
ከ 8 ሰአት በፊት
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ለ13 ወራት የዘለቀውን ውጊያ ለመቋጨት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አረጋገጡ።
“በሊባኖስ እና በእስራኤል ድንበር ላይ እየተደረገ ያለው ፍልሚያ ማክሰኞ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በአገሬው ሰዓት ይቋጫል” ሲሉ ባይደን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን የተኩስ አቁሙ ግጭትን በዘላቂነት ወደ ማቆም ስምምነት ለመድረስ ያለመ እንደሆነ አመልክተዋል።
ሄዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እስራኤል ጥቃት ከመሰንዘር ወደኋላ እንደማትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናግረዋል።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በስምምነቱ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።
እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ ሊባኖስ ላይ ወረራ በመፈጸም የተቀናጀ ጥቃቷን አጠናክራ መቆየቷ ይታወሳል።
በሊባኖስ ውስጥ በአስርት ዓመታት ውስጥ ከታዩ የከፋ በተባለው በዚህ ጦርነት ከ3 ሺህ 823 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
- እስራኤል እና ሔዝቦላህ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ የተቃረቡ መስለዋል26 ህዳር 2024
- ኳታር እስራኤል እና ሐማስን ማሸማገል ለምን ተሳናት?26 ህዳር 2024
- “መምህር በመሆኔ አዘንኩ” – የኢትዮጵያ መምህራን እሮሮከ 9 ሰአት በፊት
የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደታቀደው ረቡዕ፣ ኅዳር 18/ 2017 ዓ.ም. እንደተጀመረ ተገልጿል።
በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በሚቀጥሉት 60 ቀናት ከወረረቻቸው የሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ቀስ በቀስ ወታደሮቿን ታስወጣለች። በምትኩም የሊባኖስ መንግሥት ወታደሮች ስፍራውን የሚቆጣጠሩት ይሆናል።
ስምምነቱ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በአውሮፓውያኑ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የቋጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1701 በተሰኘው ውሳኔ የተመሠረተውን ድንበር መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህም እስራኤል እና ሊባኖስ ከሚዋሰኑበት ሊታኒ ከተሰኘው ደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲርቁ ማድረግን ያካተተ ነው።
“ይህ ስምምነት በስፍራው ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት እና በሁለቱም አገራት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ይፈጥራል” ሲል የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ይከተታተላሉ የተባሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ገልጸዋል።
እስራኤል፣ ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከጣሰ ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ መብት እንዳላት የገለጸች ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ባይደንም ይህንን በማስተጋባት “ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በተጣጠመ መልኩ ራሷን የመከላከል መብት አላት” ብለዋል።
“ሄዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እና ራሱን የሚያስታጥቅ ከሆነ ጥቃት እንፈጽማለን።በድንበር አካባቢ የሽብር መሠረተ ልማቶችን ከገነባ ጥቃት እንፈጽማለን” ሲሉ ኔታንያሁ አስፈራርተዋል።
ከሄዝቦላህ ጋር ያለው ጦርነት መጠናቀቅ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት “በኢራን ስጋት” ላይ እንዲያተኩር እንደሚያስችለው ኔታንያሁ ተናግረዋል።