
25 ህዳር 2024, 13:12 EAT
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ህወሓት ያለበትን ውስጣዊ ችግር በመግባባት ፈትቶ እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥት ማሳሰቡን ተናገሩ።
የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት የውስጥ ችግሩን መፍታት ካልቻለ ግን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት እንደሚረከበው ማሳሰቡን ጨምረው ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንን የተናገሩት በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እሁድ፣ ህዳር 15/ 2017 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሲሆን የፌደራል መንግሥት ያሉት የትኛው መስሪያ ቤት ወይም ባለስልጣን ማሳሰቢያውን እንደሰጠ ግልጽ አላደረጉም።
በደብረ ጽዮን የሚመራው የህወሃት ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ንግግሮች ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም ሪፖርት ተደርጓል።
አቶ ጌታቸው በዚሁ መግለጫቸው በክልሉ ለሁለት የተከፈለው አንደኛውን ህወሓት የሚመሩት አካላት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቪላዊ አስተዳደሮች ላይ “መፈንቅለ መንግሥት” እየፈጸመ ነው ሲሉ በድጋሚ ወንጅለዋል።
ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ሲጠይቅ የቆየው የክልሉ ዋነኛ ፓርቲ ህወሓት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገና እንዲመዘገብ የተሰጠውን ውሳኔ ሳይቀበለው ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ በአመራሩ መካከል መከፋፈልን መፍጠሩ ይታወሳል።
በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና በጊዜያዊ አስተዳሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በሚመሩት ሁለቱ ቡድኖች መካከል ባለፉት ሳምንታት ተደጋጋሚ እርስ በርስ መካሰስ የተሰማ ሲሆን፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የመፈንቅለ ሥልጣን ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ያለ ቡድን አለ ሲል መግለጹ ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው “ስልጣን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት ነው ያላቸው” ያሏቸው የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ወደ ፌደራል መንግሥት በመመላለስ “ስልጣን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል” በማለት ከስሰዋል።
“ሦስት ጊዜ ወደ ፌደራል መንግሥት ሄደዋል፤ እንደዛ የሚባል ነገር የለም፤ አንድ ላይ ሆናችሁ መምጣት አለባችሁ ተብለዋል። ያካሄዱት ስብሰባም እንደ ጉባኤ አንቆጥረውም ተብለዋል” በማለት ድርጅቱ ችግሩ ውስጣዊ ድርድር በማድረግ እንዲፈታ እንደተነገረው ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው በሰጡት መግለጫ በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን በመግለጽ፣ ህወሓትን ለማዳን ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ጨምረውም የፌደራል መንግሥቱ ህወሓት የውስጥ ችግሩን እንዲፈታ ጥሪ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ ካልሆነ ግን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥት እንደሚረከበው ማሳሰቡን ተናግረዋል።
ፓርቲው፣ በንግግር ችግሩን መፍታት ካልቻለ ግን፣ በክልሉ የሚገኘው መንግሥታዊ ስልጣን “የፌዴራል መንግሥት ይይዘዋል ተብሎ ተነግሯቸዋል፤ ምክንያቱም የፕሪቶሪያ ስምምነት ስልጣን ለህወሓት ብቻ አይልም።” ብለዋል።
በህወሓት ሊቀ መንበር እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት መካከል ያለው አለመግባባት ባለፉት ወራት እየተባባሰ በመሄድ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የአስተዳደር እርከኖች ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሶ ነበር።
በደብረጽዮን የሚመራው ቡድንም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ የተለያዩ ክሶችን ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ ሁለቱም ወገኖች የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከየትኛው ሳይወግን ገለልተኛ እንዲሆን ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በህወሓት ሊቀመንበር የሚመራው ቡድን የፀጥታ ኃይሉን ስም እያጠፋ መሆኑን በመጥቀስ ይህ አካሄድ “አደገኛ” ነው ሲሉ አሳስበዋል።
- አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ምንድን ነው?25 ህዳር 2024
- “ከእናንተ ቀድመን የገና በዓልን እናውቃለን” – አወዛጋቢው ለ77ቱ ረሃብ የተለቀቀው ዘፈን24 ህዳር 2024
- ሱዳን የከሸፈች አገር የመሆን ስጋት ላይ ናት ሲሉ የረድዔት ኃላፊ አስጠነቀቁ25 ህዳር 2024
አቶ ጌታቸው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ወራት ከ28 ኩንታል በላይ ወርቅ ከትግራይ ክልል ወደ ፌደራል መንግሥት መግባቱን፤ ሆኖም ከክልሉ ወደ መንግሥት የገባ ገንዘብ አለመኖሩን ተናግረዋል።
“ባለፉት ሦስት ወራት ከሁለት ሳምንት ከ28 ኩንታል በላይ ወርቅ ወደ ፌደራል ገብቷል። ይህ በኮንትሮባንድ የወጣውን አይጨምርም። ከዚህ ግን መንግስት አንድም ሳንቲም አላገኘም። ምክንያቱ በዚህ ጉዳይ የተሰማራ ሰፊ የኮንትሮባንድ ኃይል ስላለ” ሲሉ ተናገረዋል።
በዚህ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ፣ በትግራይ ኃይሎች ስር የሚገኙ ግለሰቦች፣ የጸጥታ ኃይሎች ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በሲቪላዊ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ባላስልጣናት እንደሚሳተፉበት ገልጸዋል።
“ይህን የሚከታተል ግብረ ሃይል አቋቋምን፤ ግን ስራው እንዳይሰራ ብዙ መስተጓጎል ይገጥመዋል። በሕገ-ወጥ የማዕድንና የሰው ዝውውር የሚጠረጠሩ ሰዎች አቃቤ ሕግና ዳኞችን ያስፈራራሉ፤ ድርጅቱን እናድናለን እያሉ የሚፎክሩ ኃላፊዎች ሳይቀር በወርቅ የኮንትሮባንድ ንግድ እጃቸው አለበት” ሲሉ ወንጅለዋል።
በተጨማሪ ወርቁን ለማውጣት ጥቅም ላይ በሚውሉ አደገኛ ባሏቸው ኬሚካሎች ምክንያት በተፈጥሮ ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ ከትግራይ ወደ ማዕከላዊው ባንክ ሲገባ የነበረው ወርቅ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወርቅ በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ እየወጣ መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው መቀለ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ላይ የክልሉ የወርቅ ማዕድን በከፍተኛ መጠን እየተዘረፈ መሆኑን እና በተፈጥሮ ሀብትም ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህ ሕገወጥ የወርቅ ማውጣት እና ማዘዋወር ተግባር በማን እንደሚካሄድ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደራቸው ከፖሊስ፣ ከደኅንነት እና ከፍትህ አካላት ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በሰሜን ምዕራብ የትግራይ አካባቢ የሚወጣው የወርቅ ማዕድንን በተመለከተ አስካሁን ግልጽ ያለ መረጃ ባይኖርም ወርቅ እየወጣ በተለያዩ መንገዶች ከኢትዮጵያ ውጪ እንደሚሄድ ይነገራል።
በዚህ የውጭ ዜጎች ጭምር እንደተሰማሩበት በሚነገረው የወርቅ ማውጣት ተግባር ውስጥ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር አለመግባባት ውስጥ የሚገኙ የህወሓት አመራሮች እንዳሉበት ቢገለጽም ከክልሉ አስተዳደር በኩል በይፋ የወጣ መረጃ የለም።
በተያያዘ ደም አፋሳሹን ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው በትግራይ ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ሥራ ባለፈው ሳምንት መጀመሩ ይታወሳል።
ይህንን በተመለከተ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት በመጀመሪያው ዙር ትጥቅ የሚፈቱ፣ ከሠራዊቱ የሚሰናበቱ እና የሚቋቋሙ 75 ሺህ ተዋጊዎች መሆናቸውን እና ሂደቱን በተመለከተ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ ገልጸዋል።