
November 27, 2024

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑት
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ በገበያ መመራት ከጀመረ በኋላ፣ ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ዕዳ ከብር አንፃር እንዳናረበት ገለጸ፡፡
የብር አቅም ከዶላር አንጻር ከተዳከመ በኋላ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለማስፋፊያ ከወሰደው ብድር በተጨማሪ፣ ለመሠረተ ልማት ኪራይ በሚያወጣው ወጪ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ከዚህ ቀደም ሲገለጽ ነበር፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑት ኩባንያው በኢትዮጵያ ለሚሰጠው አገልግሎት ደንበኞች በብር እንደሚገለገሉ፣ ነገር ግን ኩባንያው በዶላር የተበደረው ብድር እንዳለበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለአብነት የኩባንያው አንደኛው ባለድርሻ የሆነው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (International Finance Corparation-IFC) 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡
በሰኔ 2016 ዓ.ም. 100 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የምንዛሪ እኩሌታ አምስት ቢሊዮን ብር እንደነበር፣ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ ከተወሰነ በኋላ ዕዳው ከአምስት ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ማሻቀቡን፣ ምንም እንኳን ኩባንያው ባለበት የውጭ ምንዛሪ ዕዳ ላይ ለውጥ ባይኖርም በምንዛሪው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የምንዛሪ ለውጡ በኩባንያው የፋይናንስ ሪፖርት ላይ መገለጽ ስለሚገባው ኩባንያው በናይሮቢ ባቀረበው አፈጻጸም ላይ መገለጹን፣ ያለውን ዕዳ ለመክፈል ከዚህ ቀደም ከነበረው እጥፍ የሆነ ብር እንደሚያስፈልግ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡
‹‹በአጭር ጊዜ ሲታይ ተፅዕኖው አሉታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሳፋሪኮም ብቻ ሳይሆን ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች በዶላር የተበደሩ ኩባንያዎችን የሚመለከት ነው፤›› ሲሉ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ነገር ግን ጉዳዩ አሳሳቢ የሚባል እንዳልሆነና ኩባንያው ማትረፍ ሲጀምር በረዥም ጊዜ የምንዛሪ ለውጡ ብርን ወደ ዶላር በመቀየር ትርፍን ማከፋፈል የሚያስችለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኮካ ኮላ፣ ሃይኒከንና ቢጂአይ የመሳሰሉ ኩባንያዎች የተከማቸ ትርፍ ቢኖራቸውም ላለፉት አምስትና አሥር ዓመታት ኢንቨስትመንቱን ለመመለስ (ወደ ውጭ መውሰድ) የሚችሉበት አሠራር እንዳልነበረ፣ አሁን ግን የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲተመን በመወሰኑ ኩባንያዎቹ የተወሰነውን ትርፍ ወደ ውጭ ማውጣት እንዲችሉ መፈቀዱን፤ አሁን ባይሆንም በቀጣይ ሳፋሪኮምም ከዚህ አሠራር ተጠቃሚ እንደሚሆንና በዚህ ሪፎርምም ደስተኛ መሆኑን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስረድተዋል፡፡
‹‹የአካውንቲንግ አሠራር ስለሆነ በአጭር ጊዜ ያለብን ብድር በብር ሲታይ እጥፍ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ይኼ በኢትዮጵያ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ በረዥም ጊዜ ስኬታማ እንደሚሆን ያለንን ቁርጠኝነትና እምነት አይለውጠውም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የደንበኞቹን ቁጥር ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን እንደሚያደርስ የገጸው ሳፋሪኮም፣ ይህም ወደ ትርፋማነት የሚያንደረድረው መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሦስት ሺሕ ያህል ማማዎቹን ከአንድ ዓመት በኋላ አራት ሺሕ እንደሚያደርስ ተብራርቷል፡፡
ከነሐሴ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከአጭር ጊዜ ዕቅድ አፈጻጸሙ እስካሁን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደንበኛ ያፈራ ሲሆን ከሦስት ሺሕ በላይ ጣቢያዎችን ገንብቷል፡፡ ሳፋሪኮም ለቴሌኮም ኦፕሬተርነት እንዲሁም ለሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፈቃድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ከፍሏል፡፡ በአጠቃላይ ለኔትወርክ ግንባታ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ አድርጓል፡፡
‹‹እያደረግነው ያለው ኢንቨስትመንት ለዛሬ አይደለም ለረዥም ጊዜ እንጂ፡፡ አሁን ጥሩ የገበያ መነቃቃት እያገኘን ነው፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አፍርተናል፡፡ ከገቢ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት ያገኘነው ከቀደመው ተመሳሳይ ጊዜ እጥፍ ነው፤›› ሲሉ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የተገባው ኔትወርክ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ደንበኞችን መሸከም እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
በቀጣዮች 12 ወራት የጣቢያዎቹን ቁጥር ከሦስት ሺሕ ወደ አራት ሺሕ ለማሳደግ ወጥኛለሁ ያለው ሳፋሪኮም፣ ገና በጅማሮ ላይ ሆኖ ኪሳራ ማስመዝገብ የሚጠበቅና ይህም ትልቅ ኔትወርክ በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ የሚያግጥም ነው ብሏል፡፡ ነገር ግን በመጪዎቹ ከ12 እስከ 18 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የአሁኑን ስድስት ሚሊዮን የደንበኞች ቁጥር ወደ 15 እና 20 ሚሊዮን እንደሚደርስ፣ 15 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት ሲችል ደግሞ ትርፍ ማስመዝገብ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
በረዥም ጊዜ ትርፍ የማግኘት ጉዞ ውስጥ ኩባንያው ከፍተኛ የኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን 46 በመቶ የሕዝብ ተደራሽነት በበለጠ መጠን እንደሚጨምር አስታውቋል፡፡