
ከ 7 ሰአት በፊት
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሦስቱ ታላላቅ የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ለመጣል የገቡት ቃል የአራቱንም አገራት ኢኮኖሚ ሊጎዳ እንደሚችል የካናዳ፣ የሜክሲኮ እና የቻይና ባለስልጣናት አስጠነቀቁ።
“የጋራ ንግዶቻችንን አደጋ ላይ እስክንጥል ድረስ ለአንዱ ታሪፍ ሌላው ምላሽ ይሰጣል” ሲሉ የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም ተናግረዋል።
ትራምፕ ሰኞ ምሽት ከሜክሲኮ እና ካናዳ በሚገቡ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ፤ ከቻይና በሚገቡት ዕቃዎች ላይ ደግሞ 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ ለመጣል ቃል ገብተዋል። ታሪፉ እጾችን እና ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል የተደረገ ነው ብለዋል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ጉዳዩ ይፋ ከተደረገ በኋላ ትራምፕን ማነጋገራቸውን እና ረቡዕ ዕለት ደግሞ ከካናዳ የክልል ባለስልጣናት ጋር ስለሚኖረው ምላሽ ለመወያየት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ “ማንም ሰው በንግድም ሆነ በታሪፍ ጦርነት አያሸንፍም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፋዊው ግፊት የመጣው ትራምፕ ጥር ወር ላይ ሥራ ሲጀምሩ የመጀመሪያ ቀን ዕቅዳቸውን በተመለከተ ትሩዝ ሶሻል በተባለ ማህበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ነው።
አገራቸው ከአሜሪካ ጋር “ገንቢ በሆነ መንገድ” ለመሥራት መዘጋጀቷን ትሩዶ ተናግረዋል።
“ይህ ግንኙነት የተወሰነ ሥራ እንደሚፈልግ ስለምናውቅ ይህኑኑ እናደርጋለን” ሲሉ ትሩዶ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
ትሩዶ ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት በንግድ እና በድንበር ደህንነት ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል። የካናዳ ድንበርን አቋርጠው አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር አንጻር በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የስልክ ጥሪ መደረጉን በተመለከተ የትራምፕ ቡድን ለማረጋገጥ ፈቃደኛ አልሆነም።
የትራምፕ ቃል አቀባይ ስቲቨን ቼንግ አክለው እንደገለጹት የዓለም መሪዎች ከትራምፕ ጋር “የተጠናከረ ግንኙነት ለመፍጠር የሚሞክሩት እሳቸው ዓለም አቀፍ ሠላምና መረጋጋትን ስለሚወክሉ ነው” ብለዋል።
የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ሺንባም ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ማስፈራሪያም ሆነ ታሪፍ በአሜሪካ ያለውን “ስደት” ወይም የአደንዛዥ እጽ አጠቃቀምን አይፈታም።
ለትራምፕ ይላካል ካሉት ደብዳቤ ያነበቡት ሺንባም አገራቸው ከአሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ቀረጥ በመጣል “የጋራ ኢንተርፕራይዞችን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚደረገውን ህገወጥ ስደት ለመቅረፍ እርምጃ መውሰዷን እና “ስደተኞች ከአሁን በኋላ ድንበር አይደርሱም” ሲሉ ተናግረዋል።
የአደንዛዥ እጽ ጉዳይ “የአገርዎ ማህበረሰብ የጤና እና የአጠቃቀም ችግር ነው” ሲሉ አክለዋል።
የአሜሪካ የመኪና አምራቾች አንዳንድ መለዋወጫዎችን በሜክሲኮ እና ካናዳ እንደሚያመርቱ ባለፈው ወር ሥራ የጀመሩት ሺንባም ጠቅሰዋል።
“ታሪፍ ከጨመረ ማንን ይጎዳል? ጄኔራል ሞተርስ” ሲሉ ለጥያቄያቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
- “መምህር በመሆኔ አዘንኩ” – የኢትዮጵያ መምህራን እሮሮከ 9 ሰአት በፊት
- እስራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባይደን አረጋገጡከ 8 ሰአት በፊት
- አዲሱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለአፍሪካ ምን ይዘው ይመጣሉ?ከ 9 ሰአት በፊት
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “የቻይና-አሜሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ሁለንተናዊ ጥቅም ያለው ነው።”
ፌንታኒልን ጨምሮ ህገወጥ ዕጾችን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎች በድብቅ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ቻይና ትፈቅዳለች መባሉን አስተባብለዋል።
“ቻይና ለተወሰኑ ለአሜሪካ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እርምጃ ወስዳለች” ሲሉ ሊዩ ተናግረዋል።
“ቻይና እያወቀች የፌንታኒል ኬሚካሎች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ፈቅዳለች የሚለው ከእውነታው ጋር የሚቃረን መሆኑን ነው።”
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ቻይና ላይ የጣሉትን ታሮኢፍ ከማስቀጠል ባለፈ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቂት ታሪፎችንም አስተዋውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገራት የሚገበያዩት አብዛኛው ምርት ታሪፍ ይጣልበታል። አሜሪካ ከቻይና በምታስገባቸው ምርቶች ላይ 66.4 በመቶ እንዲሁም ቻይና ከአሜሪካ በምታስገባቸው ላይ ደግሞ 58.3 በመቶ ታሪፍ ይጣልባቸዋል።
በኦታዋ በሚገኘው የጋራ ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት ትሩዶ “ከአሜሪካ ጋር ጦርነት የመጀመር ሃሳብ ማንም አይፈልግም” ብለዋል።
“አትደንግጡ” ካሉ በኋላ አብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
“ይህ በቁም ነገር እና በዘዴ የምንሰራው ሥራ ነው። መደናገጥ ግን አያስፈልግም” ብለዋል።
የካናዳ ግዛቶች መሪዎች በበኩላቸው የራሳቸውን ታሪፍ አሜሪካ ላይ ስለመጣል ሐሳብ አቅርበዋል።
“ለአሜሪካ የምንሸጣቸው ነገሮች በጣም የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ናቸው። እኛ ዘይት እንሸጣቸዋለን፣ ኤሌክትሪክ እንሸጣቸዋለን፣ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት እና ብረቶችን እንሸጣቸዋለን” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስቲያ ፍሪላንድ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
ካናዳ በአውሮፓውያኑ 2022 ወደ 437 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምርቶችን ለአሜሪካን የሸጠች ሲሆን በተመሳሳይ ዓመት የአሜሪካ የውጭ ንግድ ትልቁ ገበያ እንደነበረችም የአሜሪካ መረጃ ያሳያል ።
ካናዳ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች 75 በመቶውን ወደ አሜሪካ ትልካለች።
ከካናዳ ግዛቶች በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆነችው የኦንታርዮ ሚኒስትር ዳግ ፎርድ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት የታቀደው ታሪፍ “ካናዳ እና አሜሪካ ውስጥ ባሉ ሠራተኞች እና ሥራዎች ላይ ከባድ ጫና አለው።”
“እኛን ከሜክሲኮ ጋር ማወዳደር ለእኛ ከፍተኛ ስድብ ነው” ብለዋል ፎርድ።
የፎርድ ሃሳብን የኪውቤክ፣ ሳስካችዋን እና ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ሚንስትሮችም አስተጋብተውታል። የአልበርታ ሚኒስትር ዳንኤሌ ስሚዝ በበኩላቸው ትራምፕ በጋራ ድንበራችን ላይ “ከህገወጥ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ትክክለኛ ስጋት” እንዳላቸው አምነዋል።
ትራምፕ በጥር ወር ከካናዳ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጣል ቃል ከገቡ በኋላ የካናዳ ዶላር ዋጋ ቀንሷል።