የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ

ዜና ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረቱን እንዳያባብስና የግብር ጫና እንዳያመጣ ሥጋት ፈጥሯል

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: November 27, 2024

መንግሥት ለ2017 ዓ.ም. ያቀረበው ተጨማሪ በጀት የዋጋ ንረቱን እንዳያባብሰውና በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ላይ ጫና እንዳያመጣ ሥጋት እንዳላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከለትን የፌዴራል መንግሥት ለ2017 ዓ.ም 582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲያፀድቅ ነው ሥጋቱ የተገለጸው፡፡

የፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ በሦስት ተቃውሞ፣ በአምስት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

መንግሥት ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ የሁለተኛውን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በውጤታማነት ለማወከናወን፣ ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ እንደሆነ በማብራሪያው ተገልጿል፡፡

ተጨማሪ በጀት በዋነኝነት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ዕዳ ክፍያ፣ ለማኅበራዊ ድጋፍ፣ ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለመድኃኒት ለምግብ ዘይት ግዥ፣ ለደመወዝ ማሻሻያ፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስተካከያ፣ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስፋፊያ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡

ለተጨማሪ በጀቱ ማሟያ ታሳቢ የተደረገው ከፍተኛ የሆነ የታክስ ገቢን ለመሰብሰብ፣ የታክስ ፖሊሲና የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እንደሚደረጉ በሰነዱ ተብራርቷል፡፡

የተጨማሪ በጀቱን ለመሸፈን ይሰበሰባል ተብሎ ከሚጠበቀው አጠቃላይ 281 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ ውስጥ ከምንዳና ከደመወዝ 16.5 ቢሊዮን ብር፣ ከኮርፖሬት ድርጅቶች የንግድ ሥራ 50.5 ቢሊዮን ብር፣ ከሎተሪና ከዲቪደንድ ግብር ገቢ 4.4 ቢሊዮን ብር፣ ከገቢ ዕቃዎች የቅድሚያ ገቢ ግብር አምስት ቢሊዮን ብርና የወለድ ገቢ ግብር 2.4 ቢሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪ እሴት ታክስ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢ ታክስ ከቢራ 2.8 ቢሊዮን ብር፣ ከቴሌኮሙዩኒኬሽን 9.5 ቢሊዮን ብር፣ ከሙያ አገልግሎት 1.5 ቢሊዮን ብር፣ ከሥራ ተቋራጮች 4.5 ቢሊዮን ብርና ከሌሎችም ዘርፎች ተመሳሳይ ገቢ እንደሚጠበቅ ማብራሪያው ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ከሚመረቱ ዕቃዎች ኤክሳይዝ ታክስ ከስኳር 1.2 ቢሊዮን ብር፣ ከለስላሳ መጠጥ 2.4 ቢሊዮን ብር፣ ከቢራ 4.5 ቢሊዮን ብር፣ ከትምባሆና የትምባሆ ውጤቶች 1.6 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ከተሽከርካሪ መኪኖች የጉምሩክ ቀረጥ 9.8 ቢሊዮን ብር፣ ከሕንፃና ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጉምሩክ ቀረጥ ስድስት ቢሊዮን ብር፣ ከማኅበራዊ ዋስትና ልማት ቀረጥ አሥር ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝም ተብራርቷል፡፡

ከነዳጅ ኤክሳይዝ ታክስ 1.9 ቢሊዮን ብር፣ ከአውቶሞቢል ኤክሳይዝ ታክስ 6.7 ቢሊዮን ብር፣ ከተሽከርካሪ መኪናዎችና መለዋወጫዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ አሥር ቢሊዮን ብር፣ ከተሽከርካሪ መኪናዎች ማሽኖችና መለዋወጫዎች ሱር ታክስ 2.5 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከውጭ አገር ዕርዳታ 122.9 ቢሊዮን ብርና ብድር 177.5 ቢሊዮን ብር ለተጨማሪ በጀቱ ታሳቢ መደረጉ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በፓርላማው እንዲፀድቅ የላከው ተጨማሪ በጀት ለአገር ውስጥ ብድር ክፍያ 121 ቢሊዮን ብር፣ ለውጭ አገር ብድር 64 ቢሊዮን ብር፣ ለመጠባበቂያ 278 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ 119 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የበጀት ሰነድ ለሁለተኛ ዙር የቋሚ ኮሚቴና የሕዝብ ውይይት ሳይመራ በአንድ የጉባዔ መድረክ ከሰባት ያልበለጡ አባላት ብቻ አስተያየት የሰጡበት ሲሆን፣ አባላቱ የግብር ጫናና የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት አለን ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

መሐመድ አብዱ (ፕሮፌሰር) የተባሉት የምክር ቤት አባል በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የፀደቀው በጀት የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ እሠጋለሁ?›› ብለዋል፡፡ በሴፍቲኔት ፕሮግራም በየጊዜው የሚደረገውን ድጋፍ ጠቅሰው፣ ይህ ድጋፍ የተረጂነት ስሜትን እየፈጠረ በመሆኑ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ የተረጂነትን ስሜት ሲገልጹ፣ ‹‹በሴፍቲኔት ኖሮ፣ በሴፍቲኔት ወልዶ፣ በሴፍቲኔት የዳረ ሰው አለ፤›› ሲሉ በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ አዝመራ አንዴሞ የተባሉ የምክር ቤት አባል መንግሥት የአገር ውስጥ ገቢውን ከየት ሊያመጣ ነው የሚል ጥያቄ አቀርበዋል፡፡ አክለውም ታክስ በመሰብሰብ የዋጋ ንረት ማረጋጋት ይቻላል ወይ ብለው፣ በአግባቡ ካልተመራ በኢኮኖሚው ላይ ጫና ይፈጥራል የሚል ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡

በግል ተወዳድረው ፓርላማ የገቡት ካሜል አቶ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው፣ ፓርላማው ከዚህ ቀደም አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት አፅድቆ አሁን ደግሞ የዚያን ግማሽ በጀት መምጣቱ በጣም አልተጋነነም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም 281 ቢሊዮን ብር ከታክስ ለመሰብሰብ ሲታቀድ፣ በአንዴ ይህን ዕቅድ ለማሳካት በሚል ሲኬድ የተረበሸውን ኢኮኖሚ የበለጠ አያባብሰውም ወይ ሲሉ ሥጋተቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡

በብዙ ሥፍራዎች የንግድ እንቅስቃሴ መቀዝቀዙን ጠቅሰው፣ ይህ ተጨማሪ የታክስ ዕዳ ሲመጣ የሚመጣውን ጫና ለመግታት ምን ታስቧል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካይና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በጀቱ ምርት ሊገኝባቸው በሚችሉ ዘርፎች ላይ ቢውል በኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል፣ ነገር ግን የቀረበው ተጨማሪ በጀት ለዕዳ ክፍያና ለማኅበራዊ ድጎማ የተደለደለ በመሆኑ የዋጋ ንረቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

የግብር ከፋዩን ማኅበረሰብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሊከት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣ የመንግሥት ወጪና ገቢ ተመጣጣኝ ካልሆነ የአገሪቱን ዕዳ በመጨመር ችግሩን ያባብሰዋል ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ‹‹የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍ ማሻሻያው አገራዊ ውጥንቅጥ ውስጥ እንዳስገባን በግልጽ እያየነው ነው፤›› ብለዋል፡፡ ተጨማሪ ሆኖ የመጣው የመንግሥት በጀት በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ጫና ምን ያህል እንደሆነ ተጠንቶ እንዳልተገለጸና የበጀት ሰነዱንም እንዳላገኙት ተናግረዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አሠራር ለውጡ በፈጠረው ጫና ምክንያት የአንድ ሠራተኛ ደመወዝ በውጭ ምንዛሪ ሲሰላ፣ ቀድሞ ያገኝ የነበረው በ50 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ምክንያት መንግሥት ለተቀጣሪዎቹ የደመወዝ ማሻሻያ አድርጌያለሁ ቢልም አብዛኛው ሠራተኛ ከ1,000 እና 2,000 ብር በላይ ጭማሪ ባለማግኘቱ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን እንዴት እንዲመሩ ተፈልጎ ነው ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ሠራተኛው ወደ ልመናና ጎዳና እየወጣ እንደሆነ መሸፋፈን በማይቻልበት ደረጃ ዘገባዎች እየወጡ ነው፤›› ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል የደመወዝ ማስተካከያ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ነበረበት ብለዋል፡፡

በተጨማሪም 281 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ ታክስ በመሰብሰብ ለመሸፈን የታቀደበት መንገድ ነጋዴውን ከፍተኛ የታክስ ጫና ውስጥ ከመክተት ባለፈ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን ውዝግብ ውስጥ ይከተዋል ብለዋል፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚ ከፈጠረው ውዝግብ ጋር ተዳምሮ ሌላ የታክስ ሥሌት ውስጥ ከተገባ ተጨማሪ መደናገጥ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የካፒታል ፕሮጀክቶችን በግልጽ ትቷል ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር) አዲስ መንገድ፣ ግድብ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ ሆስፒታልና መሰል መሠረተ ልማቶችን እየገነባ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እያልን ያለነው የኮሪደር ልማት ብቻ እንሥራ ነው፣ ነገር ግን እንደዚህ ሆኖ አገር እንዴት ሊለማ ይችላል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹በማብለጭለጭ ዓይነት ልማት ምንም ዓይነት ውጤት የማያመጣ ተግባር ላይ ገንዘብ ፈሰስ እየተደረገ›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ቅድስት አርዓያ የተባሉ የምክር ቤት አባል ለካፒታል በጀት  የተመደበው ገንዘብ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በርካታ ፕሮጀክቶች ተቋርጠው በመቆማቸው ፕሮጀክቶቹ እንዲጠናቀቁ በቂ የካፒታል በጀት እንዲያዝ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መሠረት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዘመናዊና ተወዳዳሪና ዕድገቱን ቀጣይ ለማድረግ የሚያግዝ የበጀት ጭማሪ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የነበርንበትን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስቀጠል ማለት የአገሪቷን ኢኮኖሚ እያደሙ ወደ ለየለት የማክሮ ፋይናንስ ቀውስ ውስጥ መክተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በታሪካችን ትልቁን ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በብድርም በዕርዳታም ያገኘንበት ወቅት ነው፡፡ ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቀው የታክስ ገቢ ብሔራዊ ኃይል ተቋቁሞ ገንዘቡ በእርግጠኝነት እንደሚገኝ እንጂ በግምት የመጣ ሥሌት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እጅግ በጣም ፍቱን መድኃኒት ነው፤›› በማለት፣ የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ አነስተኛ ነው ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ፣ ‹‹ለመንግሥት ሠራተኞች የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ድጎማ በታሪካችን ከፍተኛ ሲሆን፣ ጭማሪ የተደረገውም አሁን ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ በገበያ በመተመኑ የብርን አቅም ቢያንስ በ50 በመቶ በማዳከሙ፣ የመንግሥት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ በሁለት መባዛት አለበት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡

የታክስ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል በጉዳዩ ላይ  ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ መንግሥት አሁን ለመሰብሰብ ያቀደውን ያህል ገንዘብ ለማስገኘት የሚያስችሉት አዳዲስ የታክስ አሠራሮችን አላውቅም ብለዋል፡፡ አሁን ያሉት አሠራሮች ይህን ያህል ገንዘብ ለማስገኘታቸው እርግጠኛ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡  

ምናልባት ውስን የሆነ ጭማሪ ሊገኝ ይችላል ይሆናል እንጂ፣ ባለፈው ዓመትና ከዚያም በፊት ከነበረው በእጅጉ የሰፋ ግብር ይሰበሰባል ለማለት እንደማይደፈሩ ተናግረዋል፡፡

ለግብር ሰብሳቢ ተቋማት ኮታ በመስጠት ይህን ያህል ገንዘብ እስከሚደርስ ሰብስበህ አምጣ የሚል ትዕዛዝ ካልተሰጠ በስተቀር፣ አሁን ባሉት ሕጎች መሠረት ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ የተጋነነ ገንዘብ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡ፣ ለዚህ የታክስ ፍላጎት አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችልና ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ ምርታማነትና የንግድ እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ አለማስተዋላቸውን አስረድተዋል፡፡

ግብር አመንጪ የሆኑ አዳዲስ አሠራሮች እንደሌሉ አቶ ዮሐንስ ገልጸው፣ ‹‹ያለው ግብር ከፋይ በፊት ሥጋው እየተበላ ከሆነ አሁን አጥንቱን የመጋጥ ያህል ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡