
ከ 6 ሰአት በፊት
እስራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ወደ የቤታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ።
በአሜሪካ አማካይነት እስራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ከፍተኛ ግጭት ከነበረባቸው የሊባኖስ ከተሞች ተፈናቅለው የነበሩ ኢትዮጵያውያንም ወደ ቤታቸው ለመመለስ እየተዘጋጁ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእስራኤልን ጥቃት በመፍራት ተፈናውለው የነበሩ ሰዎች በብዛት ወደ መኖሪያ መንደራቸው እየተመለሱ በመሆናቸው የሊባኖስ ጎዳናዎች ተጨናንቀው ታይተዋል።
የእስራኤል ጦር ከሁለት ወራት በፊት በመላዋ ሊባኖስ ከባድ የአየር ድብደባ መፈጸም መጀመሩ እና እግረኛ ወታደሮችን ማሰማራቱ ይታወሳል።
በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ረቡዕ፣ ኅዳር 18/2017 ዓ.ም. እንደተጀመረም ተገልጿል።
በዚህም እፎይታ የተሰማቸው ቤት ንብረታቸውን ትተው የተፈናቀሉት ሊባኖሳውያን ብቻ ሳይሆኑ እንጀራ ፈምገው በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጭምር መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሊባኖስ የምትኖረው ኢትዮጵያዊት እናትዬ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ነዋሪዎች ደስተኛ ሆነው ወደ የቤታቸው እየተመለሱ መሆናቸውን እንዲሁም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ዓለምም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ወደቤቷ እንደምትመለስ ገልጻለች።
ነበትዬ በሚባል አካባቢ ትኖር የነበረች እና በአካባቢው ጦርነት ሲባባስ ወደ ቤይሩት ሸሽታ የነበረችው ሌላ ኢትዮጵያዊት ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት ከባድ ችግር ውስጥ እንደነበረች ለቢቢሲ ተናግራለች።
በጦርነቱም ወቅት “ቤታችን ተሰባብሮብን ነበር። በጣም ተቸግረን ቆይተናል” የምትለው ኢትዮጵያዊቷ አሁን ግን የተኩስ አቁም ስምምነት በመደረጉ ሰዎች ወደ የቤታቸው እየተመለሱ ነው ትላለች።
“መጀመሪያ ተፈናቅለን ወደ ቤይሩት መጥተን ሰው ጋር ተጠግተን ነበር የምንኖረው። አሁን ግን ተመለሱ ተብለናል” ብላለች ኢትዮጵያዊቷ።
እሷ ግን ትኖርበት ወደነበረው አካባቢ ለመመለስ ስለፈራች ባለችበት ለተወሰነ ጊዜ በመቆየት ሁኔታውን እንደምትመለከት ገልጻለች።
“እስራኤል ሰላም አውርዳ ሁሉም ሰው ወደ የቦታው እየተመለሰ ነው። ድሮ እኖርበት ከነበረው ቦታ የፈረሰም ያልፈረሰም አለ። ስለምፈራ አሁን መመለስ አልፈልግም” ብላለች።

የሄዝቦላህ ቃል አቀባይ ኢብራሒም አል-ሙሳዊ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ለማድረግ ስምምነት ላይ የደረሱት “በንጹሃን ላይ የሚፈጸም የዘር ጭፍጨፋን ለማስቆም” ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄን ሱለቨን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ “ለሳምንታት እና ለወራት በዘለቀ የዲፕሎማሲ ጥረት አማካይነት” በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማድረግ ችላለች።
ሊባኖሳውያን የተኩስ አቁም ስምምነቱ በመደረጉ በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ሆኖም ግን በርካታ መኖሪያ አካባቢዎች እና ሕንጻዎች በውጊያው ወቅት ወድመዋል።
- እስራኤል እና ሄዝቦላህ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጆ ባይደን አረጋገጡ27 ህዳር 2024
- የጦርነት ውጥረት በነገሠባት ሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ?6 ነሐሴ 2024
- በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጭንቀት፡ “የአራት ወር ልጄን ምን ላብላት?”1 ጥቅምት 2024
‘በጦርነት መሀል ልጄን ወለድኩ’
በሊባኖስ የምትኖረው ኢትዮጵያዊት ስደተኛ እናትዬ እንዳለችው፣ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ነዋሪዎች ደስተኛ ሆነው ወደ የቤታቸው እየተመለሱ ነው።
“በጣም ደስ ይላል፤ ሰዉ ወደ የቦታው እየተመለሰ ነው” ያለችው እናትዬ፣ በጦርነቱ መሀል ልጇን በሰላም እንደወለደችም ተናግራለች።
ለወራት በድንበር አካባቢ ብቻ ተወስኖ የነበረው በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል የተካሄደው መጠቃቃት ተፋፍሞ ወደ ለየለት ጦርነት ሲገባ የስድስት ወር ነፍሰ ጡር የነበረችው እናትዬ ደም ፈሷት ሆስፒታል ገብታ ነበረ።
“ልጄን የወለድኩት በጦርነቱ መሀል ነው። ከወለድኩ አሁን ሳምንት አለፈኝ። ልጄን ማርያማዊት አልኳት” በማለት በአስቸጋሪው ወቅት ለመውለድ መብቃቷን ለቢቢሲ ተናግራለች።
“በ6 ወር ከ15 ቀኔ ደም ፈሶኝ ሆስፒታል ገባሁ። በጦርነቱ ድንጋጤ ምክንያት ልጄን በሰባት ወሯ ነው የወለድኳት። ነገር ግን አሁን ልጄ ደኅና ናት።”
የሊባኖስ ጦር በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት በደቡብ ሊባኖስ ያለውን ይዞታ እያጠናከ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ነዋሪዎችም በደቡባዊ ሊባኖስ ወደሚገኙት የታይር፣ ጀብሊ እና ማርጃውን አካባቢዎች ሲመለሱ የእስራኤል ጦር ካለባቸው አካባቢዎች እንዲርቁም ተነግሯቸዋል።
ስምምነቱ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል እአአ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የቋጨው የተባበሩት መንግሥታት 1701 በተሰኘው ውሳኔ የተመሠረተውን ድንበር መሠረት ያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።
በእስራኤልና በሄዝቦላህ በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹን እና መሣሪያዎቹን ከሊባኖስ እና ከእስራኤል ድንበር ማለትም ከሊታኒ ወንዝ 30 ኪሎ ሜትር ማራቅ ይኖርበታል።
የግብፅ እና የዮርዳኖስን መሪዎች ጨምሮ በቀጠናው ያሉ መሪዎች ከአንድ ዓመት በላይ የሆነውን በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ተመሳሳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ አሳበዋል።
በሊባኖስ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አብዛኞቹ በቤት ውስጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ስደተኛ ሠራተኞች ይገኛሉ።
ኢትዮጵያዊቷ ስደተኛ እናትዬ በአሁኑ ወቅት የምትገኘው ቤይሩት ውስጥ ሸሙን በሚባል አካባቢ ሲሆን፣ ትኖርበት ወደ ነበረው ነበትዬ ጀኑቭ አካባቢ አሁን እንደማትመለስ ገልጻለች።
“አሁን እስራኤል ሰላም አውርዳ ሁሉም ወደ የቤቱ እየተመለሰ ነው። ሰውም ደስታውን እየገለጸ ነው። መንገዱ ሁሉ ወደ የቤቱ በሚመለስ ነው ተጨናንቋል። እኔ ግን አራስ ስለሆንኩ እና እኖርበት የነበረውን ቤትም ስለመቱት እዚህ ትንሽ ቆይቼ ጠንከር ስል እመለሳለሁ” ብላለች።
በጦርነቱ ወቅት ጓደኛዋ ጋር ተጠልላ ልጇን እንደወለደች ተናግራለች። ነፍሰ ጡር ሆና በጦርነቱ መሀል ማለፍ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበርም ገልጻለች።
“ሐኪም ቤት ራሱ የሚቀበለን አጥተን ነበር. . . ግን ይለፍ አናውራው. . . ብቻ እግዚአብሔር ይመስገን። በጦርነቱ ወቅት ብዙ ወላድ ነበር የመጣው። ግን ለበጎ ነው ፈተና የሚመጣው” ብላለች።
ትኖርበት የነበው አካባቢ ጦርነቱ ከነበረባቸው ቦታዎች አንዱ ሲሆን፣ አሁን ሰዎች መመለስ መጀመራቸውን ገልጻለች። እሷም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቤት ተከራይታ እንደምትመለስ አክላለች።
በጦርነቱ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ይረዳዱ እንደነበርም ሳትጠቅስ አላለፈችም።
“በጦነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያ ትብብር ነበረን። ሥራ ያለው ብር እያዋጣ ምግብ እና ልብስ ይገዛልን ነበር። ጦርነት እንዳለ እንዳናስብ ነው ያደረጉን” ስትል ገልጻለች።
እስራኤል እና ሄዝቦላህ ለ13 ወራት የዘለቀውን ውጊያ ለመቋጨት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከገለጹ በኋላ፣ የተኩስ አቁሙ ግጭትን በዘላቂነት ወደ ማቆም ስምምነት ለመድረስ ያለመ እንደሆነ አመልክተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሔዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እስራኤል ጥቃት ከመሰንዘር ወደኋላ እንደማትል ተናግረዋል።
እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ ሊባኖስ ውስጥ የእግረኛ ጦር ወረራ በመፈጸም የተቀናጀ ጥቃቷን አጠናክራ መቆየቷ ይታወሳል።
በሊባኖስ ውስጥ በአሥርት ዓመታት ውስጥ ከታዩ የከፋ በተባለው ጦርነት ከ3 ሺህ 823 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

‘ወደ ቤታችን ልንመለስ ነው’
በአሜሪካ አደራዳሪነት በተደረሰው በዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት እስራኤል በሚቀጥሉት 60 ቀናት ከወረረቻቸው የሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ቀስ በቀስ ወታደሮቿን ታስወጣለች። በምትኩም የሊባኖስ መንግሥት ወታደሮች ስፍራውን የሚቆጣጠሩት ይሆናል።
ስምምነቱ በአካባቢው ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት እና በሁለቱም አገራት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ሲሉ የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ይከታተላሉ የተባሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ገልጸዋል።
በሊባኖስ የምትኖረው ኢትዮጵያዊት ስደተኛ ዓለም “አሁን ወደ ቤታችን ልንመለስ ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከደቡባዊ ሊባኖስ ተፈናቅላ በቤይሩት እየኖረች የነበረችው ዓለም ሰው ጋር ተጠልላ እንደቆየች እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ ወደ ቤቷ እንደምትመለስ ተናግራለች።
“የመጨረሻ ቀን ብለው ትላንት [ኅዳር 17] እየመቱ ነበር። ሌሊት አራት ሰዓት ላይ [የተኩስ ማቆም] ፊርማ ተደረገ ተባለ። አሁን ወደ ቤታችን እንመለሳለን። ደስ ብሎናል” ብላለች።
ከደቡብ ሊባኖስ “ምንም ሳንይዝ ነው የወጣነው” የምትለው ዓለም፣ የጦርነቱ ወቅት “በጣም አስፈሪ ነበር” ስትል ገልጻለች።
“ሰው አገር ላይ ጦርነት ውስጥ መኖር በጣም ከባድ ነው። ስንቱ ሞቷል። ሐበሾችም ሞተዋል” ትላለች።
ትኖርበት የነበረው ቤት በጦርነቱ እንደተጎዳ ገልጻ “አከራዬ እሷ ጋር እንድቆይ ስለጠየቀችኝ እሷ ጋር ሄጄ ነው የምቀመጠው” ብላለች።
“በጦርነቱ ወቅት ቆይታችን በጣም ያስፈራ ነበር። ስንት ጊዜ የሚበላ ጠፍቶ ጭንቅ ነበር። መንገድ ላይ ወይም ሰው ጋር ተጠግተን ነበር የምንኖረው። አሁን ግን ቤታችን ሄደን ባንበላም እንኳን እዚያው ቤታችን ሄደን ብንቀመጥ ደስ ይለናል። ሰው ጋር እስከ መቼ ተጠግቶ መኖር ይቻላል? ደግሞ ልጅ ይዞ ሰው ጋር መጠጋት ይከብዳል።”
ሰዎች ወደቤታቸው መመለስ በመቻላቸው ደስታቸውን በአደባባይ እየገለጹ መሆኑን የተናገረችው እናትዬ፣ መንገዱ ወደ መኖሪያቸው በሚመለሱ ሰዎች እንደተጨናነቀም ገልጻለች።
“አሁን በቴሌቭዥን ቁጭ ብለን ስናይ ሰው ወደየቤቱ በመመለሱ ደስታውን ሲገልጽ ይታያል። እኛም ዛሬ [ኅዳር 18] ነበር ለመሄድ ያሰብነው። ግን መንገዱ ወደ የቤቱ እየሄደ ባለ ሰው ተጨናንቋል። ነገ እንሄዳለን።”
ለሦስት ወራት በዘለቀው ይፋዊ የእስራኤል ከባድ ጥቃት በበርካታ የሊባኖስ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራት በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቻቸውን ለማውጣት ቢፈልጉም የአውሮፕላን በረራዎች በመቋረጣቸው አዳጋች ሆኖባቸው ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰኑትን ለማስወጣት መቻሉን መዘገቡ ይታወሳል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ የሚገኙ ሲሆን፣ ቢቢሲ በተጨማባጭ ማረጋገጥ ባይችልም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ኢትዮጵያውን በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል።