በደቡብ ኢትዮጵያ ተማሪዎች እና መምህር
የምስሉ መግለጫ,በደቡብ ኢትዮጵያ ተማሪዎች እና መምህር

ከ 9 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ መምህራን በተለያየ አቅጣጫዎች ሰቆቃቸውን እያሰሙ ነው።

ለ17 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው መምህራን መንግሥትን መክሰሳቸው ታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአራት ክልሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ መምህራንም በደል እየተፈጸመብን ነው ብለዋል።

መምህራን ከደሞዝ መቆራረጥ ጀምሮ በግዴታ መዋጮ እንዲያወጡ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ለምን ብለው የጠየቁት ደግሞ ለድብደባ፣ ለእስር እና ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመምህራን ማኅበር በበኩሉ ከደሞዝ ጋር የተያያዙ ሪፖርቶች እንደሚቀርቡለት ጠቁሞ፤ ዳፋው ለትውልዱ እና ለትምህርት ሥርዓቱ ነው ብሏል።

“እየተራብኩ አላስተምርም” – ሲዳማ ክልል ደራራ ወረዳ

የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል ሲዳማ መምህራን በግዴታ ለብልጽግና ፓርቲ ህንጻ ግንባታ እንድናዋጣ ጫና እየደረሰብን ነው ይላሉ።

በማዕከላዊ ዞን ደራራ ወረዳ የሚገኙ መምህራን ለወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ህንጻ ግንባታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲያዋጡ ተጠይቀው ያልተስማሙ መምህራን የጥቅምት ወር ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

ደሞዛቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ እና ያልፈረሙ 200 የሚሆኑ የደራራ ወረዳ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን የጥቅምት ወር ደሞዝ አልተከፈላቸውም።

ለፓርቲ ጽ/ቤት ግንባታ መምህራንን ጨምሮ ከመንግሥት ሠራተኞች 16 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የወጠነው ወረዳው “ግዴታ በልማት መሳተፍ አለባችሁ” በሚል ጫና እያሳደረብን ነው ብለዋል።

በ10 ወር ተቆርጦ የሚያልቅ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲያዋጡ የተጠየቁት መምህራኑ “እኛ እኮ ከምንሠራው ግብር ይቆረጥብናል፤ ይሄ ደግሞ ለልማት ነው የሚውለው. . .” በሚል ስብሰባ ላይ ማሳወቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መምህራኑ ለተቃውሟቸው አቅም ካለመኖር ባለፈ፤ የብልጽግና ፓርቲ አባል አለመሆናቸውን እና ግዴታቸውም እንዳልሆነ በማስረገጥ ፊርማ አሰባስበው ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አቤቱታ ማቅረባቸውን አንድ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ተናግረዋል።

“የተባላችሁትን አድርጉ፤ ፈርሙ እና [ደሞዛችሁ] ይሰጣችኋል” የሚል ምላሽ ተሰጠን ያሉት መምህሩ፤ “እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡት መፈረምን ነው” ሲሉ ያገለገሉበት ደሞዝ ‘በግዴታ መዋጮ’ እንደተያዘባቸው ገልጸዋል።

መንግሥት “አስገድዶ [ገንዘብ] እየወሰደ ነው” ያሉ ሌላ መምህር፤ ከአካባቢው አስተዳደር “የትም ብትሄዱ ዞራችሁ እኛ ጋር ነው የምትመጡት” የሚል ግልጽ ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል።

“ከተራቡ፤ ከተጠሙ መምጣታቸው አይቀርም ብለው እየዛቱ ነው” ያሉት ሌላ መምህር፤ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ መምህራን ተገደው እንደፈረሙም ተናግረዋል።

ለመዋጮው ፈቃደኛ ሆነው የፈረሙ መምህራን “ወደው ሳይሆን እስር እና ዛቻን፤ እንዲሁም ረሃብን በመፍራት ነው” ያሉት መመህሩ፤ “ሰቆቃ ውስጥ ነው ያለነው” ይላሉ።

“ተከራይ ነኝ፤ የቤት ኪራይ አልከፈልኩም። ሌሎች ወጪዎች አሉኝ፤ መሸፈን አልቻልኩም። ለምግብ ራሱ ሌላ ቦታ ከሚሠሩ ጓደኞቼ ተበድሬ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ለመኖር በጣም እየተቸገርን ነው” ሲሉ አንድ መምህር ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

“አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነን” ያሉ ሌላ ደሞዝ ያልተከፈላቸው መምህር “ሰው ሳይበላ አይሠራም” ብለዋል።

“መብቴን እየሠራሁ ስጠይቅ ቆይቼ ባለፈው ሳምንት ግን ሰው ሳይበላ አይሠራምና በጣም ስላቃተኝ [ትምህርት ቤት] መሄድም ስላልቻልኩ ሥራ አቁሜ ሌላ ቦታ ከምትኖር እህቴ ጋር ተጠግቼ ነው ያለሁት” ብለዋል።

“እስር ቤቱን የሞሉት መምህራን ናቸው”- ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ሳርማሌ ወረዳ ለተማሪዎች ‘መጽሐፍ ህትመት’ በሚል ከመምህራን ደሞዝ ያለፈቃዳቸው ገንዘብ መቆረጡን ተናግረዋል።

በወረዳው በሚገኙ 27 ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ለሦስት ተከታታይ ወራት በየወሩ 25 በመቶ ደሞዛቸው መቆረጡን ገልጸዋል።

የጉምሮ ጎልቦ ትምህርት ቤት አንድ መምህር ስለመዋጮው በነበረ ስብሰባ ላይ የመምህራን አቅም ውስን እንደሆነ እና እንደማይችሉ መናገራቸውን ጠቁመው፤ “ግዴታ የእናንተ አሻራ መኖር አለበት ካላችሁ የቻልነውን ያህል በጥሬ ገንዘብ እንረዳለን” የሚል አማራጭ አቅርበው ነበር።

ሆኖም የወረዳው አስተዳደር መምህራን ሳይስማሙ እና ፈቃደኛ ሳይሆኑ በየወሩ ከደሞዛቸው 25 በመቶ እንዲቆረጥ አድረጓል በማለት ከሰዋል።

“እኛ የቀለም አባት ነን። ከእኛ የግድ ቢቆረጥም፣ በፈቃደኝነት ብንሰጥም ችግር የለውም። እኛን ሳታስፈቅዱ፤ እኛ ፈቃድ ሳንሰጥ፤ ሳንስማማበት ለምን ተቆረጠ?” የሚለው የብዙኃኑ መምህራን ጥያቄ መሆኑን አንድ መምህር ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በዚህም ቅራኔ የገባቸው መምህራን ሥራቸውን ሳያቆሙ በወኪሎቻቸው በኩል አቤቱታ ቢያቀርቡም ከወረዳው አስተዳደር ዛቻ፣ ድብደባ እና እስር እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

“ትምህርት እናቆማለን፤ ደሞዛችን ሳይከፈለን አናስተምርም” በሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን የተናገሩ የወረዳው የአንደኛ ደረጃ መምህር፤ ‘በግዴታ ታስተምራላችሁ’ በሚል የአካባቢው አስተዳደር ድብደባ እና እስር እንደፈጸመባቸው ገልጸዋል።

መብታቸውን የጠየቁ መምህራን እና የመምህራኑን መታሰር የተቃወሙ ከ20 በላይ መምህራን ከኅዳር 10/2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ፍ/ቤት ሳይቀርቡ መታሰራቸውን ተናግረዋል።

“መምህር የሚባል እኮ የለም፤ እስር ቤቱን የሞላው መምህር ብቻ ነው” ያሉት መምህሩ፤ ትምህርት መቋረጡንም ገልጸዋል።

“መምህር የለም እኮ፤ ማን ያስተምር?” ሲሉ ትምህርት መቋረጡን የተናገሩ ሌላ መምህር “እኔም አላስተምርም” ሲሉ ለደኅንነታቸው በመስጋት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መምህራኑ አቤቱታቸውን በማሰማታቸው የአካባቢው አስተዳደር “ስሜን እያጠፋችሁ ነው” በሚል ጫና እንዳሳደረባቸው የተናገሩት ሌላ መምህር፤ “ፍትሕ ከየት ነው የምናገኛው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

“እኔ መምህር ሆኜ ያለኝን ዕውቀት ካልሰጠሁ የወደፊት የትውልድ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚሆነው? መምህር በዚህ ልክ ከተጎዳ፤ እንደዚህ እየተሰቃየ ትውልድ ወደፊት የት ነው የሚወድቀው?”

[ይህ የቢቢሲ ዘገባ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር እና የወረዳው መምህራን የመብት ጥያቄ አንስተው የታሰሩ 27 ገደማ መምህራን ኅዳር 17/2017 ዓ.ም. ከእስር መፈታታቸውን ተናግረዋል።]

ሰልፍ የወጡ ምምህራን

“ቴሌቪዥኔን ሸጫለሁ” አማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን

የትጥቅ ግጭት ባለበት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ መምህራን በደሞዝ መስተጓጉል እና መዘግየት “ከባድ ችግር” ውስጥ ነን ይላሉ።

መምህራኑ የጥቅምት ወር ደሞዝ እንዳልተከፈላቸውም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመትም ለሦስት ተከታታይ ወራት ደሞዝ ሳይከፈላቸው መቆየቱን የተናገሩት መምህራን ደሞዝ አለመከፈሉ ይቀጥላል በሚል ችግር እና ስጋት ውስጥ ናቸው።

“ንብረታችንን እየሸጥን ነው” ያሉ አንድ የመሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር ሁኔታውን “ፈታኝ” ብለውታል።

“ያለንን ንብረታችንን ሸጠናል። አልጋ ሸጠናል፤ ወንበር ሸጠናል፤ ቴሌቪዥን ሸጠናል። ጓደኞቼ የትዳር ቀለበታቸውን እስከ መሸጥ ደርሰዋል። . . . በዚያ ላይ ኑሮ ውድነቱ አለ። አንድ ኩንታል ጤፍ 11 ሺህ ብር ገብቷል። በቆሎ አራት ሺህ፤ አምስት ሺህ ነው የሚሸጠው” ይላሉ የሁለት ልጆች አባት የሆኑት መምህር።

“ያለው አማራጭ ወደ ተለያየ ቦታ መሰደድ ነው” ያሉ ሌላ መምህር፣ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር መምህራን የቤት እቃቸውን እየሸጡ መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“አልጋውን የሸጠ መምህር አውቃለሁ። . . . ” በማለት መምህራኑ ለልጆቻቸው ዳቦ ለማቅረብ ሲሉ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን እየሸጡ ነው ብለዋል።

አካባቢውን የመንግሥት ኃይሎች ለቀው ሲወጡ ደሞዝ እንደሚቋረጥ የሚናገሩት መምህራን በወረዳው የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራኞችም ደሞዝ እንደማይከፈላቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገርም በአካባቢው መምህራን “ተለይተው” ጫና እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።

“‘የዚህ ችግር [የግጭቱ] ዋነኛ ጠንሳሾቹ እናንተ ናችሁ። እየተዋጋችሁ ያላችሁት እናንተ ናችሁ’” በሚል ጫና እንደሚደርስባቸውም የተናገሩ አንድ መምህር መታወቂያቸውን ለማሳየት ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

“መምህር በመሆኔ በጣም ተቆጨሁ” – ደቡብ ምዕራብ ክልል ካፋ ዞን

በደቡብ ምዕራብ ክልል ካፋ ዞን ጨታ ወረዳ ለልማት በሚል መምህራን “ያለፈቃዳቸው” የአንድ ወር ደሞዛቸው ለመዋጮ እንደተቆረጣባቸው ገልጸዋል።

መምህራኑ “ለገጠር መንገድ ግንባታ” ይውላል የተባለ እና በአንድ ዓመት የሚቆረጥ የአንድ ወር ደሞዝ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ “በጅምላ” እና “በማን አለብኝነት” መቆረጡን ይናገራሉ።

“ከ50 በመቶ በላይ [የመንግሥት ሠራተኞች] ደገፉት ስለተባለ በጅምላ ይቆረጣል” ተብሎ መወሰኑን የተናገሩ አንድ የአንደኛ ደረጃ መምህር፤ ፈቃደኝነታቸው እና አቅማቸው ውሳኔው ላይ ሚዛን እንዳልደፋ ተናግረዋል።

“መምህራን የልማት ተቋዳሽ አይደሉም ሳይሆን፤ አቅማችን የማይፈቅደውን አትጠይቁን ነው እያልን ያለው” ሲሉ አንድ መምህር ምሬታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

መዋጮው መምህራን ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ የጠቆሙ ሌላ መምህር አነስተኛ ገቢያችንን እና የኑሮ ጫናን አገናዝቦ “በአቅማችን ይሁን” የሚል ሀሳብ እንዳለ ተናግረዋል።

“የአራት ሺህ ብር ደሞዝተኛ ነኝ። አራት ሺህዋን ብር ከምትወስዱብኝ እባካችሁ 1500 ብር በእጄ ልስጣችሁ [ብዬ] ለመንኩ” ብለዋል የወረዳው ባሺ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር።

“እርዳታ ነው፤ አስተዋጽኦ ነው፤ ለልማት አሻራችሁን አሳርፉ ነው የሚባለው። ሰው በቻለው ነው። . . . የሚችል ነው የሚደግፈው” ሲሉ በአቅማቸው ለማዋጣት ጥያቄ ቢያቀርቡም የወረዳው አስተዳዳሪዎች ግን “የአንድ ወር ደሞዝ ሙሉ ካልሆነ አይቀበሉም” ብለዋል።

የጥቅምት ወር ደሞዝ የተቆረጠባቸው መምህራን አቤቱታ ለማቅረብ ወደ መንግሥት ተቋማት ሲያቀኑ እንግልት እንደደረሳቸው አንድ መምህር ሲናገገሩ፤ ሌላ መምህር ደግሞ “በፖሊስ ታፍነን ነበር” ብለዋል።

“ሰርቆ እንደሄደ ሰው [በፖሊስ] ታጅበን ነው የሄድነው” ሲሉ አንድ መምህር ክስተቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በወረዳው ለሁለት ቀናት ያህል ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር የተናገሩት መምህራን፣ ከዞኑ አስተዳደር ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው ስለተነገራቸው ማስተማር መጀመራቸውን ተናግረዋል።

“መምህር በመሆኔ በጣም ነው ተቆጨሁት። መምህር ከወር ደሞዝ ውጪ የሚያገኘው አንዳች ነገር የለም። አዲሱ ክልል ከተመሠረተ ወዲህ እስከ 50 ቀን ድረስ ቆይቶ ነው ደሞዛችን የሚከፈለን። ይህን ታግሰን፤ ሆድ እና ጀርባችን ተጣብቆ፣ ስቃይ አይተን ደግሞ ይሄ ደሞዝ ሲቆረጥ፤ መብታችንን ማንም ሳያስከብርልን ሲቀር. . . መምህር በመሆኔ በጣም አዝናለሁ” ሲሉ በምሬት ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

የመምህራን ማኅበር ምን ይላል?

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በተለይም በአዳዲሶቹ ክልሎች ከደሞዝ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ ሪፖርት እንደሚደርሰው ተናግሯል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ “መምህራን በወቅቱ በጊዜው ደሞዛቸው ካልተከፈለ በቀጥታ ለመምህራን ብቻ ሳይሆን በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል። በትውልድ ግንባታ እና በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ጫና ስለሚፈጥር መፍትሔ መሰጠት አለበት” ብለዋል።

“[የመምህራን] መብታቸው መከበር አለበት፤ ደሞዛቸው ሳይፈቅዱ መቆረጥ የለበትም። ይህን አጀንዳ ይዘን እንወያያለን፤ ለሚመለከታቸው አካላት እንገልጻለን። ይህ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው” ሲሉ ችግሩን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለብልጽግና ፓርቲ መዋጮ አናወጣም ላሉ የሲዳማ ክልል መምህራን ደሞዝ አለመከፈልን በሚመለከት ሪፖርት እንዳልደረሳቸው ጠቅሰው፤ ጉዳዩን እንደሚያጣሩም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ መምህራንን የግዴታ መዋጮ በሚመለከት ሪፖርት እንደደረሳቸው የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ ተናግረው፤ የመምህራን መታሰርንም አረጋግጠዋል።

“[የወረዳው] ትምህርት መምሪያ ‘በፍላጎታቸው ነው አላስገደድንም’ ይላል፤ [የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል] ማኅበሩ ደግሞ ‘በግድ ነው እየተቆረጠባቸው ያለው’ [ይላል]” ሲሉ ማኅበሩ እንደሚያጣራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“እኛ የምናበረታታው [መዋጮው] በአቅማቸው፣ በፍላጎታቸው፣ በሚችሉት ልክ ይሁን የሚል ነው። በግድ መሆን አለበት ብለን አናምን” ሲሉ የማኅበራቸውን አቋም አሳውቀዋል።

ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዳስታወቁም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል መምህራንን በሚመለከትም ማኅበሩ በም/ቤት ስብሰባው የመምህራን ደሞዝ ሊከፈል እንደሚገባ አቋም መያዙን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንንም ለሚመለከታቸው የክልሉ ተቋማት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

ማኅበሩ የመምህራንን መብት ለማስከበር ከጥያቄ ባሻገር በሕግ አግባብ ለመጠየቅ ማሰቡን በሚመለከት “መክሰስ ይቻላል፤ ምንም የሚከለክለን ነገር የለም። [ግን] ስንቱን ነው የምንከሰው? . . . ይህን ሁሉ ጠበቃ ማቆም አንችልም። በፌደራል ደረጃ አንድ ጠበቃ ነው ያለን። በየክልሎቹ ያሏቸው አሉ። ክልሎች ያን ማድረግ [ክስ መመሥረት] ይችላሉ። ያደረጉም አሉ” በማለት ከክስ ይልቅ በንግግር መፍትሄ ማምጣቱ ይበጃል ባይ ናቸው።

“ከዚህ በፊት ብዙ ታግለን፤ ተነጋግረን መፍትሄ አምጥተናል” ሲሉ ለአብነትም የደቡብ ኢትዮጵያ የደሞዝ መዘግየትን ያነሳሉ።

በቅርቡ ለ17 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው የትግራይ ክልል መምህራን ያደረግነው ጥረት አልተሳከም በሚል በክልሉ እና በፌደራል መንግሥቱ ላይ ክስ መመሥስረታቸው ታውቋል።

_____________

* ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ከአራቱ ክልሎች ዘጠኝ መምህራንን አነጋግሯል። ከመካከላቸው ሰባቱ ለደኅንታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሲሆን፣ ሁለቱ በዘገባው ውስጥ ስማቸው እንዲጠቀስ ቢፈቅዱም ቢቢሲ በአካባቢያቸው ባለው የመምህራን እስር ምክንያት ለአደጋ እንዳይጋለጡ በሚል ስማቸውን ከመጠቀም ተቆጥቧል።