

ፈንቴ አምባው (ፕሮፌሰር)
ዜና በአማራ ክልል ለጤና ዘርፍ ሽግግር ከሚያስፈልገው 15 ቢሊዮን ዶላር በጀት 13 በመቶ…
ቀን: November 27, 2024
- በጦርነቱ ወቅት የደረሰውን ጉዳት አያካትትም ተብሏል
በአማራ ክልል ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለጤና ዘርፍ ሽግግር ከሚያስፈልገው 15 ቢሊዮን ዶላር በጀት ውስጥ፣ ከመንግሥት የተገኘው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወይም 13 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ማክሰኞ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በጦርነት እየደረሱ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲደረግ ነው፡፡
ለውይይቱ መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፈንቴ አምባው (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት የአማራ ክልል ጤና ቢሮና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረጉት ጥናት ከመጀመሪያው ዙር የሰሜን ጦርነት ከደረሰው ጥፋት በተጨማሪ 969 የጤና ተቋማት ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡
በክልሉ ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ውድመት ባይከሰት እንኳን ለጤና ዘርፉ ሸግግር 15 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልግ እንደነበር፣ ነገር ግን በወቅቱ ከመንግሥት የተገኘው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በነበረው ጦርነት በ40 ሆስፒታሎችና በ443 የጤና ጣቢያ ተቋማት ላይ ውድመት መድረሱንና አምስት በመቶ ያህሉን ብቻ መልሶ ማቋቋም እንደተቻለ፣ የተቀሩትን ማዳረስ ከመቻሉ በፊት በክልሉ ውስጥ ግጭት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከ48 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በክልሉ በርካታ የሕክምና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ፣ ማኅበረሰቡ ከባድ ችግር ውስጥ መውደቁን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ድረስ ክልሉ ከግጭት መውጣት ባለመቻሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብና የቁሳቁስ ዕርዳታ በአስቸኳይ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በግጭት ምክንያት የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን አንዳንዶች ደግሞ በሥጋት ምክንያት መዘጋታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ በተፈጠረው ችግር ምክንያት 4.7 ሚሊዮን ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መሠረት 4,870 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና 5,379 ትምህርት ቤቶች ደግሞ መውደማቸው ገልጸው፣ በክልሉም ድርቅና የተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በመከሰታቸው ሕዝቡ ከባድ ችግር ውስጥ መውደቁን አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት የጤና ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ዕድል እንዳልሰጣቸው፣ በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት ፎረም ዋና ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በክልሉም ከተወሰኑ የጤና ተቋማት የመጣ ሪፖርት በማሳያነት በማቅረብ ከ1,100 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ከሥራቸው መፈናቀላቸውን ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም ሕይወታቸው ማለፉን አስረድተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የጤና ተቋማትም ሆኑ የጤና ባለሙያዎች ነፃ ሆነው ማገልገል አለባቸው የሚለውን በተግባር እንዲታይ አምባሳደሮች፣ የረድኤት ድርጅቶች፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚኖባቸው አስረድተዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት የነበረው የድጋፍ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸው፣ በወቅቱ የነበረውን ጥረት ለማስቀጠል ዓለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖባቸዋል ብለዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ወደ ነበሩበት ለመመለስ እስከ 36 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል መባሉ ይታወሳል፡፡
የወደሙ የጤና ተቋማትንና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ በዝርዝር የሚያሳይ የተጠና ነገር ባይኖርም፣ በዳሰሳ ሲታይ በመንግሥት የተመደበው የድጎማ በጀት ተቋማት መልሶ ለመገንባት በጣም አነስተኛ እንደሆነ ተገልጾ ነበር፡፡