ዜና
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ተሟጋቾች በሚደርስባቸው ጫና አገር ጥለው መሰደዳቸው ተገለጸ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: November 27, 2024

የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና የመብት ተሟጋቾች በፀጥታ አካላት የሚደርስባቸው ወከባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በፍጥነት ሊቀረፉ ይችላሉ የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት መሻሻል እንዳልታየባቸውና በርካቶች አገር ጥለው እየተሰደዱ መሆናቸውን፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታወቀ፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል በኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች መታገድና ከመብት ተሟጋቾች መዋከብ ጋር ተያይዞ፣ የሲቪክ ምኅዳሩን መጥበብ በተመለከተ ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በመዘገባቸው ማኅበራት አባላት ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን፣ ወከባዎችን፣ ማስፈራሪያዎችንና የመብት ጥሰቶችን በመከላከልም ረገድ የበኩሉን ኅላፊነት እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

ማዕከሉ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች አመራር የሆኑ ግለሰቦች በፀጥታ አካላት በአካልና በስልክ ተደጋጋሚ ወከባና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ገልጾ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በመሸሽ ከአገር ለመሰደድ መገደዳቸውን በቃልና በጽሑፍ ማስታወቃቸውን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ለአብነትም የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት መሥራችና የቀድሞ የፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፣ በደረሰባቸው ወከባና ከትትል ሳቢያ ከወራት በፊት አገር ለቀው ለመሰደድ መዳረጋቸውን ለድርጅታቸው ማሳወቃቸውን አስታውሷል፡፡

በተመሳሳይ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) የተሰኘ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ኤደን ፍሰሐና በእሳቸው የተተኩት ወ/ሪት መሠረት ዓሊ በተመሳሳይ ዛቻ፣ ወከባና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው አገር ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ መሆኑን በጽሑፍና በቃል ለማዕከሉ መግለጻቸውን በመግለጫቸው አክሏል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ዳይሬክተር የነበሩትና የማዕከሉ መሥራችና የቦርድ አባል የነበሩት አቶ ዳን ይርጋ በተመሳሳይ በፀጥታ አካላት በደረሰባቸው ከፍተኛ ጫና፣ ወከባና ማስፈራሪያ አገር ለቀው ለመሰደድ መብቃታቸውን ለማዕከሉ በጽሑፍና በቃል እንደገለጹለት አስታውቋል፡፡

‹‹በተጨማሪ ሌሎች የኢሰመጉ ሠራተኞች በሚደርስባቸው ተመሳሳይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሥራቸውን ተረጋግተው መሥራት እንዳልቻሉ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ባደረግነው ክትትልና ምርመራ ለመረዳት ችለናል፤›› ሲል ማዕከሉ ገልጿል፡፡

የሲቪል ማኅበራት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ድህነትን ለመቅረፍና ሰብዓዊ መብቶች ከሞላ ጎደል እንዲከበሩ ለማድረግ ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁንና ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸው በመግለጫውን አመላክቷል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ጠንካራ፣ ንቁና ጤናማ የሲቪል ማኅበራት ባሉበት አገር በመንግሥት ሊሸፈኑ የማይችሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ችላ ተብለው እንዳይቀሩና በቂ ትኩረት እንዲያገኙ የሚያስችልና የዜጎች መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩና ተጠያቂነትም እንዲሰፍን እንደሚረዳ አስታውሷል፡፡

የሲቪል ማኅበራት በግጭት እየታወከችና የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች በውይይትና ምክክር እንዲፈቱ ሚና እንዳለባቸው ማዕከሉ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

የሲቪክም ሆነ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲጠብ፣ ሐሳብን የመግለጽና ሌሎች የዜጎች መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች ያላግባብ በሚገደቡበትና በሚጠቡበት ዓውድ ተሳትፎአቸው እንዲኮስስ ከማድረግም ባለፈ ለግጭቶች መበራከት፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል፣ ለድህነት መንሰራፋት፣ ለተጠያቂነት መጥፋትና በአጠቃላይ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መበራከትና ለዴሞክራሲ መቀጨጭ በር እንደሚከፍት ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ከተለያዩ የሲቪል ማኅበራት አባላትና የመብት ተሟጋቶች በርካታ አቤቱታዎችንና ጥቆማዎች ሲቀበል መቆየቱን ጠቅሶ፣ ‹‹የሲቪክ ምኅዳሩን ሊያጠቡና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ምልክቶችን እያየን በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ ዕልባት ይሰጣቸው፤›› ሲልም አሳስቧል፡፡

ማዕከሉ በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. ብቻ ሦስት በሰብዓዊ መብቶች ሥራ ትልቅ ዕውቅናን ያተረፉና አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱና እየሠሩ የሚገኙ ድርጅቶች መታገዳቸውን ጠቅሷል፡፡

‹‹የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራትን አከናውነዋል›› በሚል ዕግድ የተጣለባቸው ድርጅቶች የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR) የተሰኙ ድርጅቶች መሆናቸውንም አክሏል፡፡

በሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችና በሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችና ዕገዳዎች የሲቪል ማኅበረሰቡን ምኅዳር የሚያጠቡ፣ በቀሩት የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ዘንድ ፍራቻን የሚፍጠሩ መሆናቸውን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

ዕገዳው ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ማለትም በነፃነት የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሐሳብን የመግለጽ መብትን የሚጎዳ ከመሆኑም ባለፈ የመንግሥትን ሰብዓዊ መብቶችን የማከበርና የማስጠበቅ ግዴታን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና ለሲቪክ ምኅዳሩ መጥበብ የጎላ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ሲል ገልጾታል፡፡

የታገዱት ድርጅቶች በሰጧቸው መግለጫዎች በግልጽ እንዳስቀመጡት ከዕገዳው በፊት የተሰጣቸው ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያም ሆነ፣ እነሱ የሚያውቁት በግልጽ የተካሄደ ምርመራ አለመኖሩ አካሄዱን ሕግን ያልተከተለና ግልጽነት የጎደለው ስለመሆኑ በመግለጫው አካቷል፡፡

ማዕከሉ ጥሩ ጅምርና እመርታ አሳይቶ ነበረ ያለው የሲቪክ ምኅዳሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እንዲሰፋ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላትና በዋነኝነት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርጉ የተቋቋሙ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ካውንስልና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡