
26 ህዳር 2024
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በጨበጡ በመጀመሪያ ቀናቸው ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲ ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ ይህን የሚያደርጉት በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሰዎችን ለመግታት እና የአደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከል እንደሆነ ተናግረዋል።
በአውሮፓውያኑ ጥር 20 ሥራቸውን የሚጀምሩት ትራምፕ በመጀመሪያው ቀናቸው ከካናዳ እና ሜክሲኮ የሚገቡ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የሚጭን ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ አስታውቋል።
የተሰናባቹ ፕሬዝደንት ባይደን አስተዳደር ፌንታኒል የተባለውን ዕፅ ለመሥራት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንድታቆም ቻይናን መማፀኑ ይታወሳል።
ዋሺንግተን እንደምትለው ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ በፌንታኒል ምክንያት 75 ሺህ አሜሪካዊያን ሞተዋል።
ካናዳ እና ሜክሲኮ በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን እስኪያስቆሙ እንዲሁም ፌንታኒል የተባለው ዕፅ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ እስኪያግዱ ድረስ ታሪፍ ተጥሎባቸው ይቆያል።
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚድያቸው ነው ይህን ያስታወቁት።ነ “ሜክሲኮ እና ካናዳ ይህን ሥር የሰደደ ችግር የመቅረፍ ኃይል አላቸው” ብለዋል።
“አሁን ጊዜው እነሱ ከባድ ዋጋ የሚከፍሉበት ነው!”
- አቶ ጌታቸው ረዳ፡‘ህወሓት ችግሩን መፍታት ካልቻለ ሥልጣኑን የፌዴራል መንግሥት ይረከበዋል’25 ህዳር 2024
- ኳታር እስራኤል እና ሐማስን ማሸማገል ለምን ተሳናት?26 ህዳር 2024
- ሰሜን ኮሪያውያን ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው ከሩሲያ ጋር መዋጋት ለምን ፈልጉ?26 ህዳር 2024
ትራምፕ የቤይጂንግ ባለሥልጣናትንም ወርፈዋል። እሳቸው እንደሚሉት የቻይና ባለሥልጣናት ፌንታኒል የተባለውን ዕፅ የሚያመርቱ ሰዎች በሞት ለመቅጣት ቃል ገብተው ነበር።
በዋሺንግተን የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ “ቻይና ሆን ብላ ፌንታኒል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲገባ እያስደረገች ነው የሚለው ሐሳብ በፍፁም ውሀ የሚያነሳ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ቻይና የምታምነው የቻይና-አሜሪካ ምጣኔ ሀብታዊ እና የንግድ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ ነው። በንግድ ጦርነት አሊያም በታሪፍ ጦርነት ማንም አያተርፍም” ብለዋል።
ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ እጥላለሁ በማለት ሲያስፈራሩ ተሰምተዋል።
አክለው ቻይና ከእንግዲህ በኋላ በንግዱ ዘርፍ ከአሜሪካ ልዩ ስፍራ የሚሰጣት ሀገር አትሆንም ሲሉ ለቻይና የሚሰጠው ቦታ እንደሚቀንስ ጠቆም አድርገው ነበር።
የቻይና ምጣኔ ሀብት በተለያዩ ምክንያቶች እየተንገዳገደ ባለበት ወቅት ነው አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ታሪክ ለመጫን ቃል የገባው።
የንብረት ገበያ መዳከም፣ የሀገር ውስጥ የመግዛት አቅም መቀነስ እና መንግሥት ከሀገር ውስጥ የወሰደው ብድር መጨመር የቻይናን ምጣኔ ሀብት እየተፈታተኑት ይገኛሉ።
አዲሱ የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ዩኤስ-ሜክሲኮ-ካናዳ የገቡትን ዩኤስኤምሲኤ የተባለ ስምምነት የሚሽር ነው።
ይህ ትራምፕ የፈረሙት ስምምነት ወደ ተግባር የገባው በአውሮፓውያኑ 2020 ሲሆን ሶስቱ ሀገራት በመካከላቸው ነፃ የሆነ ንግድ እንዲያደርጉ የሚያግዝ ነው።
ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ቃል ከገቡ በኋላ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር በንግድ እና የድንበር ጉዳዮች በስልክ ማውራታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ትራምፕ ሶስቱ ሀገራት ላይ ታሪፍ ጨመሩ ማለት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል ማለት ነው።