

ማኅበራዊ ‹‹ካለፈው ስህተታችን እየተማርን ካልሄድን ለመጪው ትውልድ የምናፍርበትን ጠባሳ ጥለን እንሄዳለን›› ቀሲስ…
ቀን: November 27, 2024
በሱራፌል አሸብር
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ጥሪ አቀረበ፡፡ ጉባዔው ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹ካለፈው ስህተታችን እየተማርን ካልሄድን ለመጪው ትውልድ የምናፍርበትን ጠባሳ ጥለን እንሄዳለን›› ሲልም ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስጠብቅና በሰላም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውን ለማረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቋል።
በአገሪቱ ከቀድሞ በበለጠ ሁኔታ እየተባባሱ የመጡትን የፀጥታ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ሕዝቡ በየሃይማኖቱ ስለኢትዮጵያ ሰላም እንዲፀልይ ሃይማኖታዊ መልዕክቱንም አስተላልፏል። ይህንንም በማስመልከት እሑድ ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር አገር አቀፍ የፀሎት ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከግጭት የሚኖር ትርፍ እንደሌለና ለዚህም የትግራይ ክልል ጦርነት እንደ ትልቅ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ ‹‹ካለፈው ስህተታችን እየተማርን ካልሄድን ለመጪው ትውልድ የምናፍርበትን ጠባሳ ጥለን እንሄዳለን፤›› ብለዋል። አክለውም ችግሮችን በፀብ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጉባዔው ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ መስኡድ አደም ለሪፖርተር ሰላም የዘወትር የሃይማኖት ቋንቋ መሆኑንና ሕዝቡ በየእምነቱ ሰላምን መስበክና ማቀንቀን የየዕለት ሥራው ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ጉባዔው በመግለጫው በንፁኃን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ የግድያ፣ የጥቃት፣ የዕገታ፣ የመፈናቀል፣ የዘረፋና መሰል ኢሰብዓዊ ተግባራት በተለይም ደግሞ በቅርቡ በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ሰላሌ አካባቢ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በጥብቅ አውግዟል።
በሥሩ ሰባት የእምነት ተቋማትን ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ጉባዔውን የመሠረቱት በ2003 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል።