የማነ ብርሃኑ

November 27, 2024

ምን እየሰሩ ነው?

በሴቶችና ሕፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ፍቅር ለሕፃናትና ለእናቶች የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመሠረተው በ2007 ዓ.ም. ነው፡፡ በችግር ምክንያት ተገፍተው ከነልጆቻቸው ጎዳና የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን በማንሳት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው እንዲኖሩ የማድረግ ዓላማንም የሰነቀ ነው፡፡ ድርጅቱ ከጎዳና ያነሳቸውን ሕፃናት፣ በሕፃናት መዋያ እያዋለ የምግብ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም በልጆቻቸው ምክንያት ሥራ ከመሥራት ተገድበው በተስፋ መቁረጥና በልመና ተሰማርተው የነበሩ እናቶችንም አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ማርታ ወልደአረጋይ የፍቅር ለሕፃናትና ለእናቶች የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ስለተቋቋመለት ዓላማ፣ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራትና በቀጣይ ዕቅዱ ዙሪያ የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ምን ድጋፍ እየሰጠ ነው?

ወ/ሮ ማርታ፡- ፍቅር ለሕፃናትና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሠረተ አሥር ዓመት ሆኖታል፡፡ ዓላማውም ሕይወት ያልተሳካላቸውና በአስከፊ ችግር ውስጥ ያሉትን እናቶች ከነልጆቻቸው መርዳት ነው፡፡ በተጨማሪም ጤነኛና ወጣት ሆነው በልዩ ልዩ ምክንያት በብቸኝነት የሚያሳድጓቸውን ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሥራ ለመሰማራት አማራጭ ያጡና በየቤቱም ሆነ በየመንገዱ ዕርዳታ በመጠየቅ ተሰማርተው የሚገኙትን በመደገፍ ራስን ማስቻል ነው፡፡ ሕፃናቱንና እናቶቻቸውን ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት በማውጣት፣ ልጆቻቸው በሕፃናት መንከባከቢያ እንዲቆዩና ለእናቶቻቸው ደግሞ የሥነ ልቦና፣ የሕይወት ክህሎትና የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠትና ለሥራ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁስ በማቅረብ ሥራ በመጀመር ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናቱን በሕፃናት መንከባከቢያ የምታቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? በመንከባከቢያው የሚሰጡ ተጨማሪ አገልግሎቶች ምንድናቸው?

ወ/ሮ ማርታ፡- ልመና የወጡና ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶች ሥራ ሠርተው ለመለወጥ ቢፈልጉ እንኳን ልጅ ይዘው ለመሥራት አይችሉም፡፡ ስለሆነም ከእነኚህ እናቶች ሕፃናቱን በመቀበል አራት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረግንላቸው በድርጀታችን እንዲቆዩ እያደረግን ነው፡ ከአራት ዓመት በኋላ ዕድሜያቸው ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚደርስ በመሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲገቡና እናትም በተመቻቸላት የሥራ ዕድል በመጠቀም ከልጇ ጋር አብራ እንድትኖር ይደረጋል፡፡ በሕፃናት መንከባከቢያ አገልግሎት ለሕፃናቱ የምገባ፣ የጤና፣ የአልባሳትና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ተሟልተውላቸው እንዲኖሩ እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለችግር ከተጋለጡ እናቶችና ሕፃናት ሌላ የምትደግፏቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ይኖራሉ?

ወ/ሮ ማርታ፡- ከመካከለኛው ምሥራቅ ዓረብ አገሮች በተለያየ ምክንያት የመጡና መተዳደሪያ የሌላቸው፣ የተደፈሩና በሕመሞች የተጠቁ ሴቶች የሥነ ልቦና ሕክምና በመስጠት አዕምሯቸው እንዲያገግም እንሠራለን፡፡ በመቀጠልም የተለያየ የሙያ ሥልጠና በመስጠት የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ጎዳና ላይ የወደቁትን በማንሳት ሥራ እስኪጀምሩና የራሳቸው ገቢ እስኪፈጥሩ የቤት ኪራይ እየከፈልን በመርዳት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ጎዳና የወደቁ፣ ለልመና የተዳረጉና የተቸገሩ ሴቶችን አሠልጥናችሁ የሙያ ባለቤት የምታደርጉት እንዴት ነው?

ወ/ሮ ማርታ፡- ለእነኚህ ሴቶች፣ የሕይወት ክህሎትና የሥነ ልቦና ሥልጠና የምንሰጠው በራሳችን ባለሙያዎች ነው፡፡ ነገር ግን የሙያ ሥልጠናዎችን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ወደፊት በራሳችን የሥልጠና ማዕከል አሠልጥነን ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ዕቅድ አለን፡፡ ሴቶቹ ከሚሠለጥኑባቸው ዘርፎች መካከልም እንክብካቤ በመስጠት መስክ የቤት ውስጥ እንክብካቤ አገልግሎት፣ የሞግዚትነት፣ የምግብ ሥራና የመኪና እጥበት ይገኙበታል፡፡ በሌሎችም ዘርፎች ሠልጥነው የሙያ ባለቤት በመሆን ራሳቸውን በመቻል ላይ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በእስካሁን ቆይታው ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን እናቶች ከምን ደረጃ እንደሚገኙ የሚከታተልበት አሠራር አለው?

ወ/ሮ ማርታ፡- ድርጅታችን በአሥር ዓመት ጉዞው ውስጥ አንድ ሺሕ ስልሳ ለሚደርሱ እናቶችና ሕፃናት ድጋፍ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙና ወደ ማዕከላችን ላልመጡ 1,400 ለሚደርሱ አቅመ ደካሞች የምገባና የአልባሳት ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በእኛ የታገዙና የተደገፉ እናቶች ዛሬ ላይ የራሳቸውን ገቢ ፈጥረው በራሳቸው የሚተማመኑ ጠንካራ ሴቶች ሆነዋል፡፡ ጎዳና በወደቁበት ወቅት የባከነ ሰውነት፣ ዕውቀት፣ አቅምና ጉልበት በተደረገላቸው ድጋፍ አንሠራርቷል፡፡ ብዙዎች ውስጣቸው የነበረ ኃይል ዳግም ታድሶ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው ቤታቸውን በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ላይ ትናንት የነበሩበትን የጎዳናና የልመና ሕይወት እያስታወሱ ‹ከሰው ተራ› እንድንቆጠር ያደረጋችሁን እናንተ ናቸው ሲሉም ያመሰግኑናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከእነማን ጋር በጥምረት ይሠራል?

ወ/ሮ ማርታ፡- በውጭ አገሮችና በአገር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች የምንሠራቸውን ሥራዎች በማየትና የተነሳንለትን ዓላማ በመረዳት በገንዘብ እየደገፉን ይገኛሉ፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን ስናነሳ በርካታ ቀና ልብ ያላቸው ሰዎች ከእኛ ጋር ነበሩ፡፡ ስለሆነም ከእነኚህ ግለሰቦች ጋር በጥምረት ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮና ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ወረዳዎች ጋር በጥምረት እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ አሥረኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ በተለየዩ ሥፍራዎች የተያዩ መርሐ ግብሮችን አከናውኗል፡፡ እነኚህ መርሐ ግብሮች ምን ነበሩ?

ወ/ሮ ማርታ፡- አሥረኛ ዓመት የምሥረታ በዓላችንን ስናከብር በሆታና ፌሽታ አልነበረም፡፡ በተመረጡ ሐሳቦች ሰዎችን ይጠቅማሉ ብለን ያመንባቸውን ተግባራት በመከወን አክብረናል፡፡ ሳምንት በቆየው በዚህ ክብረ በዓል የምሥጋና ቀን ብለን የረዱንን ወገኖች አመስግነናል፡፡ የቸርነት ቀን፣ የስጦታ ቀን፣ የአደራ ቀን፣ የፅዳት ቀንና የፍቅር ቀን በማለት ደም በመለገስ፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ በፅዳት፣ አካባቢን በመንከባከብና በመሰል ተግባራት ዓላማችንና ራዕያችንን ከሚደግፉ አካላት ጋር በመሆን አሥረኛ ዓመታችንን ዘክረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ልትሠሩ ያቀዳችሁት ምንድነው?

ወ/ሮ ማርታ፡- ፍቅር ለሕፃናትና እናቶች የበጎ አድራጎት ድርጅት በመላ ኢትዮጵያ ቅርንጫፎችን በመክፈት ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችንና ሕፃናትን መታደግ ይፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በአራቱም ማዕዘን በመንቀሳቀስ ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ጥላ ለመሆን እንሻለን፡፡ ለዚህ ዕቅዳችን ስኬት ደግሞ መንግሥትና አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ሁሉ ከጎናችን ሆነው ራዕያችንን እንዲደግፉ ስንልም ጥሪ እናቀርባለን፡፡