ልናገር “የሕግ ያለህ!” ወይስ “የሕግ አስፈጻሚ ያለህ?”

ቀን: November 27, 2024

በአ. ሞ.

እሠራበት በነበረውና ሰሞኑን የኢቢሲ “ዓይናችን” ፕሮግራም ላይ “የሕግ ያለህ” በሚል ርዕስ የድርጅቱ አመራሮች ከአንዲት ነጋዴ ጋር በመመሳጠር የድርጅቱንና የመንግሥትን የግዥ መመርያ ከእነ አዋጁ በመጣስ መንግሥትን ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተው የእነሱን ኪስ የሞላውን ግዥ መፈጸማቸውን ስመለከት፣ ከአሥር ዓመት በፊት በድርጅቱ ውስጥ የነበሩትና አሁንም እዚያው የተወሰኑ በአመራርነት የሚገኙ ግለሰቦች የፈጸሙት የሌብነት ድርጊት ይህንን አስጻፈኝ፡፡

በወቅቱ እኔና የድርጅቱ የሕግ ኃላፊ ከፀረ ሙስና ክፍሉና ከሠራተኞች ማኅበር ጋር የተፈጸመውን ሌብነት ታግለን ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጠቆምን፡፡ ጉዳዩ ከማስረጃ ጋር ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደርሶ ጋዜጠኞች መጥተው ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ለሕዝብ ሳይተላለፍ ቀረ፡፡ ጉዳዩ ሲታፈን ዘግይቶም ቢሆን በወቅቱ የድርጅቱ ቦርድ አባል የነበሩ ሰው፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊና አሁን ስማቸውን የማልገልጸው የክልል ፕሬዚዳንት የሆኑ ግለሰብ በጋብቻ ዝምድና የቀረቡ ሆነው ተገኝተው ምክንያቱን አወቅን፡፡

በግለሰብ አቅም መታገሉን የምንችለው ስላልነበረ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. የታተመው “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ጉዳዩን በሰፊው እንዲዘግበው አደረግን፡፡ የድርጅቱ አመራሮች ግን እኔን በቀጥታ ባያገኙኝም ጓደኞቼን ከድርጅቱ በማሰናበት ተበቀሉ፡፡ የፍትሕ መሥሪያ ቤት እስከ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ቢከራከርም የተለያዩ የበቀል ዕርምጃዎችና በጠቋሚነት የሚጠረጠሩ ሠራተኞችን ማኅደር የማበላሸት ዕርምጃ አላስቀረም፡፡

ፀረ ሙስና ትግል ውስጥ የሚገቡ ሰዎች እንዲህ ሲሳደዱ ያዩ አመራሮች እንዲስተካከሉ መጠበቅም ሆነ፣ ሌሎች ሠራተኞች ዋጋ ከፍለውና ማንነታቸውን ደብቀው ሌብነቱን ይታገላሉ ብሎ መጠበቅ የማይታሰብ ነው፡፡ በሌብነቱ የሚሳተፉ ኃላፊዎች የጠረጠሯቸውን ሠራተኞች በዝውውርና በስንብት በዕድገት ክልከላ በመቅጣት “እነሱን ያየ ይቀጣ” የሚሉት ለበቀል ዕርምጃቸው ከበቂ በላይ ጊዜ የሚሰጥና በቀልን የሚፈቅድ አሠራር ስላለ ነው፡፡ የአገራችን ፀረ ሌብነት ትግል ጠቋሚው የሚደበቅበት ማፈርና መሸሽ የሚኖርበት ደግሞ የሚያሳድድበት ነው፡፡

ሕጉ ነው የሌለው ወይስ የሕግ አስፈጻሚው?

በምሳሌ “ነገርን ከሥሩ” በማለት ከላይ ያወሳሁትን ኩነት የጠቀስኩት ‹‹ዓይናችን›› ፕሮግራም ጉዳዩን ካስተላለፈ በኋላ፣ እንደዚያን ጊዜው ጠቋሚ ናችሁ ተብለው የሚጠረጠሩትን ሰዎች የድርጅቱ አመራሮች በዝውውርና በስንብት እንደለመዱት ይጎዷቸው ይሆን? ወይስ ሌብነትን እንደሚጠየፍ የነገረን መንግሥት ሰዎቹን ለሕግ አቅርቦ ማስተማሪያ ያደርጋቸው ይሆን? የሚለው ጥያቄ ምላሽ እየጠበቀ ነው፡፡ የዓይናችን ፕሮግራም አዘጋጆችም በፀረ ሙስና ጥናት አረጋግጠው የዘገቧቸው ጉዳዮች የደረሱበትን ከሚመለከታቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል እንጂ ‹‹ቄሱም መጽሐፉም ዝም›› ሊሉ አይገባም፡፡

ከመረጃዎቼ እንደተረዳሁት ከሆነ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ አስቸጋሪ ሒደቶች የነበሩት ከመሆኑም በላይ፣ አሁን በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙት በተለይ የፀረ ሙስና ክፍል ዋና ሥራው ሌብነትና ብልሹ አሠራሮችን መታገልና ማጋለጥ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዲቀር ከእያንዳንዱ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተጻፉ በሐሰተኛ መረጃ ከተሞሉ ደብዳቤዎች ጀርባ ከሚገኘው የድርጅቱ የሕግ ባለሙያና የጡረታ ኮሚሽን የረሳው ድርጅት ስለሆነ፣ የጡረታ ዕድሜያቸው ካለፈው የኦዲት ክፍሉ ጭምር ሥራቸውን በአግባቡ ሠርተው ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፡፡

ከላይ እስከታች የተንሰራፋው ሌብነት ዋና አድራሻቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደ መሆናቸው፣ ትግሉን ማድረግ ያለበትና የትግሉ ግንባርም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመሆናቸው ሙስናን በስሙ ጠርተን እንድንታገለው አደራ ያሉን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ያስጀመሩት ሪፎርም ከዳር ባይደርስም፣ በዚህ ልክ ተገልጾ በቴሌቭዥን ለሕዝብ የተላለፈ ፕሮግራም ተሠርቶ እስካሁን አንድም ሰው ተጠያቂ አለመደረጉ አስደንጋጭ ነው፡፡

ነገሩን ይበልጥ አስደንጋጭ የሚያደርገው ደግሞ በዋነኛነት ይኼንን ሌብነት የመሩት ሰዎች ሲካፈሉ መጣላታቸው የሚጠበቅ ነውና ድርጅቱን በመልቀቅ፣ ወይም በሐሰተኛ መባረርና በጡረታ ስም ያለ ምንም ተጠያቂነት የያዙትን እየያዙ እንዲያመልጡ የሚፈቅደው መሰናበት የሚኖርበት ቦርዱ ራሱ በመፍቀዱ ነው፡፡ በቅርቡ የደረሰኝ ሌላ መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ደግሞ በእነዚሁ ሰዎች የግል ጥቅምን ብቻ የማሳደድ አባዜ ከድርጅቱ አቅም በላይ የሆነ ግብር የተጣለበት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡

በአገር ደረጃ የተቋቋመው ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ ብዙ ሲጠበቅበት የት እንደገባ ባይታወቅም፣ እንዲህ ዓይነቶቹን የመንግሥት ድርጅቶች በደንብ መመርመርና ተዘግቶ የኖረው ምቹ ቀጣና መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ አለሁ ለማለት ያህል ድርጅቱ ቦርድ ቢኖረውም እኔ ሳውቀው ከበፊት ጀምሮ ሥራ አስቀጣሪ ኤጀንሲ ይመስል አባላቱ እከሌን ቅጠሩልኝ ይላሉ እንጂ፣ ድርጅቱን ተመልክቶት እንኳን ስለማያውቅ ዛሬም እጅና ህሊናው ያደፈውን ማኔጅመንት በድርጅቱ ውስጥ እንዲቀጥል የፈቀደውና ዕርምጃ እንዳይወሰድ የተከላከለውም ሆነ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባቀረበው መሠረት ዕርምጃ ያልወሰደው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡

እኔ እዚያ ድርጅት ውስጥ በነበርኩበት ወቅት የግብርና ሚኒስቴር በበላይነት ይቆጣጠረው የነበረና ለአገራችን ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የሚመጡ የዕርዳታ እህሎችን ለተፈናቃዮች የሚያደርስ ድርጅት ሲሆን በኋላም የአደጋ ሥጋት ኮሚሽን ተረክቦታል፡፡ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ለደንቡ ያህል ተቆጣጣሪ ተብሎ ቢሰየምም፣ ድርጅቱ በመንግሥት የልማት ድርጅትነት እየታወቅ እንኳን የአወቃቀር ግልጽነት ችግር ያለበትና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታ ኤጀንሲም ሆነ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አያውቁትም፡፡

ሕጉ ነው የሌለው ወይስ ተቋማቱ?

እንደ ቀደምትነቷ አገራችን ኢትዮጵያ ከዚያኔው ሕገ ልቦና ጀምሮ እስከ እስካሁኑ ድረስ ብዙ ሕጎች አሏት፡፡ የሕግ ችግር አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ሕግን በመፈጸምና በማስፈጸም በኩል ግን ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ሕጎቹ የሚፈጸሙት እየተዘረዘሩ ለአፈጻጸም በሚሄድላቸው ተቋማቶች እንደ መሆኑ፣ የተቋሞቹን ክትትልና ውሳኔዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ድርጅት እንዲህ መበላሸት ከዋና ምክንያቶች አንዱ የተቆጣጣሪው አካል ቸልተኝነት ሲሆን፣ የጀመረውም ዕርዳታ ማስተባበሪያ ሲባልና ፍርድ ቤት እየተመላለሱ የሚገኙት የቀድሞ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የሚመሩት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና የድርጅቱ ቦርዱ ቢሆኑም፣ ለአገራችን ተፈናቃዮች ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የሚገኙ እህሎች ሽያጭና ዘረፋ ከግለሰቦች ደረጃ አልፎ ባለሥልጣን ጋር መድረሳቸውና በዚህም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዕርዳታዎችን እስከ ማቆም መድረሳቸው ይታወቃል፡፡

ይኼንን ጉዳይ ማሳያ ለማድረግ ያህል ሌብነትን እንዲከላከል ሥልጣን የተሰጠው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማው ከደረሰውና ጥናቱን ካደረገ በኋላ የግዥ ሒደቱ እንዲቆም አመራሮቹን ያሳወቀው በቃል መሆኑን መረጃዎቼ ያመለክታሉ፡፡ በኮሚሽኑ መጽሔት ላይም አለ፡፡ ግዥው ከተጠናቀቀ በኋላ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቴሌግራም መጽሔት ጉዳዩ ከታወቀ በኋላ የተከታተልኩ እንደ መሆኔ የተገዙት የድርጅቱ መኪኖች ጉዳይ ዕልባት እስኪያገኝ እየተባለ፣ አሁን መንግሥት እንዲያጣ ተደርጓል ከተባለው የገንዘብ መጠን በላይ በሚያሳጣ መልኩ ለረዥም ጊዜ ያለውሳኔ ያለሥራ ቆመው ግማሾቹ በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ ገቡ፡፡

እንደጠቀስኩት በድርጅቱ ውስጥ የሚሠራው እያንዳንዱ ነገር ሰንሰለቱ ብዙዎችን እስከ ላይ የሚያነካካ እንደ መሆኑ ፍርድ ቤት ተንከራቶ ይምጣ ተብሎ እኛ በወቅቱ ከድርጅቱ ስንሰናበት፣ በዚህም ከኃላፊዎች ኪስ ሳይሆን ከመንግሥት ካዝና ሲከፈለን ተጠያቂ ያልነበረው በሕግ አለመኖር ሳይሆን በሕጉ አስፈጻሚ አለመኖር ነበር፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ሕጉ ቢኖርም ከዚያን ጊዜው በተሻለ ኹናቴ ለሕዝብ ቢገለጽም ማስረጃ እያለ ሕጉን የሚያስፈጽም ጠፍቷል፣ ቦርዱም እነዚህን ሰዎች አስቀጥሏል፡፡ ስለዚህ የሕግ ያለህ ሳይሆን የሕግ አስፈጻሚ ያለህ የተቋማት ያለህ የተጠያቂነት ያለህ ነው፡፡

ሕጉ ነው የሌለው ወይስ ተጠያቂነቱ?

በዚያኔው አወቃቀር በግብርና ሚኒስቴር የታቀፈውን የዕርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የመሩት አቶ ምትኩ ካሳ የታሰሩት፣ ኤልሻዳይ የተባለውና እስከ ዛሬ ድረስ ያልተገለጸው ድርጅት በተግባር የሌሉና በሪፖርት በሚቀርቡ ተፈናቃይ ተረጂዎች ስም የሚወጣው የዕርዳታ እህል እየተሸጠ ከሽያጩ ከተገኘው ገቢ ላይ ቅንጡ የግል መኖሪያ ቤት አሠርተዋል በሚል ጥርጣሬ ነው፡፡ ከድርጅቱ አሽከርካሪዎች ውስጥ በዚህ በኩል የተሳተፉ ሲኖሩ ሐሰተኛ ተረጂዎችን በመፍጠር በኩልም የመስክ ሠራተኞች በተባባሪነት ተጠርጥረዋል፡፡ አቶ ምትኩ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጻፉ ደብዳቤዎች ነው ዕርዳታ እህሉ እየወጣ የተሰጠው ቢሉም፣ የስንዴ ፖለቲካው ብዙዎችን ያነካካልና በሕግ ስለተያዘ ትተነው ይኼንን ማንሳት ያስፈለገኝን ነጥብ ልግለጽ፡፡

በዚህ ድርጅት እኛም ሆንን እስካሁን የሚገኙ ሠራተኞች የሚቃወሙት በድርጅቱ ውስጥ የመሥሪያ ቢሮ ሳይቀር ለግለሰቦች ተሰጥቶ ሲሠሩ የቆዩና ለረዥም ዓመታት ድርጅቱ መሥራት የሚችለውን ሥራ የሚሠሩ የግል ትራንስፖርት ድርጅቶች ስላሉ ነው፡፡ ለተወሰኑ የዕለት ደራሽ አመራሮች ከእያንዳንዱ ጭነት በሺዎች ኮሚሽን እየቆረጡ ዛሬ ባለብዙ ሚሊዮን ብሮችና ባለብዙ ከባድ መኪና ባለቤቶች ሲሆኑ፣ ዕለት ይህ ድርጅት ግን ጠያቂ የሌለው የመንግሥት በመሆኑ ቢሮዎቹም እኛ ትተነው ስንሄድ ካለበት ሁኔታ ብሶበት አለ፡፡

የደረሰኝ መረጃ እንደሚያሳየው ድርጅቱ ከገቢዎች ሚኒስቴር ከአቅሙ በላይ ግብር ተጠይቋል፡፡ ይኼ ግብር የተጠየቀው ‹‹ሰብ ኮንትራክት›› በሚባል ሥራ ምክንያት ሲሆን፣ ያኔ እኛ ስንቃወም ሲያሳድዱ የነበሩት ዋና ኃላፊ መንግሥት የሰጣቸውን አደራ ባለመወጣት መጠየቅ ሲገባቸው ያለ ምንም ተጠያቂነት በጡረታ እንዲሸሹ ተደርጓል፡፡ ግብሩ የተከመረው ድርጅቱ አትርፎበት ሳይሆን በኃላፊውና በጓደኞቻቸው የድርጅቱ መኪኖች በአሻጥሮች እየቆሙ የተመሳጠሩ ሁለትና ሦስት የግል ድርጅቶች፣ ለሠሩትና ላቀረቡት በገቢዎች የማይታወቅ ደረሰኝ ነው፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከፀረ ሙስና ጋር በመሆን በድርጅቱ ውስጥ ያሉትን ኦዲትና ፀረ ሙስና ክፍሎች በመተው፣ የዚያን ድርጅት አራትና አምስት ዓመት እንኳን ወደኋላ ሄደው ማየት ቢችሉ የሚወጣው ጉድ ብዙ ነው፡፡ በአንድ የመንግሥት ድርጅት ውስጥ ጨረታ ወጥቷል እየተባለ አንድና ሁለት ድርጅቶች ብቻ ጨረታውን ሲያሸንፉ፣ የድርጅቱ የኦዲት ክፍል የሕግ ክፍል የፀረ ሙስና ክፍል ጥያቄ የማያቀርቡበት ሁሌም ኋላ እንዲቀር፣ ሁሌም ሠራተኞች እንዳይቆዩና ሚስጥር እንዳያውቁ የሚፈለግበት ብቸኛ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ ቦርድም ይህንን ጥያቄ የማያቀርብበትና አሠራሩን የማይፈትሽበት ምክንያት ከጥቅም ትስስር የተነሳ ነው እንጂ ጉዳዩ ከመሰወሩ አይደለም፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ አሁን በያዘው ጥናትና ምርመራ ላይ የአመራሮቹን ሀብትና ንብረት፣ በተለይ የባንክ እንቅስቃሴያቸውና ከገቢያቸው ጋር ቢፈትሹ ግኝቱ እንደሚሰፋ ይታወቃል፡፡ ምን ላይ እንደደረሰ ባላውቅም ለፀረ ሙስና ኮሚሽን እኔም የጠቆምኩት ነበር፡፡

ሌብነት ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲቀንስ እንሠራለን በማለት ለምክር ቤት ንግግር ያደረጉት አዲሱ ፕሬዚዳንታችን ቃል በተግባር እንደሚፈጸም ማሳያዎች የሕግ አስፈጻሚውን መከታተል ሲሆን፣ በዚህ ድርጅት ማኔጅመንት አባላትና በሠራተኛ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ በድርጅቱ ፀረ ሙስና ክፍል፣ በሕግ ክፍሉና በኦዲቱ ተባባሪነት በተጣሰው ሕግ ተጠያቂ ጠፍቷል፡፡

ድርጅቱ በድጋሚ በውድቀት አፋፍ ላይ ስለሆነ እንደ ከዚህ በፊቱ በገንዘብና በባለሥልጣን ትውውቅ ከተደፋፈነ ብሎም የተሳተፉት በሙሉ ከነጋዴዋ ጭምር አብረው ካልተጠየቁ፣ ሕግም የሕጉ አስፈጻሚውም እያሉ የሌሉ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች በትኩረት በእንዲህ ዓይነቶቹ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ለዘመናት በዝምታና በድብቅ የሚደረገውን ስርቆት እንዲመረምሩ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ዋና ኦዲተርም በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎቻቸው በጥቅማ ጥቅም እየተደለሉ ዝም ሲሉ የሕግ ኃላፊ ጭምር እየተከታተሉ ዕርምጃ እንዲወስዱ እጠይቃለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡