ዮሐንስ አንበርብር

November 27, 2024

ኢትዮጰያ ከውጭ የምታስገባው ነዳጅ የሚከማችበት የጂቡቲ ሆራይዘን ዴፖ

መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በብቸኝነት የያዘውን ነዳጅ አስመጥቶ ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ንግድን ለግል ኩባንያዎች የመፍቀድ ውጥን መያዙን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራለትን የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር ለመመልከት ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ባዘጋጀው ውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ከሳሁን (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት የተለያዩ የንግድ ዘርፎችን ለውድድር ክፍት ማድረግ በጀመረው መንገድ መሠረት ነዳጅ ከውጭ ገዝቶ ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ንግድም በሚቀጥለው ዓመት ለግል ዘርፍ ተዋንያን ክፍት ሊደረግ እንደሚችል ተናግረዋል።

የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለዝርዝር ዕይታ ለምክር ቤቱ የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከተመራ በኋላ በተካሄዱ ቅድመ ውይይቶች በረቂቅ አዋጁ ላይ በርከት ያሉ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ከሚገኘው ከብቸኛው ነዳጅ አቅራቢ ተቋም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በተጨማሪ ሌሎች አቅራቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያመላክተው ማሻሻያ አንቀጽ ይገኝበታል።

የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚሳተፉበት የነዳጅ ስትሪንግ ኮሚቴ በቅርቡ ባካሄደው ውይይት የግል ኩባንያዎች ነዳጅ ከውጭ አስመጥተው ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ፣ ዘርፉንም በገበያ መርህ የሚንቀሳቀስ ለማድረግ ምክክር መደረጉን፣ ሚኒስትሩ ካሳሁን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ይህ አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲካተት የተደረገውም ከዚህ በመነሳት እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የግል ድርጅቶች የነዳጅ ምርቶችን እንደ ማንኛውም ዓይነት ሸቀጥ ከውጭ አስመጥተው በገበያ መርሕ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመንፍጠር መታቀዱን አብራርተዋል።

መንግሥት ብዙ የንግድ አውታሮችን ለገበያ ክፍት እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ነዳጅ አስመጥቶ ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ንግድም በተመሳሳይ መንገድ ለግል ባለሀብቶች ክፍት ሊደረግ እንደሚችል አስረድተዋል።

‹‹የአገሪቱን የኤክስፖርት ገቢ ሙሉ በሙሉ ለነዳጅ ግዥ የሚያወጣ አገር ሊያድግ አይችልም። በእኛ ሁኔታ ያለው ዕውነታ እንደዚያ በመሆኑ የአገራችንን ዕድገት እያቀነጨረ ነው። ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀውም ይህ ሁኔታ በመሠረታዊነት መቀየርን ታሳቢ በማድረግ ነው፤›› ብለዋል።

መንግሥት በነዳጅ ዘርፍ ላይ የጀመረው ሪፎርም በዚህ ዓመት በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ካመጣ፣ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ግንባታ በዚህ ዓመት በሚፈለገው ደረጃ ተከናውኖ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በገበያ ዋጋ መሸጥ የሚቻልበት ደረጃ ከተደረሰ የግል ኩባንያዎች ነዳጅ አስመጥተው እንዲሸጡ በቀጣዩ ዓመት ሊፈቀድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ይህ ከተሳካና ዘርፉ ለግል ኩባንያዎች የሚከፈት ከሆነ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ተልዕኮ ለግዙፍ የመንግሥት ፕርጅቶችና ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ነዳጅ ማቅረብ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት  የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕግ አግልግሎት ኃላፊ ትዕግሥት ንጉሤ፣ ሌሎች ነዳጅ አስመጪዎች እንዲሰማሩ የሚደረግ ከሆነ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ የተጣለው የመጠባበቂያ የነዳጅ ዲፖ የመገንባትና መጠባበቂያ የነዳጅ ክምችት የመያዝ ግዴታ በሌሎች አቅራቢዎች ላይም በተመሳሳይ ሊጣል እንደሚገባና ይህንን የሚገልጽ ድንጋጌ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ እንዲካተት ጠይቀዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በአገሪቱ ፍትሐዊ የነዳጅ አቅርቦት ሥርጭት እንደሌለ በመጥቀስ ረቂቅ አዋጁ ይህንን ችግር በሚፈታ መንገድ እንዲቀረፅ ጠይቀዋል። 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ፣ የፍትሐዊነት ችግርን በሕግ ማዕቀፍ ከመፍታት ባሻገር ችግሩ አንገብጋቢ በመሆኑ ኅዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በነዳጅ ኮታ አሠራር ላይ ከሁሉም ኩባንያዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል። 

ረቂቅ አዋጁ ሕግ ወጥ የነዳጅ ግብይትና ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለማስቀረት፣ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለሚጠቁሙ ክፍያ ለመክፈል የሚያስችል ድንጋጌን አካቷል።

ረቂቅ አዋጁ የተለያዩ የማሻሻያ አንቀጾችን አካቶ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።