
November 27, 2024
በትግራይ ክልል ሕገወጥ የወርቅ ምርት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ሕፃናት በሜርኩሪ ምክንያት፣ እንዲሁም ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለሕጋዊ ወርቅ አምራቾች በተሰጡ ቦታዎች ላይ እስከ 30 ሜትር የዘለቀ የወርቅ ቁፋሮ ላይ በመሰማራታቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው በማዕድን ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በሚሊኒየም አዳራሽ ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢዛና የማዕድን ልማት ድርጅት አማካይነት በቀረበ ‹ቀጣይነት ያላቸው የማዕድንና ልማት ዕቅዶች› በሚል ርዕስ በቀረበ አንድ ጥናት ነው።
የጥናቱ አቅራቢና የኢዛና የማዕድን ልማት ተወካይ አቶ ጉዕሽ ኃይለ ሥላሴ እንደገለጹት፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ 371 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሜሊ አካባቢ ማዕድን በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሕፃናት በሜሪኩሪ ምክንያት ጤናቸው አደጋ ላይ ወድቋል።
የኢዛና ጥናታዊ ጽሑፍ በአሁኑ ወቅት በትግራይ የወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ልማት በስፋት በማኅበራትና በባህላዊ አምራቾች እንደሚካሄድ የሚገልጽ ሲሆን፣ የወርቅ ተንገስተን በተባለ ማዕድንና በመዳብ (ኮፐር) የሕገወጥ ምርት ሒደትና ንግድ መስፋፋቱንም ያስረዳል።
አቶ ጉዕሽ ከወርቅና ከኮፐር ውጪ ተንገስተን› የተባለው ማዕድን በዓለም አቀፍ ገበያ ስትራቴጂካዊ ሀብቶች ተብለው ከሚጠቀሱ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም በመከላከያ ላይ ያተኮሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል ባለው ውድድር እጅግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው ጥናት በትግራይ ክልል በምርት ሒደት የማዕድናት ብክነት 70 በመቶ መድረሱን፣ ሜርኩሪና ሳያናይድ የተባሉ ኬሚካሎች ማዕድናትን ለማውጣት ጥቅም ላይ እየዋሉ በመሆናቸው ምክንያት ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት እየተከሰተ መሆኑን፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ውድመት በተለይም የደን ጭፍጨፋና የአፈር መሸርሸር መስፋፋቱን፣ እንዲሁም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛም መበራከቱም ተገልጿል።
ሕገወጥ የወርቅ ማምረት እንቅስቃሴዎች በአዲ ዳዕሮና በአዲያቦ አካባቢዎች የደን ጭፍጨፋ ማስከተላቸውን፣ በማይህበይ አፅገደ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች እስከ 30 ሜትር ድረስ ጥልቀት ያላቸው ጉድጓዶችን ወርቅ ለማውጣት ቆፍረው መገኘታቸውን፣ ይህም ሕይወታቸውን እስከማጣት ድረስ የሚያደርስ አደጋ ላይ እየጣላቸው መሆኑን፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዝባን ገደና አካባቢ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴዎች የአፈር መሸርሸር እንዲከሰት ማድረጋቸው በጥናቱ ተብራርቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከክልሉ የወርቅ ምርትና ግብይት ጋር በተያያዘ ከኢዛና የጥናት ግኝት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ጉዳዮችን ማንሳታቸው ይታወሳል።
አቶ ጌታቸው በክልሉ እየተከናወነ ያለውን ሥር የሰደደ ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮ በሚመለከት፣ ባለፉት አራት ወራት ብቻ 28 ኩንታል ወርቅ በሕገወጥ መንገድ መውጣቱን ጠቁመው፣ ‹‹ወደ መንግሥት ካዝና የገባ ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ ማዕድናት ለማውጣት ጥቅም ላይ የሚውሉት ኬሚካሎችም ኅብረተሰቡን ዘላቂ ለሆነ ጉዳት እየዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢዛና ማዕድን ልማት ተወካይ አቶ ጉዕሽ ሕገወጥ የማዕድን ማውጣት ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው በሕጋዊ ፈቃድ ሰጪ አካላት ለድርጅቱ በተሰጡ ሥፍራዎች ላይ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል። በድርጅቱ ሥር የሚተዳደረው በክልሉ ብቸኛ የወርቅ አምራች የሆነው ሜሊ የወርቅ ፋብሪካ በጦርነቱ ወቅት ለደረሰበት ውድመት ጥገና ሲደረግለት መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርብ ሳምንታት ሥራ እንደሚጀምርም ተነግሯል።
አቶ ጉዕሽ የፋብሪካውን መልሶ ግንባታ ለማጠናቀቅ የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት፣ ለጥገና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና የመሣሪያ መለዋወጫ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የገጠሙ የውጭ ምንዛሪ እጥረቶች ማጋጠማቸውን፣ ነገር ግን ፋብሪካው በእርግጥም በቅርብ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
‹‹እኛ የምርት ሥራ ለማስጀመር አስፈላጊ ኬሚካሎችን ጭምር ወደ አገር ውስጥ አስገብተናል፡፡ ጥያቄው ሥራ የመጀመር ብቻ ሳይሆን ያልተቆራረጠና ዘላቂነት ያለው ሥራ እንዴት መሥራት እንችላለን የሚለው ነው። ለምሳሌ የመሠረተ ልማት ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው፤›› ብለዋል።
ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ወደ ፋብሪካው የሚደርሰው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር 16 ትንንሽ ከተሞችን አልፎ እንደሚደርስ የገለጹት ተወካዩ፣ ‹‹ይህ ማለት በአንዱ ከተማ የኃይል መቋረጥ ቢገጥም፣ የፋብሪካው ሥራ ላይ ችግር ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ ይህ መፍትሔ ከሚያሻቸው ቀዳሚ ጉዳዩች መካከል አንዱ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኢዛና ከዚህ በተጨማሪ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ደኅንነት መጠበቅ ዋነኛና ቀዳሚ መሆኑን፣ ለክልሉ ማዕድን ዘርፍ ዕድገትና ሕገወጥ ንግዱን ለማስቆም ግዴታ ካላቸው ጉዳዩች መካከል ተጠቃሽ ነው ብሏል።