
26 ህዳር 2024
በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የሰሜን ኮሪያውያን ኮብላዮች ድፍረት የተሞላበት እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታውቅ ተልዕኮ ለመወጣት ሐሳብ እያቀረቡ ነው። ሐሳባቸው ከተሳካ የዩክሬንን ጦር በመደገፍ ወደ ግንባር ተጉዘው በሩሲያ በኩል የተሰለፉትን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ለማስኮብለል ነው ትኩረታቸው።
የሰሜን ኮሪያን ጦር አስተሳሰብ እና አረዳድ በተመለከተ ልዩ ግንዛቤ አለን ይላሉ። ይህ ደግሞ “በክብር” ለመሞት ዝግጁ ሆነው የሠለጠኑትን ወታደሮች ለማሳመን በሚገባ ዝግጁ ያደርገናል ሲሉ ይከራከራሉ።
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ዩክሬን ውስጥ የሚዋጉ 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ማሰማራቷ እየተነገረ ነው። ይህ ነው እንግዲህ ሸሽተው ደቡብ ኮሪያ የደረሱትን ሰሜን ኮሪያውያንኑን ያነሳሳው።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ገንዘብ ለማግኘት እና ወታደራዊ ቴክኖሎጂያቸውን ለማዘመን የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ብዙዎች ያስባሉ። እያንዳንዱ ወታደር በየወሩ 2 ሺህ ዶላር ሊያገኝ እንደሚችል የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ገምቷል። ይህ ለሰሜን ኮሪያ ትልቅ ሚባል ገንዘብ ነው።
የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እአአ በ1970ዎቹ በቬትናም ጦርነት ተሳትፈዋል። ከዚያ ወዲህ በዩክሬን መሰማራታቸው መዘገቡ በዘመናዊ ጦርነት ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ያደርገዋል።
ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ከ1950 እስከ 1953 ድረስ የዘለቀው የኮሪያ ጦርነት ካበቃ በኋላ ጦርነት ውስጥ ያሉ በሚመለስል መልኩ ኖረዋል። ደቡብ ኮሪያ በአሜሪካ፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በቻይና በመደገፍ ዛሬ ነገ ፈነዳ በሚያስብል ውጥረት ውስጥ እንደገቡ እየኖሩ ነው።
ከ70 ዓመታት በፊት የኮሪያ ልሳነ ምድር ለሁለት ከተከፈለ በኋላ ወደ 34 ሺህ የሚገመቱ ሰሜን ኮሪያውያን ወደ ደቡብ ሸሽተው ገብተዋል።
ወደ ተግባር መለወጥ
የደቡብ ኮሪያ ክርስቲያን ወታደሮች ማኅበር እና የሰሜን ኮሪያ የሸሹ ከፍተኛ የጦር አባላት ማኅበር የተሰኙ እና ከሰሜን ኮሪያ ከድተው በወጡ ሰዎች የተቋቋሙ ሁለት የሲቪክ ቡድኖች ይገኛሉ። የሰሜን ኮሪያን “ኢሰብዓዊ ባህሪ” በማውገዝ የጋራ መግለጫ አውጥተው ወደ ዩክሬን መሄድ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
“የኪም ጆንግ ኡን አገዛዝ የሕዝብ ልጆችን ወደ ጦርነት በመላክ ለአገዛዙ ገንዘብ ለማስገኘት እና ጦሩን ለማዘመን የሚያደርገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን” ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ የክርስቲያን ወታደሮች ማኅበር መሪ የነበሩት ሲም ጁ-ኢል ለተልዕኮው ፍጥነት እንደሚፈልግ ያምናሉ።
“[የተላኩት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች] በሰሜን ኮሪያ በተሰጣቸው ትምህርት ምክንያት በቅዠት ውስጥ ሆነው ‘የእኔ ሞት የክቡር ነው’ ብለው በማመን ሊዋጉ ይችላሉ። [ይህ እንዳልሆነ] እንዲገነዘቡ ማድረግ አለብን” ብለዋል።
“ወደ ጦር ግንባር ከሄድኩ ከሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ጠመንጃ እና ጥይቶችን ጋር እጋፈጣለሁ። ትኩረቴ ግን ስለጦርነቱ እውነታ በማስተማር ላይ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

ስትራቴጂዎች
የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ለማግኘት የሚያስችሉ የተለያዩ ዘዴዎችን አቅርበዋል። በድሮን በሚጣሉ በራሪ ወረቀቶች፣ በሜጋፎን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች የሥነ ልቦና ጦርነት የመፍጠር ሃሳብን አቅርበዋል።
“በራሪ ወረቀቶችን [የፕሮፓጋንዳ ቁሳቁሶችን] ለመበተን ድሮኖችን እና እንደ ዩቲዩብ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን እንጠቀማለን። ወደ ጦር ግንባር መቅረብ ከቻልን ደግሞ ሜጋፎን በመጠቀም ሥነ ልቦናዊ ጦርነት ልናካሂድ እንችላለን” ሲሉ ዎርልድ ኢንስቲቲዩት ፎር ኖርዝ ኮሪያን ስተዲስ እና የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ የጦር አባላት መሪ የሆኑት ዶ/ር አህን ቻን-ኢል ተናግረዋል።
በአንድ ወቅት በሰሜን ኮሪያ ሲቪል መከላከያ ውስጥ ያገለገሉት ዶ/ር አህን፤ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነውን ስቶርም ኮርፕስ የተባለው የሰሜን ኮሪያ ልዩ ኃይል መሳተፉ ያሳስባቸዋል።
“ሁለት ወይም ሦስት የሰሜን ኮሪያ ጦር (ወደ ሩሲያ) ከተላከ በእርግጠኝነት የምንሠራው ሥራ ይኖረናል። የመግለጫው የወጣበት ምክንያትም ይኼው ነው” ብለዋል።
ወደ ዩክሬን የዘመቱ ወታደሮች እንዲሸሹ ለማድረግ አንዳንድ ከድተው በሸሹ የቀድሞ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በቅርቡ አንድ ድርጅት ማቋቋሟቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከግንባር ለማምለጥ መመሪያ የሚሰጡ በራሪ ወረቀቶችን እና የድምጽ ፋይሎችን ለዩክሬን ኃይሎች ማድረስን የሚያጠቃልሉ ስልቶችን አዘጋጅተዋል።
- ቭላድሚር ፑቲን በሚሊዮን በርሜል የሚቆጠር ነዳጅ ለሰሜን ኮሪያ ሰጡ22 ህዳር 2024
- ለሩሲያ የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡት አገራት እነማን ናቸው?17 ጥቅምት 2024
- አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳዔል ምንድን ነው?25 ህዳር 2024
ተግዳሮቶች
ተግባራዊነት እና ዲፕሎማሲያዊ መሰናክሎች እነዚህን ዕቅዶች ሊያወሳስቡ ይችላሉ። የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዩክሬን ላይ የጉዞ እገዳ ጥሏል። ይህንን ሕግ የጣሱ ሰዎች እስከ አንድ ዓመት እስር ወይም እስከ 7 ሺህ ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
ሰሜን ኮሪያዎቹ ኮብላዮች ወደ ዩክሬን ከተላኩ ፒዮንግያንግ እና ሞስኮን ሊያበሳጭ ከመቻሉም በላይ የቀጠናው ፀጥታ እንዳይረጋጋ ያደርጋል የሚል ስጋትም አለ።
“‘ሄደን እንዋጋለን’ ብሎ ማወጅ ጥሩ ቢሆንም፤ ነገር ግን በውጭ ግንኙነት ረገድ ወታደሮችን መላክ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ሲሉ የሰሜን ኮሪያ ቡድን ኃላፊ ሊ ሚን ቦክ ተናግረዋል።
ሌሎች ደግሞ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን እንዲከዱ የማሳመኑን አዋጭነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።
የሰሜን ኮሪያ ልዩ ኃይል የሆነው የስቶርም ኮርፕስ የቀድሞ አባል የሆኑት ሊ ዎንግ-ጊል እንዲህ ያሉት ነገሮች መዘዝ ሊኖራቸው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “እንዲከዱ ለመንገር ከሞከርክ ጭንቅላትህን በጥይት ይመቱታት” ብለዋል።
በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ አንዳንድ የኮበለሉ ሰዎች ስለ ሰሜን ኮሪያ ጦር አሁናዊ ዕውቀት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል።
የሰሜን ኮሪያ የክርስቲያን ወታደሮች ማኅበር አባል የሆኑት ሲምም በሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ውስጥ ያለውን ታማኝነት መስበር ያለውን ፈተና ይገነዘባሉ።
“ኪም ጆንግ ኡን ሰዎች ‘የሰሜን ኮሪያ ጦር ቀልድ አይደለም’ እንዲሉ ይፈልጋል” ብለዋል።
“የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን ለማዝመት ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ብቻ ታቀዶ የተሠራ ነውን? ከሩሲያ ጋር አቅደው እና አሠልጥነው የተዘጋጁበት ነው” ብለዋል።
“[የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች] በጀግንነት በመታገል ለመሪው እና ለፓርቲው ለመሞት ቆራጥ እና ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ገንዘብ እና ምግብ የሌላቸውን ሰዎች ሰብስበን እንደመላክ መታሰብ የለበትም።”
የኮሪያ የመከላከያ ትንተና ኢንስቲትዩት ባልደረባው ዶ/ር ዱ ጂን-ሆ እንደሚሉት ከሆነ የድምጽ ማጉያ መግጠም በጣም አደገኛ ነው። “[የፀረ ሰሜን ኮሪያ ድምጹ] ሲከፈት በድሮኖች ይመታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቀድሞ የስቶርም ኮርፕ አባል ሊ ዉንግ-ጊል አነስ ያሉ ቀጥተኛ የመገናኛ ዘዴዎችን ስለመጠቀም ሃሳብ ያቀርባሉ።
በቀጥታ ከመገናኘት ይልቅ የቪዲዮ ወይም የድምጽ መልዕክቶች የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ።
“ወደዚህ [ወደ ደቡብ ኮሪያ] የመጡ እና እንደዚህ በደስታ የሚኖሩ የሰሜን ኮሪያ ኮብላዮችን የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎችን መላክ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል።”
ሊ አክለውም የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች እንደዚህ ዓይነት መልዕክት ለማግኘት ሊቸገሩ ስለሚችሉ ቪዲዮ እና ድምጽ የተጫነባቸው የኤምፒ3 ማጫወቻዎችን ወይም የቆዩ ሞባይል ስልኮችን መላክን እንዳሀሳብ አቅርበዋል ።

የመቋቋም ብቃት
እነዚህ አደጋዎች እና ጥርጣሬዎች ቢኖሩም ግን ኮብላዮቹ በተልዕኳቸው ጸንተዋል።
“እኛ [ኮብላዮች] ትክክል ነው ብለን የምናምንበትን ነገር የምናደርግ ሰዎች ነን። የሕይወታችንን የመጨረሻ ቀናት በዚህ መንገድ አስተዋጽኦ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው” ብለዋል ሊ።
የኮብላዮቹ ዕቅዶች ውይይት እየተደረገበት ቢሆንም የዩክሬን መንግሥት አስቀድሞ እርምጃ ወስዷል።
ኤ ዎርድ ቶ ዘ ሶልጀርስ ኦፍ ዘ ኮሪያን ፒፕልስ አርሚ [ለሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የተላከ መለዕክት] በሚል በሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ እንደ ዩቲዩብ እና ቴሌግራም ባሉ መድረኮች ለቋል።
የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ እና የውህደት ሚኒስቴሮች የሰሜን ኮሪያ ኮብላዮች ወደ ዩክሬን ለመጓዝ በማቀዳቸው ላይ “ምንም አቋም የለንም” ብለዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ሄርሂ ታይኪይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የሰሜን ኮሪያ ኮብላዮችን “ለመቀበል” እና እነሱንም “ዓለም አቀፍ ጦር” እንዲቀላቀሉ አበረታተዋል።
“እነሱን ዩክሬን ውስጥ በማግኘታችን እና ከእነሱ ጋር በመተባበር ደስተኞች ነን። ስለሰሜን ኮሪያ ኃይሎች ያላቸው ዕውቀት፣ ቋንቋ እና ስለማንነታቸው ያላቸው ግንዛቤ ለእኛ በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
“[የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር] ፑቲን በዩክሬን ላይ በከፈቱት ጦርነት ውስጥ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሳተፍ ምላሽን የሚጠይቅ ከባድ ዓለም አቀፍ ስጋት ይፈጥራል” ሲሉ አክለዋል።