርጓል።

መንግሥትን ጨምሮ ኹሉም ታጣቂ ኃይሎች ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ ማድረግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተረድተው፣ ከመሰል ጥፋቶች እንዲታቀቡም ፓርቲው አሳስቧል።

የፓርቲው ሙሉ መግለጫ ከዚህ በታች ተያይዟል።

የተመለከትነው ዘግናኝ ቪዲዮ የሽብር ጥግ ማሳያ ነው። በአንጻሩ መንግሥታዊ መዋቅሩ ድርጊቱን ለፖለቲካ ትርፍ ያዋለበት መንገድ የሚወገዝ ተግባር ነው።

(በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የተመለከትነውና ከየት መጣውን ለማጣራት ጥረት እያደረግን ያለውን ምስል ወድምጽ(video) እጅግ ዘግናኝና በጽኑ ቃል የሚወገዝ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። ፓርቲያችን ድርጊቱ በማን፣ የትና መቸ እንደተፈጸመ ለማጣራት ጥረቶችን እያደረገ ሲሆን በዚሁ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በተለመደው መልኩ በገለልተኝነት ጥረታቸውን አድርገው ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነታችን ነው።

ከዚኹ ጋር ተያይዞ እጅግ ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገቡና ከዚኽ ዘግናኝ ድርጊት ጀርባ ምን የተደገሰ ነገር አለ? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርጉ አንዳንድ ኹነቶችን ታዝበናል። ወለጋ የደም ምድር፣ የእልቂት ሜዳ ሲሆንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በዘግናኝ ኹኔታ በአንድ ጀምበር ሲያልቁ፤ መላው የኦሮሚያ ሕዝብ የቀን ገዥና የጨለማ ገዥ እየተፈራረቀበት ቁምስቅሉን ሲያይ፣ ልጆቹን ሲነጠቅ፤ አፋርና ሶማሌ ሥርዓቱ በፈጠረው ግጭት ወገኖቻችን በመቶዎች ሲሞቱ፤ እዚኹ አፍንጫችን ሥር ምሥራቅ ሸዋ በአንድ ሌሊት 43 ሰው ቤት ተዘግቶ ሲቃጠል፤ ሞጆ ወረዳ ላይ አረጋዊ ካህን ከነቤተሰባቸው ለዘር እንዳይተርፉ ወንዝ ዳር እንደበግ ሲታረዱ፤ የዝቋላ አቦ ገዳማውያን አባቶች ተቆራርጠው ጭምር ሲገደሉ፤ ደራ ላይ የመስጅድ ኢማም ከነቤተሰባቸው ለዘር እንዳይተርፉ በዘግናኝ ኹኔታ ሲገደሉ፤ በመላው አማራ ሰው በተገኘበት ይገደል ተብሎ የታወጀ እስኪመስል ድረስ ነብሰ ጡሮችና ሕጻናት ሲያልቁ፤ ትግራይ የሞት ጥላ አንዣቦ በረሃብና በሰው ሠራሽ መንገድ ሕጻናት ጭምር ሲያልቁ፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ ለመስማትም ለማየትም በሚዘገንን መልኩ እልቂት ሲፈጸም ምንም እንዳልተፈጠረ አሸሸ ገዳሜ ሲደልቁ የኖሩ የመንግሥት ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ ብቻ እንዴት ከደስታ እንቅልፋቸውና ፈንጠዝያቸው ነቅተው ሙሾ አውራጅ ሆኑ? “ለሞቱት ዛፍ እንተክላለን” እያለ በሞት ላይ ሲዘብት የነበረው መንግሥት እንዴት ተሰምቶት ሀዘን ተቀመጠ? ኦሮሚያ የደም መሬት ሲሆን የሕዝቡን ብሶት ተጋርቶ የማያውቀው፣ አትግደሉን እያለ ልጆቹን ቀንበር ጠምዶ ለወጣው ሕዝብ ጠብ የሚል መፍትሔ ያልሰጠውና ሲጠየቅም ጆሮ ዳባ ልበስ የሚለው የክልሉ መንግሥት እንዴት አኹን ነቅቶ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ መግለጫ አወጣ? የሚሉት በውል መታየት ያለባቸው ሰበዞች ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህ አስነዋሪ ድርጊት ጀርባ ማን ነው ያለው የሚለውንም ፍንጭ ይሰጡ ይሆን ወይ? ብለን እንድንጠይቅ አስገድዶናል።

ዘግናኝ ድርጊቱን አውግዞ፣ ተገቢው ማጣራት ተደርጎበት አጥፊዎችን ለፍርድ አደባባይ ማቅረብ፣ ድርጊቱም በምድራችን ዳግም እንዳይከሰት ተባብሮ መሥራት ሲገባ ሀኪም አጥቶ በጽኑ ደዌ ተይዞ የሚሰቃየውን ፖለቲካችንን መንግሥታዊ መዋቅሩና መንግሥት የሚዘውራቸው ሚዲያዎቹ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ያደረጉት እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍና እልቂት ጠመቃ ውሎ አድሮ ከተጠያቂነት እንደማያድን በእርግጥ መናገር ይቻላል።

በአንጻሩ ከዚህ በፊት ጽንፍ በወጣ የፖለቲካ አቋማቸው የምናውቃቸው ግለሰቦች ተው ባይ ሆነው መታየታቸው እጅጉን የሚደነቅ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይሄው ስክነትና ፖለቲካዊ መቀራረብ መሆኑን በተግባር ለማስተማር ጅምር ሙከራዎች ታይተዋል። በመሆኑም

፩. እናት ፓርቲ ድርጊቱንና የድርጊቱን ፈጻሚዎች በጽኑ ያወግዛል፤ በገለልተኛ አካል ተጣርቶም ፍትሕ እንዲሰፍን አጥብቆ ይጠይቃል።

፪. መንግሥትና የመንግሥት ሚዲያዎች ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት እንዲያቆሙ እናሳስባለን።

፫. መንግሥትን ጨምሮ ኹሉም ታጣቂ ኃይሎች ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው ንጹሓን ዜጎችን ዒላማ ማድረግ የጦር ወንጀል መሆኑንና ይዋል ይደር እንጂ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በመረዳት ከዚህ መሰል ጥፋት እንዲታቀቡ አጽንዖት ሰጥተን እናሳስባለን።

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

እናት ፓርቲ

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ