
ከ 3 ሰአት በፊት
በሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት እና በክልላዊው ጁባላንድ መሪዎች መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።
የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የጁባላንዱ ፕሬዝደንት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የእስር ትዕዛዝ ያወጣ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የጁባላንድ መንግሥት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
በዋና ከተማዋ የሞቃዲሾው የሚገኘው ባናዲር ክልላዊ ፍርድ ቤት የጁባላንዱ ፕሬዝደንት አሕመድ ማዶቤን በሀገር ክህደት ከሷቸዋል።
የጁባላንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ እና አመፅ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆነዋል ሲል ክስ አቅርቧል።
በባናዲር ክልላዊ ችሎት በአሕመድ ማዶቤ ላይ የወጣው የእስር ማዘዣ ፍርድ ቤቱ የሶማሊያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ እና የይታሰሩ ጥያቄን ከተቀበለው በኋላ ነው።
በእስር ትዕዛዙ መሠረት የሶማሊያ ብሔራዊ ፖሊስ አዛዥ የጁባላንዱን ፕሬዝደንት አሕመድ ሞሐመድ ኢስላም አሊያም በቅፅል ስማቸው አሕመድ ማዶቤን በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት እንዲያቀረብ ታዟል።
የክስ መዛግብት እንደሚያሳዩት ማዶቤ በብሔራዊ አንድነት እንዲሁም በሶማሊያ ሉዓላዊነት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል የሚሉ ክሶች ቀርበውባቸዋል።
ማዶቤ ከሀገር ክህደት በተጨማሪ ምሥጢራዊ የሚባሉ መረጃዎችን ለሌሎች ሀገራት አሳልፈው በመስጠት ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት እና ሕግ ውጪ የሆነ ድርጊት ፈፅማል ተብለው ተከሰዋል።
ይህ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና በጁባላንድ ራስገዝ አስተዳደር መሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ምክንያቱ በአገሪቱ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን ክልላዊ የውክልና ምርጫ በማስቀረት አገራዊ ምርጫ እንኪካሄድ የፌደራል መንግሥቱ መወሰኑን ተከትሎ ነው።
የጁባላንድ መሪዎች ግን ይህ ውሳኔ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ነው በማለት በተናጠል ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ በመወስን ከቀናት በፊት በተካሄደው ምርጫ አሕመድ ማዶቤ ለሦስተኛ ጊዜ በመሪነት ተመርጠዋል።
- “ወደ ቤታችን ልንመለስ ነው፤ ደስ ብሎናል” – በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንከ 6 ሰአት በፊት
- “መምህር በመሆኔ አዘንኩ” – የኢትዮጵያ መምህራን እሮሮ27 ህዳር 2024
- እስራኤል በሦስት ወራት ጥቃት የገደለቻቸው የሂዝቦላህ ቁልፍ መሪዎችከ 6 ሰአት በፊት
ይህን የእስር ትዕዛዝ ተከትሎ የጁባላንድ ቴሌቪዥን ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማዘዣ ወጥቷል ከማለት ውጭ ያለው ነገር የለም።
በአውሮፓውያኑ 2012 የጁባላንድ ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት ማዶቤ ባለንበት ኅዳር ወር ለሦስተኛ ጊዜ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
የሶማሊያም ማዕከላዊው መንግሥት ግን ማዶቤ ለሦስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን መመረጣቸው ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም ሲል ይሞግታል።
በክልላዊው አስተዳደር እና በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት ተጋግሎ የፌዴራሉ ወታደሮች ራስ ካምቦኒ ወደተባለችው ኬንያ ድንበር ላይ በምትዋስን ከተማ ላይ ሰፍሯል።
ማዕከላዊው መንግሥት ጦሩን ማደራጀቱን የተመለከቱት የጁባላንድ ወታደሮችም ለሚፈጸም የፌደራል መንግሥቱ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በተጠንቀቅ መቆማቸው ተሰምቷል።
የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት ጁባላንድ እና ማዕከላዊው መንግሥት ከግጭት ተቆጥበው ውይይት በማድረግ ውጥረታቸውን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የሶማሊያ ዓለም አቀፍ አጋሮች ባለፈው ሳምንት በጋራ ባወጡት መግለጫ ጁባላንድ እራሷን ወዳገለለችበት ብሔራዊ የምክክር ጉባኤ በመመለስ በፌደራል ምንግሥቱ እና በግዛቲቱ መካከል ያለውን አለመግባባት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የአጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በጁባላንድ ያለው ውጥረት እጅግ እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ግንባሩ በተለይም ራስ ካያምቦኒ በተባለ አካባቢ የሶማሊያ ፌደራል ኃይሎች መሰማራታቸውን ተከትሎ የጁባላንድ አስተዳደር ኃይሎችም መንቀሳቀሳቸውን በማንሳት ውጥረቱ መባባሱን ገልጿል።
እየተቀሰቀሰ ያለው ቀውስ የጁባላንድን እና አጠቃላዩን የሶማሊያ ቀጣናን መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚጥል ተናግሯል።
እየተባባሰ የመጣው መቃቃር የንጹሃንን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ኃይሎች ሁኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ በቀጣናው ደኅንነት እና ልማት ላይ ተጽዕኖ ሊያደርሱ ይችላሉም ብሏል።
ኦብነግ በሶማሊያ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል።
በመሆኑም ያለው ግንባሩ ሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና የጁባላንድ አስተዳደር ለአገር አንድነት እና የጋራ ዓላማ ሲሉ ልዩነታቸውን በምክክር እና ድርድር እንዲፈቱ ጠይቋል።
ግንባሩ አክሎም በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሁሉም ሶማሌዎች ውጥረቱ እንዲረግብ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።