የሊባኖስ ጦር የተኩስ አቁም በተደረገበት አካባቢ ይሰማራል

26 ህዳር 2024, 08:03 EAT

እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የተቃረቡ ሲሆን የእስራኤል ካቢኔ በጉዳዩ ዙሪያ ለመወያየት ማክሰኞ እንደሚገናኝ የእስራኤል እና የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው የሊባኖስ ሚሊሻ መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ቀርቧል።

የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ መውጣት እና ሔዝቦላህ በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ ማቆምን ይጨምራል ተብሏል።

“የተቀራረብነት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለን እናምናለን። ነገር ግን እስካሁን ፍጻሜው ላይ አልደረስንም” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።

አሜሪካ እና የረዥም ጊዜ የሊባኖስ አጋር የሆነችው ፈረንሳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጥረት አድርገዋል።

ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ሁለቱ ወገኖች የስምምነቱ የመጨረሻ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በሚነጋገሩበት ወቅት በእስራኤል እና በሔዝቦላ መካከል የተኩስ ልውውጡ እየተባባሰ መጥቷል።

እሑድ ዕለት ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ወደ 250 የሚጠጉ ሚሳዔሎች የተተኮሱ ሲሆን አብዛኞቹ እንዲከሽፉ ሆነዋል። የእስራኤል አየር ኃይል በቤሩት እና በሌሎች ቦታዎች በሚገኙ የሔዝቦላህ ይዞታዎች እና የጦር መሳሪያ ማከማቻዎች ላይ የአየር ድብደባ ማድረጉን ቀጥሏል።

ስምምነቱ በእስራኤል እና በሔዝቦላህ በሚለቀቁ አካባቢዎች የሊባኖስ ጦር መሰማራትን ይጨምራል ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዲፕሎማት ተናግረዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስምምነቱን “በመርህ ደረጃ” መቀበላቸው የተነገረ ሲሆን የሊባኖስ ፓርላማ ምክትል አፈ-ጉባዔ ኤሊያስ ቡ ሳብ በበኩላቸው አሁን የተኩስ አቁሙን በተመለከተ ምንም አይነት ከባድ እንቅፋት የለም ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የእርቁን ስምምነት የሚከታተለው ማን ይሆናል የሚለው ትልቁ አንገብጋቢ ጥያቄ መፍትሔ አግኝቷል ብለዋል። በዚህም በአሜሪካ የሚመራ እና ፈረንሳይን ጨምሮ አምስት አገራትን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ሔዝቦላህ ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ ወደ ሚገኘው ደቡብ ሊባኖስ እየተመለሰ ነው ብሎ ካመነ ወይም በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ ነው ብሎ ካመነች ወደ ሊባኖስ የመመለስ እና ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ መብቷን ለማስጠበቅ እስራኤል መጠየቋም ስምምነቱን እንዳጓተተው ታውቋል።

የአሜሪካው ልዑክ አሞስ ሆችስታይን ግን ወደ ሁለቱ አገራት በመሄድ በዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የጊዜ ገደብ እንዳለ በግልጽ መናገራቸው ይታመናል።

በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሃይል (ዩኒፊል) እና የሊባኖስ ጦር ከነበራቸው ድክመት አንጻር የተኩስ አቁም እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ስጋት የተቀረፈ ይመስላል።

እዚህ ጋር ግን የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ይነሳል። ቀን አክራሪው የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጊቪር የተኩስ አቁም ስምምነትን በመቃወም “ከባድ ስህተት” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈው ነበር። ሔዝቦላህ በወታደራዊ ኃይል በመዳከሙ ቡድኑን ለማጥፋት ይህ “ታሪካዊ ዕድል” ነው ብለዋል።

ሔዝቦላህ በጋዛ የሚገኘው ሐማስን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን በመተኮሱ ፍጥጫው የጀመረው ባለፈው ዓመት መስከረም 27 ነበር።

በመስከረም ወር በተጠናከረው እና ከሔዝቦላህ ጋር በምታደርገው ጦርነት 60 ሺህ የሚጠጉ እና በቡድኑ ጥቃት ምክንያት ከሰሜናዊ እስራኤል የሸሹ ነዋሪዎችን መመለስ መሆኑን ቴል አቪቭ አስታውቃለች።

ቀጥሎም ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመሰንዘር ብዙ መሠረተ ልማቶቹን እና የጦር መሳሪያዎቹን ከማውደም በተጨማሪ መሪውን ሃሰን ነስረላህን እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን ገድላለች።

የሊባኖስ ባለስልጣናት እንደተናገሩት ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት በ2006 በሔዝቦላ እና በእስራኤል መካከል የነበረውን ጦርነት ባቆመው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1701 ውሎች ብቻ መገደብ አለበት።

እስራኤል ውሳኔው ሙሉ በሙሉ አልተከበረም ስትል ሊባኖስ በበኩሏ በግዛቷ ላይ ወታደራዊ በረራዎችን ጭምር በማድረግ እስራኤል ጥሰት ፈጽማለች ስትል ትናገራለች።

እአአ ከጥቅምት 2023 ወዲህ ሊባኖስ ውስጥ ከ 3 ሺህ 750 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ቢያንስ 15 ሺህ 600 ሲቆስሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከቤታቸውን መፈናቀላቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በሔዝቦላህ እሑድ ባደረሰው ጥቃት በሰሜን እና በመካከለኛው እስራኤል በርካታ ሰዎች ሲቆስሉ ህንጻዎች ተጎድተዋል። የተወሰኑት ጥቃቶች የተፈጸሙት በቴል አቪቭ አቅራቢያ መሆናቸውን የእስራኤል ፖሊስ አስታውቋል።

እስራኤል ቅዳሜ ዕለት በማዕከላዊ ቤይሩት ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 29 ሰዎች መሞታቸውን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሰኞ ዕለት በተፈጸመ የእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 31 ሰዎች መሞታቸውን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደነገረው ገልጾ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ከሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው እና በደቡብ ቤሩት ህንጻዎች ላይ በርካታ ጥቃቶችን መፈጸሟን እስራኤል አስታውቃለች።