ሊባኖስ በሚገኝ የኢራን ኢስላሚክ ሪፐብሊክ መስራች ሆኑት ሩሆላህ ኳሚኒ ምስል ፊት ለፊት የሚያለቅሱ እናት

ከ 6 ሰአት በፊት

የእስራኤል መንግሥት በሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር የሚያደርገው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት መቆሙን አስታውቋል። እስራኤል ካለፈው ዓመት መስከረም 26 ጀምሮ በጋዛ የሚገኘውን ሐማስን ጨምሮ በሁለት ግንባሮች ጦርነት ውስጥ ቆይታለች።

በአካባቢው የተፈጠረው የጦርነት መባባስ በመካከለኛው ምሥራቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ሊያስጀመር ይችላል በሚል ፖለቲከኞች እና ተንታኞች ያላቸውን ፍራቻ እንዲገልጹ ምክንያት ሆኗል።

በሊባኖስ የተኩስ አቁም ሲታወጅ እስካሁን በጋዛ አልሳካ ያለው ለምን ይሆን በሚል በአካባቢው የሚገኙ የቢቢሲ ባለደረቦች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ካሪን ቶርቢ፣ የቢቢሲ ኒውስ አረቢክ ባልደረባ ከቤሩት

እስራኤል በሊባኖስ ከሚገኘው ሄዝቦላህ እና በጋዛ ከሚገኘው ሐማስ ጋር የገባችበት ጦርነት የተለያየ መልክ አለው ነው። ጋዛ በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያለች ሲሆን፣ ሊባኖስ ሉዓላዊ አገር ነች። ምንም እንኳን በአንድ ወቅት እስራኤል ሊባኖስን ተቆጣጥራ ነበረ ቢሆንም በሄዝቦላህ እና በሌሎች ኃይሎች ትብብር ለቅቃ እንድተወጣ ተደርጋለች።

ምንም እንኳን ግዙፍ ወታደራዊ አቅሟ እና በአየር ኃይል የበላይነት ቢኖራትም እስራኤል ባደረገችው የምድር ዘመቻ ሊባኖስ ውስጥ ኪሳራ ሲደርስባት ቆይታለች። ከሁለት ወራት ገደማ በኋላም በደቡብ ሊባኖስ ያሉ ከተሞችን መቆጣጠር አልቻለችም።

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሄዝቦላህ የሚፈጽምባትን የሮኬት ጥቃትን ማስቆም እና የቡድኑን ድንበር ዘለል ጥቃት የመፈጸም አቅምንም ማውደም አልተቻላትም።

ሄዝቦላህ ጥቃቱን አጠናክሮ በእስራኤል ዋና ዋና ከተሞች ያለውን የነዋሪዎች ሕይወት በማወክ ጉዳት ማድረስም ችሏል።

ይህ የሆነው የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ የሚደርስበት ኪሳራ እየጨመረ በሄደበት ወቅት ነው።

እስራኤል የተፈናቀሉ ነዋሪዎቿ ወደ ሰሜን የሚመለሱበትን ሁኔታም መፍጠር አልቻለችም። ይህ ደግሞ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ በማሳመን ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በዚህ ላይ ደግሞ የእስራኤላውያን ጦር መዳከም እና ተጠባባቂ ሠራዊትን ወደ ግጭት ማስገባት የሚያስከትለውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖም ማሰብ ያስፈልጋል።

“እስራኤል ጋዛ ውስጥ በቀጣይ ቀን ስላላት ዕቅድ አላስቀመጠችም” ሲሉ የግሎባል ኤንድ ሪጅናል ስትራቴጂስ ኢን ዘ ሚድል ኢስት ደራሲ የሆኑት ዶ/ር ሊላ ኒኮላስ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ይህ ሊቀየር የሚችል መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

በአንፃሩ በሊባኖስ ውስጥ ግልጽ የሆነ የስምምነት ማዕቀፍ በመኖሩ የተኩስ አቁም ላይ የሚደራደሩበት መሠረት አለ። ይህም እአአ በ2006 በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል የነበረውን ጦርነት ያቆመውን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1701 መሠረት ያደረገ ነው።

ሄዝቦላህ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል አስወንጭፎ ያደረሰው ጉዳት

የስምምነቱ አብዛኛው ነገር ግልጽ አይደለም። በዚህ መንገድ ሁለቱም ወገኖች እንዲንቀሳቀሱ የመጀመሪያ ዓላማቸውን መከለስ ነበረባቸው። እስራኤል የሄዝቦላህን ስጋት ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እና በወታደራዊ መንገድ ዜጎቿን ወደ ሰሜን እስራኤል በሰላም እንዲመለሱ ማድረግ አልቻለችም።

በአመራሩ፣ በተቋማቱ እና በወታደራዊ ይዞታው ላይ በደረሱ በርካታ ጥቃቶች የተሽመደመደው ሄዝቦላህም የጋዛ ጦርነት ሳያበቃ በእስራኤል ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ላለማቆም ያስቀመጠውን የመጀመሪያ ዕቅድ ያስቀረ ይመስላል።

“[የሄዝቦላህ የገንዘብ እና የርዕዮተ ዓለም ደጋፊ የሆነችው] ኢራን ቡድኑን የበለጠ ወደሚያዳክመው ረዥም ጦርነት እንዲገባ እንደማትፈልግ ግልጽ ነው” ሲሉ ዶክተር ኒኮላስ አክለዋል።

አድናን ኤል-ቡርሽ፣ የቢቢሲ ኒውስ አረቢክ ባለደረባ ከጋዛ

በጋዛ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ስምምነቱ ሄዝቦላህ “የግንባሮች አንድነት” ስትራቴጂን ለመተው እንደ ወሰነ አድርገው ቆጥረዋል። ይህ ፅንሰ-ሀሳብ ከእስራኤል ጋር በጀመረው ጦርነት መጀመሪያ ላይ ዘመቻዎችን በጋራ ለማካሄድ በሄዝቦላህ እና በሐማስ የጸደቀ ጽንሰ-ሀሳብ ነው።

“የትግል ጥምረት” አባል ከሚባሉት መካከል በጋዛ ውስጥ ያሉ ሌሎች ቡድኖችን፣ የየመን ሁቲዎችን እና ሌሎች ትናንሽ የኢራቅ ቡድኖችን ያጠቃልላል።

በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እና በጋዛ ተመሳሳይ ነገር ባለመኖሩ መካከል ያለው ቁልፍ ልዩነት ሄዝቦላህ ድርድሩን ለሊባኖስ መንግሥት ሲተው ሐማስ የጋዛ ድርድርን ከመምራት ባለፈ መቀመጫውን በራማላህ ላደረው የፍልስጤም መንግሥት ለመተው ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው።

በፍልስጤማውያን መካከል ያለው ክፍፍል እና ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ውይይት የሚመራ አንድ እና ዕውቅና ያለው ግዛት አለመኖሩ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት አንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗል።

እስራኤል ሐማስ ዋና ዋና የሚባሉ ሰዎችን ከገደለች በኋላ በቡድኑ አመራር ላይ ክፍተት እንዳለ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ ማለት ሐማስ የተኩስ አቁሙን በብቃት ለመደራደር አቅም የለውም ማለት ነው። በጋዛ ውስጥ እና ከጋዛ ውጭ ባሉ የሐማስ መሪዎች መካከል ያለው የግንኙነት መስመር ችግር ስላለበት ድርድሩን የበለጠ ፈታኝ ያደርገዋል።

“እስራኤል የጋዛን ጦርነት እንደ ዋነኛው ጦርነት ትቆጥረዋለች። ምክንያቱም ጦርነቱን ያነሳሳው ሐማስ እንጂ ሄዝቦላህ ባለመሆኑን ነው። እስራኤል የሐማስ አቅም እንዳዳከመች ሲሰማት ሄዝቦላህ ደግሞ እራሱን ለእስራኤል እንዳቀረበ ተደርጎ ይቆጠራል” ሲሉ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ፋቲ ሳባህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል የተኩስ አቁም ድርድር ስታደርግ ከሐማስ የበለጠ ሄዝቦላህ ጉዳት የማድረስ አቅም እንዳለው ታምናለች ሲሉ ፕሮፌሰር ሳባህ አክለዋል።

“የሄዝቦላህ ሮኬቶች እንደ ቴል አቪቭ እና ሃይፋ በመሳሰሉ ከተሞች ላይ አርፈው በእስራኤል እና ከሰሜን በተፈናቀሉት በሺህዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል” ሲል ሳባህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቤይሩት ላይ ምታደርሰውን ጥቃት “የእስራኤል ጠብ አጫሪነት” ሲሉ የገለጹት አሜሪካ እና ፈረንሣይን የመሳሰሉት አጋር አገራት አመለካከትም እስራኤል ላይ ተጽዕኖ እንዳሳረፈባት ፕሮፌሰር ሳባህ ያምናሉ።

በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር ላይ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች

ሙሃናድ ቱቱንጂ፣ የቢቢሲ ኒውስ አረቢክ ዘጋቢ ከእየሩሳሌም

እስራኤል እና ሊባኖስ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። የሊባኖስ እና የጋዛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ እውነታዎች የተለያዩ መሆናቸው አንደኛው ነው።

ሄዝቦላህ የሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር አካል ሲሆን፣ በሊባኖስ ካሉ በርካታ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ቡድኖች አንዱን ብቻ የሚወክል ነው። አንዳንድ ተንታኞች ሁሉም የሊባኖስ ዜጎች ከእስራኤል ጋር ባለው ግጭት የሄዝቦላህን አመለካከት አይጋሩም ይላሉ።

በጋዛ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በጋዛ ያለው የፖለቲካ እና የጦር የበላይ ሲሆን፣ ፀረ እስራኤል አቋም ባላቸው በጥቂት አንጃዎች ይደገፋል።

ለእስራኤላውያን በሊባኖስ ያለው ጦርነት በጋዛ ካለው ጦርነት የተለየ ነው።

በሊባኖስ የሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ በሰሜን እስራኤል ነዋሪዎች ላይ ያለን ወታደራዊ ስጋት ለማስወገድ እና ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ ያለመ ነው።

እስራኤል ሐማስን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እንዳሰበች አስታውቃለች። ይህ ግብ ግን እስካሁን ሙሉ በሙሉ ሊሳካ አልቻለም። እስራኤል አሁንም በጋዛ ያሉትን 101 ታጋቾችን የማስመለስ ስኬቷ የተኩስ አቁም ድርድሩ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

የእስራኤል የቀድሞ የብሔራዊ ደልንነት ምክር ቤት ሃላፊ ያኮቭ አሚድሮር ግጭቱ ወደ ሌሎች የሊባኖስ አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል በሚል በብዙ ሊባኖሳውያን ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህም በቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ከታየው ጋር የሚመሳሰል ውድመት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

እስራኤል በሊባኖስ የምትከተለውን አካሄድ ከጋዛ ግጭት ለመለየት ያደረገችውን ስልታዊ ውሳኔ እንደሆነም ገልጸዋል። ይህ ስምምነት እስራኤል በጋዛ የሚገኘውን ሐማስን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትኩረት እንድታደርግ ስለሚያስችላት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የተኩስ አቁሙ ስምምነት ትክክለኛ ውጤት በስምምነቱ ላይ ሳይሆን በአፈፃፀሙ ላይ የሚወሰን መሆኑን አሚድሮር ገልፀው፤ ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሚጥስ ከሆነ እስራኤል ልትሰጥ የምትችለው ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠይቀዋል።