

የበለፀጉ አገሮች ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ገንዘብ እንዲመደቡ በኮፕ 29 ጉባዔ ወቅት በሰላማዊ ሠልፍ ተጠይቋል
ዓለም ለአየር ንብረት ለውጥ የተመደበው 300 ቢሊዮን ዶላርና የደሃ አገሮች ስሞታዎች
ቀን: November 27, 2024
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአዘርባይጃን ዋና ከተማ ባኩ ሲካሄድ የቆየው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር (Cop-29) ባሳለፍነው እሑድ መቋጫ አግኝቷል፡፡ ድርድሩ በዋናነት ያተኮረው በዓለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየተባባሰ መጥቷል የተባለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመግታት የታለሙ ተግባራትን ለመከወን የሚያስችል በጀት ማቅረብ ላይ ነበር፡፡
በበለፀጉና ኋላ በቀሩ አገሮች ተደራዳሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት የተሞላበት፣ የሐሳብ ልዩነቶች ሽኩቻ የተስተዋለበት ድርድር የተጠናቀቀው የበለፀጉ አገሮች ለታዳጊ አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2035 ድረስ በየዓመቱ 300 ቢሊዮን ዶላር እንዲያቀርቡ የሚለው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው፡፡ ይህ የመዋዕለ ነዋይ አቅርቦት መጠን ከመንግሥታት የሚመነጭ ነው፡፡ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር ደግሞ ከግሉ ዘርፍ ተጠባቂ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ይህ መጠን ከመወሰኑ በፊት ቀርቦ በነበረው 250 ቢሊዮን ዶላር ላይ የታዳጊ አገሮች ተደራዳሪዎች በተለይም ትናንሽ ደሴቶች በመባል የሚታወቁት የተደራዳሪዎች ቡድን አባላት ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር፡፡ እነዚህ ታዳጊ አገሮች በተለይም ትናንሽ ደሴቶች የሚባሉት አየር በካይ የሆነ የካርቦን ልቀት የማያመርቱ ሆነው ሳለ፣ የአየር ለውጥ ገፈት ቀማሽ የመሆናቸው ጉዳይ ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ሲቀርብበት የቆየ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2015 በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለአዳጊና ትናንሽ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥና ጦሶቹን መታገያ በጀት 100 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ተመድቦ ነበር፡፡ የአሁኑ 300 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት ከቀደመው በእጅጉ በልጦ ቢቀርብም፣ 134 ታዳጊ አገሮችን በሚወክል ቡድን ከተጠየቀው አንፃር በ200 ቢሊዮን ዶላር ያነሰ ነው፡፡
ህንድን ወክለው ስብሰባውን ከታደሙት መካከል፣ ሊና ናንዳን በጀቱን ‹‹ብዥታ›› ነው ስትል ገልጻዋለች፡፡ ‹‹መጠኑ ሁላችንም ላይ የተጋረጠውን ትልቅ ችግር ለመጋፈጥ አያስችልም፤›› ብላለች፡፡
የትናንሽ ደሴቶች ጥምረት ሊቀመንበርና የሳሞአ ተወካይ ሴድሪክ ሹስተር ስምምነቱ ከመደረሱ በፊት፣ ‹‹እኛ እዚህ የመጣነው ስምምነት ላይ ለመድረስ ነው፣ ሆኖም እየተደመጥን ያለን አይመስለንም፤›› ብለው ነበር፡፡ ትንንሽ ደሴት አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ አማካይነት ለሚፈጠር የባህሮች ሙላትና ይህንንም ተከትሎ ለሚደርሱ ከፍተኛ የመጥለቅለቅ አደጋዎች ተጋላጭ ናቸው፡፡
እጅግ ኋላቀር የሚባሉ አገሮች ተወካዮች ቡድን መሪ ኢቫንስ ጓጄዋ በበኩላቸው፣ ቀደም ብሎ ቀርቦ የነበረው በጀት ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹ከታዳጊ አገሮች ጋር ምን ማድረግ እንደሚኖርብን እንመክራለን፤›› ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ የኮሎምቢያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ ‹‹በድርድሩ የመጀመርያ ውጤት ደስተኞች ባለመሆናችን ነበር ረግጠን የወጣነው፤›› ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች የአሜሪካውን ልዑክ ጆን ፖዴስታን በተቃውሞ ሲያዋክቡ ተስተውለዋል፡፡ ምድሪቱን በመጥበስ ተወዳዳሪ የሌላት አሜሪካ የሚገባትን እየከፈለች አይደለም ሲሉም ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡
የኮፕ ፕሬዚዳንት ሙክታር ባባዮቭ፣ ‹‹ሁላችንም ከድርድሩ ማለፊያ ውጤት እንፈልጋለን፣ ያ ሳይሆን ባኩን ለቀን አንሄድም፤›› ነበር ያሉት፣ የድርድሩ ጡዘት ጫፍ ነክቶ በነበረበት ባለፈው ቅዳሜ፡፡
የፓናማው ዋና ተደራዳሪ ዩዋን ካርሎስ ሞንቴሬይ ጎሜዝ የበለፀጉ አገሮችን የድርድር ሥልት ሲተቹ እንደተናገሩት፣ ‹‹ሆነ ብለው ያጓትቱታል፡፡ እነሱ በርካታ ሆነው ነው የሚመጡት፣ ያቆዩናል፣ ያደክሙናል፣ ብዥ ሲልብን፣ ሲርበን፣ ሲጠማንና ሲያንጎላጀን ይሰብሩናል፤›› ብለው ነበር፡፡
የበለፀጉ አገሮች የየራሳቸው የፐብሊክ ፋይናንስ እጥረት እንዳሉባቸውና የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የሱዳን፣ እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬን ጦርነቶችና ግጭቶች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ታዳጊ አገሮች የሚጠብቁትንና የተጠየቀውን ያህል ለመመደብ እንዳላስቻላቸው በመከራከር፣ አሁን የተመደበው ካለፉት ዓመታት በእጅጉ የተሻለ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ በቅርቡ ዩክሬይን ሩሲያ ላይ እንድትተኩስ የፈቀዷቸው የረዥም ርቀት ሚሳይሎች እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚሊዮን ያላነሰ እንደሚያወጡ ይነገራል፡፡
የሆነ ሆኖ የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎችና ተሟጋቾች ቢያንስ አንድ ትሪሊዮን ዶላር በጀት ከበለፀጉ አገሮች ወደ ታዳጊና ደሃ አገሮች መተላለፍ እንደሚኖርበት፣ እነዚህ አገሮችም በሚመደብላቸው የመዋዕለ ነዋይ አቅርቦት ልክ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን በየአገሮቻቸው በማከናወን ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይመክራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ከነበሩት ስብሰባዎች በተለየ ኮፕ-29 አሳክቷል የተባለ ሌላው ጉዳይ የካርቦን ገበያን (ንግድ) ይመለከታል፡፡ እነዚህ በካርቦን ንግድ ላይ የተደረጉ ስምምነቶች አገሮች የአየር ንብረት ውጥኖቻቸውን በፍጥነትና በርካሽ እንዲያሳኩ ያግዟቸዋል፣ ይህም የዓለም የካርቦን ልቀትን በዓመት ውስጥ በግማሽ ለመቀነስ የተወጠነውን ለማሳካት የሚደረገውን ሳይንሳዊ ጉዞ ያፋጥነዋል፡፡
ስምምነት ከተደረሰባቸው ሌሎች ጉዳዮች አንዱ ግልጽ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ሪፖርት ሥርዓትን መዘርጋት ይመለከታል፡፡
‹‹አዲሱ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አቅርቦት ግብ ለሰው ልጆች የኢንሹራንስ ፖሊሲ ነው፤›› ሲሉ የተደመጡት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ለውጥ ዋና አስፈጻሚ ሳይመን ስቲየል ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በኮፕ 29 ድርድር ወቅት ከታዩ ለውጦች መካከል ከዚህ ቀደም በበካይ ኢንዱስትሪዎቻቸው ቢታወቁም፣ ገንዘብ ይከፍሉ ያልነበሩ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም ገንዘብ ለማዋጣት መስማማታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
ስምምነት የተደረሰበት አዲስ በጀት ንፁህ ኃይል (Clean Energy) ምርት እያመጣ ያለውን እመርታ ያፋጥናል ብለዋል ሳይመን ስቲየል፡፡ የዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ የታዳሽ/ንፁህ ኃይል ልማት ላይ የሚፈስ የመዋዕለ ነዋይ መጠን በያዝነው ዓመት መገባደጃ ከሁለት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚፈልግ ይገመታል ብሏል፡፡
በባኩ የኮፕ-29 ስብሰባ ከ700 በላይ አገሮች ተወካዮች ሲሳተፉ፣ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪክ ድርጅቶች፣ ተሟጋቾች፣ ሳይንቲስቶች ታድመው ነበር፡፡ (ኢትዮጵያም በፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተመራ ቡድኗ መወከሏ ሲታወቅ፣ ቡድኑ ኢትዮጵያ የአየር ለውጥንና መዛባቶችን ለመከላከል እያደረገች ያለችውን ጥረት እንደ ተሞክሮ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ በድርድሩም በደሃ አገሮች ቡድን ውስጥ ተወክላ አስተዋጽኦ አድርጋለች ተብሏል፡፡
ወደ ንፁህና ታዳሽ ኃይል የሚደረገው ሽግግር እንዲፋጠን የሚደረገው ጥረት ግን ተግዳሮቶች ከወዲሁ እንደተደቀኑበት ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ አምራች አገሮች ሳዑዲ ዓረቢያና አዘጋጇን አዘርባይጃንን ጨምሮ በነዳጅ ምርት እንደሚገፉበት ያሳወቁት ከስብሰባው የመጀመርያ ቀናት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚህ አቋማቸውም ወደ ታዳሽ ኃይል ሊኖር የሚችለውን ሽግግር ተገዳድረዋል፡፡
አሜሪካ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የአየር ለውጥ ድርድር ግዴታዎቿ ልታፈገፍግ እንደምትችል ተፈርቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 20 ቀን 2025 መንበራቸውን የሚረከቡት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› በሚል መርሐቸው አማካይነት አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ሊኖራት የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚቀንስ ወይም የሚሽር ዕርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ሥጋትም አለ፡፡ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2016 ለመጀመርያ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ አገራቸውን ከዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር አስወጥተው እንደነበር ፖለቲኮ በዘገባው አስታውሷል፡፡
እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች ከሆነ ደግሞ፣ ዓለማችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ አስከፊ ድርቆች፣ የውኃ እጥረት፣ ከፍተኛ ሰደድ እሳቶች፣ የባህር ማበጥ (የባህር ጠለል መጠን መጨመር)፣ ጎርፍ፣ የዓለም ሰሜንና ደቡብ ዋልታ ግግር በረዶ ተራሮች መቅለጥ፣ አውደሚ ወጀቦች ብሎም የብዝኃ ሕይወት መመናመን ተጋርጠውበታል፡፡
የዓለም አማካይ የአካባቢ ሙቀት መጨመር መጠንን ከቅድመ ኢንዱስትሪያል በላይ፣ ከሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መጠን በታች እንዲወሰን ማድረግ ይገኝበታል፡፡ ይህ ደግሞ ግብርናን ጨምሮ በሁሉም የልማት መስኮች አስቻይ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ግድ ይላል፡፡
ታዋቂ የዜና ዘገባዎች ምንጭ የሆነው አክሲዮስ እንደዘገበው፣ ያለፉት አሥር ዓመታት በዓለም ታሪክ ዓመታዊ አማካይ የሙቀት መጠን በመጨመሩ በሪከርድ የተመዘገቡበት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2024 ደግሞ ከቀደሙት ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሞቃቱ ዓመት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
መጠን የለሽ የአየር ሁኔታዎች መከሰት ብሎም የአየር ፀባይ ተለዋዋጭ መሆን የዓለም ሙቀት መጨመር ማሳያዎች ሲሆኑ፣ ከመፍትሔዎቹ አንዱ፣ ከካርቦን ነዳጅ ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን እንደሆነ የዘርፉ ሊቃውንት ማሳሰብ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡
እነሱ እንደሚሉት፣ ይህንን ሽግግር በማፋጠን ዕውን ማድረግ ማለት፣ የአጭር ጊዜ ጫናዎችን በመቋቋምና አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል የረዥም ጊዜ ተፈላጊ ለውጥ ላይ መድረስ ነው፡፡ የኃይል ደኅንነትን፣ አቅርቦትንና መሠረተ ልማቶችን ማጠናከርና በዚህም ታይቶ በማይታወቅ መጠን እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ማርካት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥርት ያለ ዓለም አቀፋዊ አካሄድ እንደሌለ የሚናገሩም በርካቶች ናቸው፡፡
ለአሁኑ ታዲያ፣ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአዘርባይጃን ዋና ከተማ ባኩ የተሰበሰቡ የዓለም የፖለቲካ መሪዎችና የዘርፉ ሊቃውንት የበለፀጉ አገሮች ለደሃና ለታዳጊ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያና ተፅዕኖውንም መቀነሻ የሚሆን የ300 ቢሊዮን ዶላር በጀት ለማቅረብ ሲስማሙ ታዝበዋል፡፡ በተመደበው ገንዘብ ማነስ ቢያዝኑም፣ ታዳጊ አገሮቹ የያዙትን ይዘው ማልቀስ ተገደዋል፡፡ አሁን ጥያቄው የበለፀጉት ቃል የገቡትን ያህል በጊዜው ያቀርባሉ ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመጪዎቹ ዓመታት የሚታይ ይሆናል፡፡
በባኩ በተካሄደው ዓመታዊ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ወቅት ከወጡ ሪፖርቶች መካከል፣ የአገሮችን የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ደረጃዎችን አመላካች የሆነው ይገኝበታል፡፡ በዚህም አመላካች (Climate Change Performance Index) መሠረት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ቦታዎች ክፍት የተተው ሲሆን፣ ዴንማርክ አራተኛ ደረጃ ስትይዝ ኔዘርላንድስ አምስተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ ዋናዎቹ በካይ አገሮች የሆኑት ቻይናና አሜሪካ 55ኛ እና 57ኛ ደረጃ ላይ በመገኘት አየር ለውጥን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት በሚጠበቅባቸው መጠን አለመሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎች በቁጥርም በኃይለኝነታቸውም እየጨመሩና እየከፉ የመጡ ሲሆን፣ የሚያደርሱት ጥፋትም በገንዘብ ሲተመን እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 በአሜሪካ በርካታ የቶርኔዶና የንፋስ ወጀብ ክስተቶች እስከ 500,000 የሚሆንን ሕዝብ ለጊዜው የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥባቸው አድርገዋል፡፡ በምዕራባዊ ካናዳ ከፍተኛ ሰደድ እሳት ተከስቶ፣ 250,000 ካናዳውያን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሲያስገድድ፣ አራት የእሳት አደጋዎች ተፋላሚያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በኤፕሪል 2024 ለወትሮ ደረቅና በረሃማ የሆነችው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በከባድ ዝናብና ጎርፍ ተመትታለች፡፡ በቅርቡም በበረሃማዋ ሳዑዲ ዓረቢያ የበረዶ ክስተት ተስተውሏል፡፡ በብራዚል የሪዮ ግራንዴ ደ ሱል ግዛት በኤፕሪል መጨረሻና በሜይ መግቢያ ለአሥር ቀናት በወረደ ከባድ ዝናብ 100 ሰዎች ሞተዋል፣ 130 የሚሆኑ የደረሰቡት አልታወቀም፣ 400ዎቹ ደግሞ ቆስለዋል፡፡
ዘንድሮ በታይላንድ በደረሰ የሙቀት ወላፈን 30 ሰዎች ሲሞቱ፣ ተመሳሳይ የሆነ ክስተት ህንዳውያንን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ከመሄድ እንዲቆጠቡ አድርጓል፡፡ ዝርዝሩ ተቆጥሮ የሚዘለቅ አይደለም፣ ጉዳቱም እንደዚያው፡፡
- ጥንቅር በአዲስ ጌታቸው