ባለስቲክ ሚሳዔል
የምስሉ መግለጫ,የሩሲያ ባለስቲክ ሚሳዔል

ከ 7 ሰአት በፊት

በአውሮፓውያኑ የካቲት 20222 ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ስታውጅ አንቶን የሚያገለግልበት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጣቢያ በተጠንቀቅ ቆሞ ነበር።

“ከዚያ ቀደም ልምምድ ብቻ ነበር የምናደርገው። ነገር ግን ጦርነቱ የተጀመረ ቀን፤ የጦር መሣሪያዎቹ በተጠንቀቅ ቆሙ” ይላል የቀድሞው የሩሲያ የኒውክሌር ኃይል መኮንን።

“የጦር መሣሪያዎቹን ወደ ባሕር እና ወደ አየር ለመተኮስ ዝግጁ ነበርን። በመርኅ ደረጃ የኒውክሌር ጥቃት ለማድረስ ዝግጁ ነበርን ማለት ነው።”

የቢቢሲው ዊል ቬርኖን ከአንቶን ጋር የተገናኘው ከሩሲያ ውጭ ነው። ለአንቶን ደኅንነት ሲባል ያለበት ቦታ በዚህ ታሪክ ውስጥ አይጠቀስም። ትክክለኛ ስሙ እና ገጽታውን የሚያሳይ ፎቶውም ይፋ አይደረግም።

አንቶን በጣም ምሥጢራዊ በሆነ የሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጣቢያን መኮንን ሆኖ ያገለግል ነበር።

የሚሠራበትን ጣቢያ የሚያረጋግጡ መዛግብት ለቢቢሲ አሳይቷል።

አንቶን የተናገራቸውን ሁሉንም ክስተቶች ቢቢሲ በግሉ ማጣራት ባይችልም ሩሲያ ታወጣ ከነበረው መግለጫ ጋር የሚጣጣሙ ናቸው።

አንቶን ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የሩሲያ ኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂ (በስተግራ)

የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ድንበር በብዛት ካቀኑ ከሦስት ቀናት በኋላ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸው የኒውክሌር ኃይሎች “በልዩ ተጠንቀቅ እንዲጠብቁ” መታዘዛቸውን አሳወቁ።

አንቶን እንደሚለው በተጠንቀቅ ጠብቁ የሚለው ትዕዛዝ የመጣው ጦርነቱ በተጀመረበት ቀን ሲሆን፣ እሱ የሚገኝበት የጦር ክፍል “ከጣቢያው ፈፅሞ እንዳይወጣ” ተደረገ።

የቀድሞው መኮንን “ከሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ውጭ ምንም ነገር አልነበረንም” ይላል።

“ምን እንደሆነ አልገባኝም ነበር። በተሰጠኝ ትዕዛዝ መሠረት ግዴታዬን መወጣት ጀመርኩ። እኛ እየተዋጋን አልነበረም። ሥራችን የነበረው የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎችን መጠበቅ ነበር።”

ከሁለት አሊያም ከሦስት ሳምንታት በኋላ በተጠንቀቅ ቆማችሁ ጠብቁ የሚለው ትዕዛዝ እንዲነሳ ተደረገ።

የሩሲያ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ለጋዜጠኞች ብዙ ጊዜ ቃላቸውን ሲሰጡ አይሰማም። የአንቶን ቃል በሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጣቢያ ውስጥ ምን እንደሚከናወን ፍንጭ የሰጠ ነው።

“በዚህ ጣቢያ ለመመረጥ ከፍተኛ ፈተና አልፈን ነው የምንመጣው። እንዲሁ መመረጥ የለም። ሁሉም ሰው ዲሲፕሊን ያለው ወታደር ነው” ይላል።

“ሁሉም ሰው በየጊዜ ማጣራት እና ሐሰትን የሚለይ መሣሪያ ተገጥሞለት ምርመራ ይደረግበታል። የሚከፈለን ከፍተኛ ገንዘብ ነው። የኒውክሌር ጠባቂዎች ወደ ጦር ሜዳ አይሄዱም። ሥራቸው የኒውክሌር ጥቃትን መከላከል አሊያም ጥቃት ማድረስ ነው።”

የቀድሞው የሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂ እንደሚለው ሁሉም ጥብቅ ክትትል ይደረግበታል።

“በእኔ ሥር ያሉ ወታደሮች ምንም ዓይነት ስልክ ወደ ኒውክሌር ጣቢያው ይዘው እንዳይገቡ የማድረግ ኃላፊነት ነበረብኝ” ይላል።

“በጣም ጥብቅ የሆነ ማኅበረሰብ ነው። ሁሉም ሰው ይተዋወቃል። ቤተሰቦቹ እንዲጎበኙት የሚፈልግ ወታደር ሦስት ወራት አስቀድሞ ለኤፍኤስቢ (ለሀገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት) የፈቃድ ደብዳቤ ማስገባት አለበት።”

ግራፍ

አንቶን የኒውክሌር ጣቢያው የደኅንነት ቡድን አባል ነበር። ይህ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሩሲያን ኒውክሌር ይጠብቃል።

“በየጊዜው ሥልጠና ይሰጠናል። በሁለት ደቂቃ ውስጥ ምላሽ እንድንሰጥ ነው ሥልጠና የወሰድነው” ይላል ኩራት ቢጤ እየታየበት።

ሩሲያ 4,380 ገደማ የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች አሏት ይላል የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌዴሬሽን ያወጣው ዘገባ። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል 1,700 የሚሆኑት ናቸው “ለአገልግሎት ዝግጁ” ሆነው የሚጠብቁት።

ሁሉም የኔቶ ሀገራት ተደማምረው ያላቸው የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሩሲያ ብቻዋን ከታጠቀችው ጋር እኩል ሊሆን ይችላል።

ፑቲን በተለምዶ ‘ታክቲካል’ ተብሎ የሚጠሩ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። እኒህ አነስተኛ ኒውክሌሮች ከሚሳዔሎች ጋር እኩል ሲሆኑ፣ መጠነ ሰፊ የሆነ ጥፋት ላያደርሱ ይችላሉ።

ነገር ግን በጦርነት ወቅት እኒህን አነስተኛ ኒውክሌሮች መጠቀም ሁኔታዎችን የበለጠ ሊያወሳስባቸው ይችላል።

የፑቲን መንግሥት ምዕራባውያንን ለመፈታተን አንዳንድ ሙከራዎች ሲያደርግ ይስተዋላል።

ባለፈው ሳምንት ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መመሪያቸው ላይ ማሻሻያ አድርገዋል። ይህ መመሪያ ሩሲያ በምን ዓይነት ሁኔታ የኒውክሌር መሣሪያዋን ትጠቀማለች የሚለውን የሚቃኝ ነው።

የተሻሻለው መመሪያ እንደሚለው ኒውክሌር ከሌላት ሀገር “ኒውክሌር ካላቸው ሀገራት ጋር በሚደረግ ትብብር” ጥቃት ከተፈፀመ ሩሲያ የኒውክሌር መሣሪያዋን መጠቀም ትችላለች ይላል።

የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂዎች
የምስሉ መግለጫ,የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂዎች ልዩ ሥልጠና የወሰዱ ወታደሮች ናቸው

አንዳንድ ምዕራባዊያን ተንታኞች የሩሲያ ኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በሶቪየት ኅብረት ጊዜ የነበሩ እና ላይሠሩ የሚችሉ ናቸው ይላሉ።

አንቶን በዚህ አይስማማም። “ሁኔታውን በጣም አቅልለው ለማየት የሚሞክሩ ተንታኝ ተብዬዎች የሚናገሩት ወሬ ነው” ይላል።

“አንዳንድ ቦታዎች ያረጁ የጦር መሣሪያዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ሀገሪቱ በጣም ግዙፍ የሆኑ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች አሏት።”

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ካወጀት ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንቶን “ወንጀለኛ” ያለው ትዕዛዝ ደረሰው።

“ሰላማዊ ዩክሬናውያን ተዋጊዎች ናቸው፤ ስለዚህ መወገድ አለባቸው” የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠው ይናገራል። “ይህ ፍፁም የማላደርገው ነበር ነው። የጦር ወንጀል ነው። ይህንን ላለማድረግ ቃል ገባሁ።”

ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች አንቶን ወደ መደበኛው ጦር እንዲዛወር አደረጉት። ወደ ጦር ሜዳ እንደሚሄድ ተነገረው።

ለንደን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

አንቶን ወደ ጦር ሜዳ ከመላኬ በፊት በጦርነቱ መሳተፍ አልፈልግም የሚል ደብዳቤ ፈረመ። ይሄኔ የወንጀል ክስ ተመሠረተበት። ወደ መበደኛ ውትድርና የተዘዋወረበትን ደብዳቤ እና የተከሰሰበትን ወረቀት ለቢቢሲ አሳይቷል።

ከዚህ በኋላ ነው ከሩሲያ ሸሽተው የሚያመልጡ ወታደሮችን በሚያግዝ ድርጅት አማካይነት ከሀገር ሸሽቶ አመለጠ።

አንቶን እንደሚለው ከኒውክሌር ጥበቃ ጣቢያው አምልጦ ቢሆን ኖሮ ከሀገር መሸሽ አይችልም ነበር። ነገር ግን ወደ መደበኛ ጦር መዛወሩ በቀላሉ እንዲያመልጥ አስችሎታል።

አንቶን በርካታ ሩሲያውያን ዜጎች ጦርነቱን እንደማይደግፉት ይናገራል።

ከሩሲያ የሚያመልጡ ወታደሮችን የሚያግዘው ‘ጎ ባይ ዘ ፎረስት’ የተባለ ድርጅት በየወሩ ከ350 በላይ ሰዎች ለማምለጥ እንደሚመዘገቡ ለቢቢሲ ይናገራል።

ነገር ግን በቀላሉ ማምለጥ አይቻልም። ቢያንስ አንድ ሰው ለማምለጥ ሲሞክር ተገድሏል። ሌሎች ደግሞ ተይዘው በግዴታ ወደ ሩሲያ ተመልሰው ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

አንቶን ከሩሲያ ቢያመልጥም የደኅንነት ሰዎች አሁንም እየፈለጉት እንደሆነ እና ተደብቆ እንደሚኖር ይናገራል።

ግራፍ