

ዜና በአቶ አብነት ገብረ መስቀል የገንዘብ ዕግድ ይነሳልኝ አቤቱታ ላይ መቃወሚያ ቀረበ
ቀን: November 27, 2024
ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት ውድቅ በተደረገው የአቶ አብነት ገብረ መስቀል የገንዘብ ዕግድ ይነሳልኝ ጥያቄ ላይ በሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ጠበቆች መቃወሚያ ቀረበበት፡፡
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአንድም ሁለት ጊዜ ውድቅ የተደረገው የአቶ አብነት የዕግድ ይነሳልኝ ጥያቄ በልደታ ምድብ ሁለተኛ የውል ጉዳዮች ፍትሐ ብሔር ችሎት እንዲታይ ቢቀርብም፣ በሼክ አል አሙዲ ጠበቆች ዕግዱ መነሳት የለበትም የሚል መቃወሚያ ቀርቦበታል፡፡
በአጠቃላይ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ባለውና በዓመት 2.6 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ እንዳለው በተነገረው በናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ኖክ) የአክሲዮን ድርሻ እንዳላቸው የተነገረው አቶ አብነት ገብረመስቀል ከትርፍ ክፍፍል ጋር በተያያዘ ከሼክ አል አሙዲ ጋር መካሰሳቸው ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የአቤቱታ መቃወሚያ መዝገብ ያመለክታል፡፡
ይኼው የፍትሐ ብሔር ክስ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ የአቶ አብነት የአክሲዮንና የትርፍ ድርሻ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ዕግድ እንደተጣለበት መዝገቡ ያትታል፡፡
ይሁን እንጂ በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ በመቃወም ከአንድም ሁለት ጊዜ ዕግድ ይነሳልኝ የሚል አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ችሎቱ ውድቅ እንዳደረገውም መዝገቡ ይጠቁማል፡፡
በአቶ አብነት በኩልም ዕግዱ ይነሳልኝ የሚል አቤቱታ በነሐሴ 2016 ዓ.ም. የቀረበ ሲሆን በተረኛ ችሎት በኩል ጉዳዩ ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ታይቶ የሼክ አል አሙዲ ወገኖች መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በይደር ተቀጥሮ ነበር፡፡
ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም. አቤቱታ መቃወሚያቸውን በሰነድ ይዘው የቀረቡት የሼክ አል አሙዲ ወገኖችም ችሎቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠውን የዕግድ ውሳኔ የመመልከት መብት የለውም ብለው ተቋውሟቸውን አቅርበዋል፡፡ ዕግዱ ሊነሳ እንደማይገባው በመጠቆም አቶ አብነት ዕግድ ይነሳልኝ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ 100 ሚሊዮን ብር በዋስትና አስይዣለሁ ብለው መግለጻቸውንም የተሳሳተ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዕግድ አይነሳ አቤቱታ መዝገቡን የተቀበለ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመጪው ሰኞ ኅዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙም ታውቋል፡፡