
ከ 4 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በሦስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የጣሉትን እገዳ ኣለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪው አምነስቲ አወገዘ።
የመብቶች እና የዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኙት ድርጅቶች ላይ የተጣለው እገዳ በሲቪል ማኅበረሰቡ ምኅዳር ላይ የተቃጣው አፈና እየጨመረ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲል አምነስቲ ማክሰኞ፣ ኅዳር 17/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ድርጅቶቹ “ፖለቲካዊ ገለልተኝነት ማጣት” እና “ከብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ በመሥራት” በሚል ግልጽ እና ተጨባጭ ባልሆኑ ውንጀላዎች መታገዳቸው ተቀባይነት የለውም ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር ታይግሬ ቻጉታህ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንደነዚህ ዓይነት ውንጀላዎችን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማፈን በመሳሪያነት ሲጠቀሙበት እንደቆዩ” ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
እገዳው መጀመሪያውኑ ሊጣል የማይገባው እንደነበር የፌደራል መንግሥት የሰዎችን የመደራጀት እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን የሚጋፋውን ይህንን እገዳ በአስቸኳይ ሊቀለብስ እንደሚገባ ምአሳስበዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ተንሰራፍተው ባሉበት ሁኔታ፣ የጅምላ እስር እና የግዳጅ መፈናቀሎች ሪፖርቶች እየወጡ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የሲቪል ማኅበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊነቱን አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ሦስት ስመ ጥር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች መታገድ በሲቪል ማኅበረሰቡ ምኅዳር ላይ የተቃጣው ጭቆና እየጨመረ መሆኑ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኢላማ መደረጋቸው ተጠያቂነት አለመኖሩ ማሳያ ነው” ብለዋል።
- የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በመንግሥት ዕገዳ እንደተጣለበት አስታወቀ22 ህዳር 2024
- አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች በፀጥታ አካላት ጫና እና ዛቻ መሰደዳቸው ተነገረ26 ህዳር 2024
- “መምህር በመሆኔ አዘንኩ” – የኢትዮጵያ መምህራን እሮሮከ 9 ሰአት በፊት
ከዚህ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለውን አካሄድ ድጋሚ ሊያጤነው እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በጦርነቶች የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመዝገብ፣ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ለማጣራት የሚያስችለውን ዘዴ ለመዘርጋት እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ ነው አምነስቲ ምክረ ሃሳብ ያቀረበው።
ዳይሬክተሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ቁርጠኛ” እንዲሆንም መልዕክታቸውን አስተላልፈው ከኢትዮጵያ አንጻር የሚያራምዱትን አቋም እንዲያጤኑት ጠይቀዋል።
“የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች፣ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት [በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት] የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣረው የባለሙያዎች ቡድን የሥልጣን ጊዜ መጠናቀቅን ተከትሎ የያዙትን ፖሊሲ አልባ አቋማቸውን ወደ ጎን በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ለሰብዓዊ መብቶች ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል” ብለዋል።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ አካላት በደረሰባቸው ዛቻ እና ወከባ ምክንያት አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች ከአገር መሰደዳቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባወጣው መግለጫ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች በፀጥታ ኃይሎች “ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ እና ወከባ” እየደደረሰባቸው እንደሆነ አስታውቋል።
በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ ያለው የሲቪል ምኅዳር ሊጠብ እና አደጋ ላይ ሊወድቅ እንሚችል ምክልቶች እየተስተዋሉ ነው ብሏል።
በአካል እና በስልክ ይደርሳል የተባለውን ማስፈራሪያ እና ወከባ በመስጋት አራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መሪዎች አገር ጥለው መሰደዳቸውን ማዕከሉ በመግለጫ ላይ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ደረሱኝ ባላቸው አቤቱታዎች እና ጥቆማዎች ተሰደዱ የተባሉትን መሪዎች ስም ዝርዝር አውጥቷል።
የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል (ካርድ) መሥራች እና የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤደን ፍስሐ እና እሳቸውን የተኩት ወ/ት መሠረት አሊ እንዲሁም ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በደረሰባቸው “ከፍተኛ ጫና፣ ወከባ እና ማስፈራሪያ” እንደተሰደዱ ገልጿል።