
ከ 9 ሰአት በፊት
በቅርብ ጊዜያት አሜሪካንን የመሩ ፕሬዝደንቶች ለአፍሪካ ትኩረት ሲሰጡ አልታዩም። ተንታኞች አዲሱ የትራምፕ አስተዳደርም የተለየ ይዞ ነገር ይመጣል ብለው አያስቡም።
ዶናልድ ትራምፕ ጥር 12/2017 ዓ.ም. የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ማርኮ ሩቢዮ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ። እርግጥ ነው ሹመታቸው በሴኔቱ መፅደቅ አለበት።
ሩቢዮ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉዳይ ፈርጠም ያሉ ናቸው ይባልላቸዋል። የአሜሪካን ግብ ከማሳካት ወደ ኋላ የሚሉ አይመስሉም። ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና ላይ ያላቸው አቋም ጠንከር ያለ ነው።
የፍሎሪዳው ሴናተር ስለአፍሪካ ብዙም ያሉት ነገር ባይኖርም ጠላት እና ወዳጅ ብለው የሚለይዋቸው ሀገራት የትራምፕ አስተዳደር ለሚመጡት አራት ዓመታት የሚያራምደውን ፖሊሲ የሚያሳይ ይሆናል።
ዋይት ሐውስ በአፍሪካ ጉዳዮች ይህን ያህል ጊዜ የሚያጠፋ አይመስልም ይላሉ 14ኖርዝ ስትራቴጂስ የተባለ አፍሪካ ላይ የሚያተኩር የንግድ አማካሪ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዊሊያምስ ሊንደር።
“ሩቢዮ በአፍሪካ ጉዳዩ ጥርስ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው አይደሉም፤ በአፍሪካ ጉዳይ ፍላጎት ያላቸውም አይመስሉም” የሚሉት ዊሊያም አፍሪካ በትራምፕ ዘመነ መንግሥት ትረሳለች የሚል ስጋት አላቸው።
የውጭ እርዳታ
ትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚል ፖሊሲ ያራምዳሉ። ማርኮ ሩቢዮም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ከዚህ አንጻር የሚቃኝ ይመስላል። ማለትም የውጭ እርዳታ ጉዳይ የአሜሪካን ጥቅም በማስጠበቅ ላይ የተመሠረተ ይሆናል።
“ከቻይና ጋር የሚደረግ ፉክክር እና ቁጥጥር እንዲሁም አስፈላጊ የሚባሉ ማዕድኖችን የማሰስ ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” ይላሉ የቻታም ሐውስ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር አሌክስ ቫይንስ።
በአፍሪካ እና በአሜሪካ መካከል የሚኖረው ግንኙነት “በአብዛኛው የንግድ ልውውጥ ላይ ያተኮረ” ይሆናል ይላሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የስድስት ቢሊዮን ወታደራዊ እርዳታ ስታፅድቅ ከተቃወሙ ጥቂት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት መካከል አንዱ ማርኮ ሩቢዮ ነበሩ። አሜሪካ “አሸናፊ የሌለውን” ጦርነት በገንዘብ እየደገፈች ነው ሲሉ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ነቅፈው ነበር።
ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና ግብፅን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በየዓመቱ ከአሜሪካ እርዳታ ይደረግላቸዋል። ኢትዮጵያም በቅርቡ ገንዘብ ማግኘቷ ይታወሳል።
ሩቢዮ ከዚህ ቀደም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እስር ቤት ሳለ ከእስር እንዲለቀቅ መጠየቃቸውን እና የወቅቱን የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት መተቸታቸው አይዘነጋም።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካ ለውጭ እርዳታ የምታፈሰውን ወጪ እንድትቀንስ ጠይቀው ነበር። አሜሪካ ኤድስ፣ የሳንባ በሽታን እና ወባን ለመከላከል የምታወጣውን ወጪ በግማሽ እንደትቀንስ ዕቅድ አውጥተው ነበር።
ነገር ግን ይህ ዕቅዳቸው በኮንግረሱ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ዩሮዢያ ግሩፕ የተባለው ድርጅት የአፍሪካ ክልፍ ኃላፊ የሆኑት አማካ አንኩ የትራምፕ አስተዳደር ለአፍሪካ የሚያደርገውን እርዳታ ይቀንሳል በሚለው አይስማሙም።
“የውጭ እርዳታ ከጠቅላላ በጀታቸው እጅግ ትንሽ መጠን ያለው ገንዘብ ነው። እርዳታን ማቋረጥ ይህን ያህል አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ።
- ትራምፕ በመጀመሪያ ቀናቸው ቻይና፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ ታሪፍ ለመጫን ቃል ገቡ26 ህዳር 2024
- ዋይፋይ ካንሰር ያመጣል የሚሉት እና ክትባቶችን የሚጠራጠሩት የትራምፕ ዕጩ የጤና ሚኒስትር25 ህዳር 2024
- የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፡ ሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነት ይፈርሙ ይሆን?21 ህዳር 2024

ቻይና
ማርኮ ሩቢዮ ቻይና “ለአሜሪካ እጅግ ትልቋ እና ዘመናዊ ተቀናቃኝ ናት” ብለው ነበር።
በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የሚኖር ቁርሾ የተሞላበት ግንኙነት ለአፍሪካ ሀገራት አያዋጣም። ምክንያቱም ቻይና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር እጅግ የጠበቀ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት አላት።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከአሜሪካም ሆነ ከቻይና ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው ነው የሚሹት።
የማርኮ ሩቢዮ ፖሊሲ በትራምፕ የመጀመሪያው ዘመነ ሥልጣን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከነበሩት ማይክ ፖምፔዮ ፖሊሲ ለየት ያለ አይሆንም የሚሉት አንኩ፤ አሜሪካ “ፀረ-ቻይና ፖሊሲዋን በአፍሪካ ማራመድ ትፈልጋለች” ብለው ያምናሉ።
ባለፈው ጥቅምት ደቡብ አፍሪካ የታይዋን ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከፕሪቶሪያ ወደ ጆሀንስበርግ ይዛወር ማለቷን ተከትሎ ሩቢዮ “ደቡብ አፍሪካ ለቤይጂንግ በማጎብደድ ከፍተኛ ጥፋት እየሠራች ነው” ብለው ነበር።
ዕጩው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሪክስ የተባለው እያደጉ የመጡ የሀገራት ጥምረትን በግልፅ ተቃውመዋል። ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ የስብስቡ መሥራች ስትሆን፤ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ደግሞ በቅርቡ ብሪክስን ተቀላቅለዋል።
“ድርጅቱ የተመሠረተው በፑቲን ነው። ዓላማው ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስን ከዓለማችን መሪነት ማስወገድ ነው” የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።

ፀጥታ
ዊሊያም እንደሚሉት አሜሪካ ከቻይና እና ከሩሲያ እየገጠማት ያለውን ፉክክር ተከትሎ በአፍሪካ ወታደራዊ ተሳትፎ ልታደርግ ትችላለች። እንደ ኬንያ ያሉ አጋር ሀገራትንም መደገፏን ትቀጥላለች ብለው ያስባሉ።
በቀደመው ጊዜ እንደ ሶማሊያ ባሉ ሀገራት ትልቅ ተሳትፎ የነበራት አሜሪካ በምን ዓይነት መልኩ ትቀጥላለች የሚለው ግልፅ አይደለም የሚሉት ደግሞ አሌክስ ቫይንስ ናቸው።
ቫይንስ እንደሚሉት በትራምፕ ዘመነ መንግሥት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ አፍሪካ መጥተው ጉብኝት የማድረጋቸው ነገር የሳሳ ነው።
ሩቢዮ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ሀገራት የአሜሪካ ተቀናቃኝ ከሆኑ ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ እየፈለጉ ነው የሚል ትችት አሰምተው ነበር።
በ2022 አልጄሪያ ከሩሲያ የጦር መሣሪያ መግዛቷን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ እንድትጥል ለፕሬዝደንት ጆ ባይደን ደብዳቤ ፅፈዋል።
“ሩሲያ ለአልጄሪያ ከፍተኛውን ወታደራዊ ቁሳቁስ የምታቀርብ አገር ናት” ሲሉ የጻፉት ሩቢዮ፣ “ቢሆንም ያልተጠቀሙበት ማዕቀብ የመጣል ሥልጣን በእጅዎ ላይ አለ” ብለው ነበር።
አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር በአፍሪካ ጉዳይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት ባይኖርም ዲፕሎማሲያዊ ለውጦች ሊታዩ እንደሚችሉ ተንታኞቹ ያስረዳሉ።
ከሩሲያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ባለው የግል ወታደራዊ ቡድን በሆነው ቫግነር ላይ ዘጋቢ ፊልም እያዘጋጁ ሳለ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ በተገደሉት ሦስት ሩሲያውን ጋዜጠኞች ሞት ዙሪያ የተባበሩት መንግሥታት ምርምራ እንዲያካሂድ በአውሮፓውያኑ 2019 ጠይቀው ነበር።
በተጨማሪም ሩቢዮ ሊቢያን ለረጅም ዓመታት ለመሩት ሚአማር ጋዳፊ መውደቅ ምክንያት የሆነውን በአሜሪካ የተማራውን የኔቶ በሊቢያ የፈጸመውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ደግፈው ተከራክረዋል።
በአጠቃላይ ሲታይ በሩቢዮ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ዘመን አሜሪካ ከአፍሪካ አንጻር በምታራምደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ጉልህ ለውጥ አይኖርም የሚሉት አማካ አንኩ፣ አሁን ያለው ማኅበራዊ እና ወታደራዊ መረሃ ግብሮች በነበሩበት ይቀጥላሉ ይላሉ።
አክለውም ምናልባትም ዲፕሎማሲያዊ የአቅጣጫ ለውጥ ሊኖር ይችላል ብለው ይገምታሉ።
“እንደማስበው ከአፍሪካ ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተወሰነ ደረጃ ሊቀዛቅዝ ይችላል፤ ምክንያቱም በከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት አማካይነት ወደ አህጉሪቱ የሚደረጉ ጉብኝቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስለማይሆነ ነው” ብለዋል።
“[በቀድሞው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን] እንደነበረው ግድየለሽነት የተሞላባቸው ንግግሮች ይኖራሉ፣ ያ ግን ብዙም ችግር የሚፈጥር አይሆንም። ነገር ግን ጉልህ የሆኑ ለውጦችን አናይም።”