
26 ህዳር 2024
በጋዛ በሚፈጸመው የማያባራ ጥቃት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ጋብ እንዲል ያስቻለውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ባለፈው ዓመት እንዲደረስ ያስቻለችው ኳታር የማሸማገል ጥረቷን እንዳቆመች አስታውቃለች።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እያሸማገለ የነበረው የኳታር መንግሥት ሁለቱም አካላት ለመደራደር ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ጥረቱን አቁሜያለሁ ብሏል።
በተጨማሪም በአገሪቱ የሚገኘውን የሐማስ ቢሮ እንዲዘጋ ከአሜሪካ ጫና እየመጣ ነው ተብሏል።
ትንሿ እና በሀብት የበለጸገችው ኳታር በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ለራሷ ሰላም የማምጣት ሚናን ሰጥታ ስትሠራ የቆየች ሲሆን፣ ነገር ግን አሁን ባለው የጋዛ ጦርነት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ማድረግ ተስኗታል።
ኳታር ዋነኛ የሰላም አደራዳሪ እንዴት ሆነች?
ኳታር በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የምትገኝ ትንሽ አገር ናት።
ስፋቷ 11 ሺህ 600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቢሆንም በዓለማችን ከፍተኛ መጠን ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ በመላክ በቁንጮነት ከተቀመጡት አንዷ ናት።
በነፍስ ወከፍ ገቢም በዓለም በስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የኳታር መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን የማምጣት ሚናን ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ በተለያዩ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነቶችን በማምጣት የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል።
- ኳታር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የነበራትን የሽምግልና ሚና አቋረጠች10 ህዳር 2024
- ሐማስ ትልቅ ተስፋ በተጣለበት የዶሃ የሰላም ስምምነት አልሳተፍም አለ15 ነሐሴ 2024
- ኳታር በእስራኤል እና ሐማስ በሚደረገው ድርድር የአሸማጋይነት ሚናዬን እያጤንኩ ነው አለች18 ሚያዚያ 2024
ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያስቻለ ሲሆን፣ በዚህም 105 የእስራኤል ታጋቾች እና በእስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ 240 ፍልስጤማውያን ልውውጥ ተደርጓል።
ይህ ሐማስ እና እስራኤልን የማደራደሩ ተግባር ለኳታር አዲስ አይደለም።
ኳታር ከዚህ ቀደም ጊዜያዊ የታሊባን ኤምባሲ በዶሃ እንዲከፍት ፈቅዳ ነበር።
አሜሪካ ከታሊባን ጋር መደራደሪያ መስኮት ማግኘት የቻለችውም በዚሁ ቢሮ አማካኝነት ነው።
በዚህም ኳታር በአፍጋኒስታን ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የታሊባን እና የአሜሪካ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 2020 እንዲቋጭ አስችላለች።
በስምምነቱም መሠረት አሜሪካ እና አጋሮቿ ከአፍጋኒስታን ኃይላቸውን ሲያስወጡ ታሊባን ሥልጣን ተቆጣጠረ።
ኳታር የደኅንነት ቁልፍ ሰዎቿን በመጠቀም በኢራቅ እና በሶሪያ አይሲስ (እስላማዊ መንግሥት) ያገታቸውን ምዕራባውያን ለማስለቀቅ ቁልፍ ሚና ነበራት።
ኳታር ባለፈው ዓመት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በተደረገው የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት ላይ ዋነኛ ሸምጋይ ነበረች።
በዚሁ ዓመት ኳታር አራት ዩክሬናውያን ሕጻናት ለአገራቸው እንዲበቁ አድርጋለች። ልጆቹ በሩሲያ ታግተው የነበሩ እንደሆኑ ነው የተነገረው። ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በቀጥታ መነጋገር ስለማትችል ውክልናውን የሰጠችው ለኳታር ነበር።
በአፍሪካ ውስጥ በቻድ መንግሥት እና በ40 ተቃዋሚዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አድርጋለች። በአውሮፓውያኑ 2010 በሱዳን መንግሥት እና በዳርፉር ግዛት ያሉ ታጣቂዎች ተደራድረው ወደ ሰላም እንደሚጡም አስችላለች።
እነዚህ እና ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ኳታር ቁልፍ የማደራደር ሚና እንዳላት የሚመሰክሩ ናቸው።

ኳታር ሰላም የማስፈን ሚናን ለምን ወሰደች?
የኳታር መንግሥት የአገሪቱን ሰላም የማስፈን ሚናን በሕገ መንግሥቱ አስፍሯል።
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 7 እንደሚያትተው “የመንግሥት የውጭ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በማበረታታት ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነትን በማጠናከር መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው” ይላል።
ኳታር በዓለም ላይ ለየት ያለ ሚናን ትጫወታለች። በጠላትነት የሚተያዩ አገራት ወዳጅ እና አጋር ናት።
ከአረብ አገራት ለምዕራባውያን ቅርብ አጋር እንደ ኳታር ያለ ብዙም የለም። ኳታር ዋነኛ የምዕራባውያን አጋር ከመሆን በተጨማሪ የአሜሪካ ጦር ሰፈርም ይገኝባታል። በተቃራኒው ምዕራባውያኑ አሸባሪዎች ለሚሏቸው ታሊባን እና ሐማስ ቢሮ እንዲከፍቱ በመፍቀድ መቀመጫ ሰጥታቸዋለች።
ይህም በቀጥታ እርስ በርስ መነጋገር በማይችሉ የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል እንደ ድልድይ ሆና መሥራት እንዳስቻላት በዩናይትድ ኪንግደም መቀመጫውን ያደረገው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ የተሰኘ የጥናት ተቋም ባልደረባ ዶክተር ኤችኤ ሄልየር ይናገራሉ።
“ኳታር እንደ ታሊባን እና ሐማስ ያሉ ቡድኖች ጋር ለመገናኘት ተመራጭ አገር ናት። ምክንያቱም ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ግጭት ውስጥ ገብታ አታውቅም” ይላሉ።
አክለውም “በአገሪቷ የአሜሪካ የጦር ሰፈር መገኘት ለእነዚህ ቡድኖች ተወካዮች ደኅንነት እንዲሰማቸው ያደርጋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
“ከግድያ ሙከራዎች ነጻ ሆነው በደኅንነት መደራደር እንደሚችሉ ይሰማቸዋል” በማለት ነው ዶክተር ሄልየር የሚገልጹት።
“ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ውጤት የሚያመጣ ተደራዳሪ ሆኖ መታየት የአገሪቱ የገጽታ አካል ነው” ሲሉ በዩናይትድ ኪንግደም የዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ጥናት የሚያደርገው ቻታም ሐውስ ባልደረባ ዶክተር ሳናም ቫኪል ይገልጻሉ።
“የሰላም አደራዳሪ መሆኗ ኳታርን ለአሜሪካ ጠቃሚ ያደርጋታል፤ በዚህም በምዕራባውያኑ ዋነኛ ስፍራ እንዲሰጣት ሆኗል” ይላሉ ዶክተር ሳናም።
በተጨማሪ “በዙሪያዋ ያለውን ቀጣናም የተረጋጋ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ያደርገዋል።”
ኳታር የሰላም ድርድሮች ሲካሄዱ የሚያሸማግሉ እና የሚቆጣጠሩ በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ ዲፕሎማቶች እንዳሏት ነው ዶክተር ሳናም የሚያስረዱት።
ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ተፋላሚ ቡድኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ወይም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ያልቻሉባቸው አጋጣሚዎችም አሉ።
ኳታር የጋዛው ጦርነት እንዲቋጭ ማድረግ ለምን ከበዳት?
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እያደረገ የነበረውን ጥረት ማቋረጡን አስታውቋል። ነገር ግን በዶሃ የሚገኘው የሐማስ ቢሮ እንደሚዘጋ የወጡ ሪፖርቶችን ውድቅ አድርጓል።
የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ ለአሸባሪ ቡድን መጠለያ በመስጠት ለሐማስ ድጋፍ ትሰጣለች ሲል ወቅሷል።
ነገር ግን ዶክተር ሄልየር “የኳታር መንግሥት የሐማስ አመራሮች ቢሯቸውን ከደማስቆስ ወደ ዶሃ እንዲያደርጉ የጋበዘው ከሶሪያ መንግሥት ጋር ጥል ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ነው። የኳታር አመራሮች ይህንን ሲያደርጉም ከአሜሪካውያን ጋር ምናልባትም ከእስራኤል ጋር በመተባበር ነው” ይላሉ።
ባለፉት ግጭቶች ኳታር እስራኤል እና ሐማስ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነቶች እንዲደርሱ አስችላለች፤ “በዚያን ወቅት ሁለቱም ወገኖች ሁኔታዎች ወደ ቀደመ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ፍላጎት ነበራቸው” ይላሉ።
“የአሁኑ የተለየ ነው” የሚሉት ዶክተር ቫኪል ለዚህም “የእስራኤል መንግሥት ሰላምን ከሚፈልገው በላይ ለደኅንነቱ ዋስትናን ማረጋገጥ ይፈልጋል። ጦርነቱን መቀጠል ይህንን ዓላማውን እንደሚያሳካ ያስባል። ሐማስ በበኩሉ ህልውናው እንዲቀጥል ሰላም ይፈልጋል” ብለዋል።
ሐማስ ቢሮውን ከኳታር ወደ ቱርክ ወይም ኢራን ሊያዛውር ይችላል የሚሉ መላምቶች እየተሰጡ ነው።
ዶክተር ሄልየር በበኩላቸው ይህ ሊሆን የማይችልበትን ሁኔታ ሲያስረዱ ኳታር ለመሪዎቹ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ እንደሆነ በመጥቀስ ነው።
“እስማኤል ሃኒያ [የቀድሞ የሐማስ የፖለቲካ መሪ] ከዶሃ ወደ ኢራን በሄደበት ወቅት በፍጥነት ነው በእስራኤል የተገደለው” ብለዋል።