አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል በሩሲያ
የምስሉ መግለጫ,አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል በሩሲያ

25 ህዳር 2024

ዩክሬን ከአሜሪካ በተሰጣት ሚሳዔል በሩሲያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የሩሲያ የአጸፋ ጥቃት የበረታባቸው ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ አገራቸውን የጦር መሳሪያዎች መሞከሪያ አድርጋታለች ሲሉ ሰሞኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዲኒፕሮ በተሰኘችው የዩክሬን ግዛት ላይ የተፈጸመውን የሩሲያን ጥቃት አስመልክተው ፕሬዚዳንቱ “በሁሉም ባህሪያት፣ በፍጥነቱ እና በከፍታው ከአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ጋር ተመሳሳይነት አለው” ሲሉ ገልጸዋል።

ሩሲያ በጥቃቱ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።

በርካታ ምዕራባውያን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ጥቃቱ የተፈጸመው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።

ጥቃቱ የተፈጸመው በዚህ መሳሪያ ከሆነ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል (አይሲቢኤም) በዓለማችን ላይ ተግባራዊ የሆነበት የመጀመሪያው ጦርነት ይሆናል።

ለመሆኑ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች (intercontinental ballistic missiles) ምንድን ናቸው? ተግባር ላይ መዋሉ ለምን ጥያቄ ያስነሳል?

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ምንድን ነው?

አህጉር አቋራጭ ሚሳዔል ስሙ እንደሚያመለክተው አውዳሚ አረሮችን ተሸክሞ በጣም ረጅም ርቀት ለመጓዝ እንዲችል ደርጎ የተሠራ ተወንጫፊ የጦር መሳሪያ ነው።

እያንዳንዱ ሚሳዔል በአንድ ጊዜ በርካታ አረሮች ተሸካሚዎች ሊኖሩዋቸው የሚችሉ ሲሆን፣ እነዚህም የተለያዩ ዒላማዎችን ይመታሉ።

የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት አህጉር አቋራጭ ሚሳዔሎችን ለመሞከር የመጀመሪያዋ አገር ነበረች። ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1957 ነበር።

በአሁኑ ወቅት ከሩሲያ በተጨማሪ አሜሪካ እና ቻይና ከፍተኛ የመሬት ላይ አህጉር አቋራጭ ሚሳዔሎች አላቸው። ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ አነስተኛ ወይም የባሕር ሰርጓጅ ተለዋጮች አሏቸው።

የአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎቹ ከሌሎች የባለስቲክ ሚሳዔሎች በበለጠ ሰፊ ግዛትን ማቋረጥ የሚችሉ እንዲሁም ፍጥነት ያላቸው ናቸው።

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎች ምን ያህል ርቀት ይጓዛሉ?

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል በመደበኛነት 5500 ኪሎ ሜትር ርቀትን ቢሸፍንም አንዳንዶቹ ሚሳዔሎች ግን ከዚህ በበለጠ ርቀት ሊጓዙ ይችላሉ።

ሩሲያ ከሰሞኑ ያስወነጨፈችው ሚሳዔል የተተኮሰው ከደቡባዊ ኦስትራካን ግዛት እንደሆነ ይታመናል። የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል እስከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሊወነጨፍ የሚችል ሲሆን፣ ከዚህ ግዛት የሚተኮሱ ሚሳዔሎች እስከ አሜሪካ ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፍ ሊደርሱ የሚችሉ ናቸው።

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎች በምን ያህል ፍጥነት ይጓዛሉ?

ሩሲያ በዩክሬኗ ዲኒፕሮ ግዛት ላይ ባደረሰችው ጥቃት አርኤስ 26- ሩብዜህ የተሰኘ ሚሳዔል ተጠቅማለች የሚል ግምት አለ።

እነዚህ ሚሳዔሎች በሰዓት 24500 ኪሎ ሜትር ወይም በሰኮንድ 7 ኪሎ ሜትር ገደማ የመወንጨፍ ፍጥነት አላቸው።

ባለስቲክ ሚሳዔሎች በሮኬት ኃይል ወደላይ ተወንጭፈው ነው ዒላማቸውን የሚመቱት። ፍጥነታቸውን የሚያገኙትም ወደ ላይ የሚወነጨፉበት አካሄዳቸው ነው።

እነዚህ ባለስቲክ ሚሳዔሎች ያነሰ ፍጥነት ካላቸው ክሩዝ ሚሳዔሎች በበለጠ ለማክሸፍም ሆነ ለመቀልበሰ የበለጠ አዳጋች ያደርጋቸዋል።

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል
የምስሉ መግለጫ,አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎች የኒውክሌር ሚሳዔሎች ናቸው?

አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች የኒውክሌር ወይም መደበኛ የሆኑትን የሚታወቁ ዓይነት አረሮችን ሊሸከሙ ይችላሉ።

በዩክሬን ላይ የተወነጨፈው ባለስቲክ ሚሳዔል የኒውክሌር አረሮችን ተሸክመው ነበር የሚል አስተያየት እስካሁን አልተሰማም።

ባለስቲክ ሚሳዔሉ “ምንም ልዩነት ሳያደርግ ጥቃቶች” እንደፈጸመ የዩክሬን አየር ኃይል ቢገልጽም ስለደረሰው ጉዳት ሆነ የሰዎች ሞት ተከስቶ ስለመሆኑ መረጃ አልሰጠም።

አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔሎች ምን ያህል ያወጣሉ?

ሩሲያ ለአህጉር አቋራጭ ሚሳዔል መርሃ ግብሯ ምን ያህል እንደምታወጣ ባይታወቅም አሜሪካ ምን ያህል እንደምታወጣ መረጃዎች አሉ።

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን ሴንቲነል ለተሰኘው የአህጉር አቋራጭ ሚሳኤል መርሃ ግብሩ 140 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንዳጸደቀ በሐምሌ ወር አስታውቆ ነበር።

የአንድ ሴንቲነል አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ዋጋ 162 ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተዘግቧል። እነዚህ የጦር መሳሪያዎች በማንኛውም መለኪያ እንዲሁም ለየትኛውም አገር በጣም ውድ ናቸው።

ከተረጋገጠ፣ ሩሲያ ይህንን ሚሳዔል ለምን አሁን አስወነጨፈች?

ከአንድ ሺህ ቀናትን በላይ ያስቆጠረው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ ከመቀዛቀዝ ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፋፋመ ይገኛል።

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ለሩሲያ ወግነው በጦር ግንባሮች ላይ ተሰማርተዋል የሚሉ መረጃዎች በስፋት እየወጡ ነው። ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛቶች ዘልቃ በመግባት ወረራ ፈጽማለች።

በቅርቡም ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አትካምስ የተሰኘውን የአሜሪካ ረጅም ርቀት ሚሳዔል ዩክሬን በሩሲያ ውስጥ ለምትፈጽመው ጥቃት እንድትጠቀም ፈቅደዋል። የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ስቶርም ሻዶው ሚሳዔሎች የሩሲያን ድንበር ተሻግረው ተወንጭፈዋል።

ዩክሬን የሩሲያ ግዛቶችን ለመምታት የረጅም ርቀት ሚሳዔሎችን ለመጠቀም ከመረጠች ሩሲያ “ተገቢውን” ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታ ነበር።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ለመመለስ በዝግጅት ላይ እያሉ ነው ጦርነቱ በዚህ መልክ የተፋፈመው።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በ24 ሰዓታት ውስጥ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካደውን ጦርነት እንደሚያስቆሙ ቃል ቢገቡም ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል እስካሁን ግልጽ አልሆነም።

ነገር ግን ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ከሁለት ወራት ያነሰ በሆነው የሥልጣን ጊዜያቸው ለዩክሬን እስካሁን ያልፈቀዷቸውን የጦር መሳሪያዎች በመስጠት ጦርነቱን እንዲባባስ አደርገውታል።

ዩክሬን በአሜሪካ በተሰጣት የረጅም ርቀት ሚሳዔል ሩሲያን ስታጠቃ፣ ሩሲያ ደግሞ አህጉር አቋራጭ ነው የተባለውን ሚሳዔሏን በመጠቀም ጦርነቱ ከመባባስ አልፎ ሌላ ገጽታ ይዟል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከምትፈጽመው ጥቃት በተጨማሪ ለዩክሬን ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን የሚያስታጥቁ አገራትን ጭምር ዒላማ እንደምታደርግ እየዘተች መሆኑ ሌላ ስጋትን ፈጥሯል።