

ማኅበራዊ ሦስቱን የአባላዘር በሽታዎች ለመግታት
ቀን: November 27, 2024
ኤችአይቪ ኤድስ፣ ቂጥኝና ሔፒታይተስ ቢ ከእናት ወደ ልጅ በመተላለፍ የእናትን፣ የሕፃንንና የቤተሰብን አኗኗር የሚያቃውሱ ተላላፊ የአባላዘር በሽታዎች ናቸው፡፡ ራስን በመጠበቅ ተላላፊነቱን መቆጣጠር የሚቻል ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ችግሩ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ ከችግሮቹ ዋነኛውም የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡
ጤና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ ለሚዲያ ባለሙያዎች ባዘጋጀው መድረክ እንደተገለጸው፣ እ.ኤ.አ. በ2030 ኤችአይቪ ኤድስ የማኅበረሰብ ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ዕቅድ ተነድፎ በመሠራት ላይ ነው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቃዱ ያደታ እንደተናገሩት፣ ኤችአይኢ ኤድስ የማኅበረሰብ ሥጋት በማይሆንበት ደረጃ ማውረድና ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔውን ከአምስት በመቶ በታች ማድረስ በዕቅድ ተቀምጧል፡፡
ከአሥር ዓመታት በፊት፣ ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔው 43 በመቶ እንደነበር በማስታወስ፣ ዛሬ ላይ ይህ አኃዝ ወደ 8.7 በመቶ ዝቅ ማለቱንና ለዚህ ውጤት መገኘት በዘርፉ በስፋት በመሠራቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሥራ አስፈጻሚው፣ ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ሦስት ተመሳሳይ በሽታዎችን ያማከለ ስትራቴጂ ተነድፏል፡፡ አንደኛው ኤችአይኢ ኤድስ፣ ሁለተኛው ሔፒታይተስ ቢ እና ሦስተኛው ቂጥኝ ናቸው፡፡ እነዚህን ሦስት በሽታዎች አንድ የሚያደርጋቸው ምክንያት ሁሉም የአባላዘር በሽታዎች መሆናቸውና ከእናት ወደ ልጅ መተላለፋቸው ነው፡፡
እነዚህን በሽዎች ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለቅድመ ወሊድ አገልግሎት የሚመጡ እናቶች በሙሉ ሦስቱንም በሽታዎች ያማከለ ምርመራ እንደሚያደርጉና ከምርመራ በኋላ በሚገኘው ውጤት መሠረትም አስፈላጊው ሕክምና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ኤችአይኢ ካለባቸው እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት በመጀመሪያ ሁለት ወራት ዕድሜያቸው ውስጥ የቫይረስ መጠናቸው መታየት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ነፍሰ ጡር እናቶች ይህንን እንዲያደርጉ የግንዛቤ ሥራ በሰፊው መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አቶ ፈቃዱ እንደተናገሩት፣ በዓመት ከሦስት ሚሊዮን በላይ እናቶች አርግዘው ይወልዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑ እናቶች ደግሞ ከኤችአይኢ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ከወሊድ በፊት፣ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ የሚሰጡ መድኃኒቶችን መውሰድና የጤና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኤችአይቪ ኤድስ ካለባቸው እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ካላገኙ 30 በመቶ ያህሉ ይሞታሉ፡፡ 50 በመቶ የሚደርሱት ደግሞ በአንድ ዓመት ዕድሜያቸው የሚሞቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም እናቶች በጊዜ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው መኖሩንና አለመኖሩን በማረጋገጥ መድኃኒት መጀመር፣ ለሚወልዱት ልጅ በሕይወትና በጤና ለመቆየት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ800 በላይ በሚሆኑ ጤና ተቋማት ኤችአይቪ ባለባቸው ወጣቶችና እናቶች ላይ ኬዝ ቤዝድ ሰርቪላንስ እየተካሄደ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የዲሞግራፊ፣ የሶሺዎ ኢኮኖሚና ሌሎችም መረጃዎች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በኤችአይቪ ኤድስ የመያዝ ምጣኔ እየተመዘገበ ያለው ከ15 እስከ 29 የዕድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶች ላይ ነው፡፡ አዲስ በቫይረሱ ከሚጠቁ ሰዎች መካከል 70 በመቶ ያህሉም በዚሁ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ የዕድሜ ክልል የትኩስነትና የአፍላነት ጊዜ በመሆኑ፣ ከአላስፈላጊ ወሲብ መታቀብ፣ አንድ ለአንድ መወሰንና የመከላከያ ዜዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ከቀድሞ በተሻለ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በወጣቶች ዘንድ አዲስ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለየ በሚፈለገው ልክ ያልቀነሰው በወጣቶች ላይ ነው፡፡
ከ30 ዓመታት በፊት ከ133 ሺሕ በላይ በኤችአይቪ ኤድስ የሚያዙ አዲስ ሰዎች በዓመት ይመዘገቡ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ ቁጥር በዓመት ከ8 ሺሕ በታች ወርዷል፡፡፡ ለቁጥሩ መቀነስም ፖዘቲቭ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን አውቀው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰዳችው፣ በውስጣቸው ያለው የቫይረሱ ልኬት ዝቅ እያለና የማስተላለፍ ዕድላቸው እየመነመነ መምጣቱ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ለኤችአይቪ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት የሚሰጠውን የኤችኤቪ ምርመራ አገልግሎት አሁን ካለበት 73 በመቶ፣ በ2025፣ 95 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡