
ከ 3 ሰአት በፊት
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አምባሳደር አሊ ዩሴፍ አህመድ አል-ሻሪፍ ደግሞ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበ ከአገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው የሱዳን ጦር ኃይልን የሚመሩት ጄኔራል አል-ቡርሃን ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ነው ለጉብኝት አሥመራ የገቡት።
በተመሳሳይ ቀን ማክሰኞ ኅዳር 17/2017 ዓ.ም. የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸው ተገልጿል።
ጄኔራል አል ቡርሃን ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ለሥራ ጉብኝት አሥመራ ሲገቡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል እንዳደረጉላቸው የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ መስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ አመልክተዋል።
ከጄኔራሉ ጋር የባህል እና ማስታወቂያ ሚኒስትር እና የሱዳን የደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት አሥመራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ መሪዎቹ በሁለትዮሽ ጉዳዮች፣ በሱዳን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የጋራ በሆኑ ወቅታዊ ቀጣናው እና ጆኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
- ከሀገር የሸሸው የቀድሞው የሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂ ምን ይላል?ከ 7 ሰአት በፊት
- ከሀገር የሸሸው የቀድሞው የሩሲያ የኒውክሌር ጣቢያ ጠባቂ ምን ይላል?ከ 7 ሰአት በፊት
- ትራምፕ በመጀመሪያ ቀናቸው ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ ታሪፍ ለመጫን ቃል ገቡ26 ህዳር 2024
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ ጊዜ የሱዳን የውጭ ጉዳይ አምባሳደር አሊ ዩሴፍ አህመድ አል-ሻሪፍ አዲስ አበባ ገብተው ከኢትዮጵያው አቻቸው ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር እንደተወያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች እና በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸው፤ ኢትዮጵያ በጦርነቱ ተፈናቅለው ወደ ግዛቷ ለገቡ ሱዳናውያን ላደረገችው አቀባበል አምባሳደር አሊ ምስጋና አቅርበዋል ተብሏል።
ጌዲዮን (ዶ/ር) በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ድጋፍ እንምትሰጥ አመልክተው፤ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የቀጥታ ንግግሮች እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው ማለታቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ቀን ወደ ኤርትራ ያመሩት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር እና ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከአገራቱ ባለሥልጣናት ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች በሱዳን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ዋነኛ አጀንዳቸው እንደሚሆን ይታመናል።
በጄኔራል ሞሐመድ ሃምዳን ጋዳሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ጦር ተገፍተው መቀመጫቸውን በወደብ ከተማዋ ፖርት ሱዳን ያደረጉት ጄኔራል አልቡርሃን ባለፉት ሳምንታት በአንዳንድ ስፍራዎች ድል እየቀናቸው መሆኑ ይነገራል።
ለሱዳን ወሳኝ ወደ ሆኑት ሁለቱ ጎረቤት አገራት የተጓዙትም እያካሄዱት ላለው ወታደራዊ ዘመቻ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሊሆን ይችላል።
ከወራት በፊት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ፖርት ሱዳን አቅንተው ከጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር በመገናኛት የመጀመሪያው የአገር መሪ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።